ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

Read Time:3 Minute, 53 Second

የ20ኛ የጨዋታ ሳምንት አሰልጣኝ ነክ የትኩረት ነጥቦች እና ዓበይት አስተያየቶችን እንደሚከተለው ቃኝተናል።

👉 የአሰልጣኝ አሸናፊ አስተያየት

በዘንድሮው የውድድር ዓመት ጠንካራ ቡድን ከገነቡ አሰልጣኞች አንዱ የሆኑት የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከፋሲል ከነማ ጋር ካደረጉት ጨዋታ ጅማሮ ቀደም ብሎ ለሱፐር ስፖርት በሰጡት አስተያየት ክለቡ የሊጉ ቻምፒዮን የመሆኑ ጉዳይ አይቀሬ ቢሆንም አሸንፈው በመውጣት የሚያረጋግጡበትን ጊዜ ለማዘግየት ወደ ሜዳ እንደሚገቡ በዚህ ገልፀው ነበር።

” በዚህ ዓመት ምርጡ ቡድን ፋሲል ነው። በዚህ ጨዋታም አሸንፈው በመውጣት የሊግ አሸናፊነታቸውን ቶሎ ማረጋገጥ ነው የሚፈልጉት። ግን ከፋሲካ በፊት እንዳያደርጉት እንጥራለን። ”

አሰልጣኙ እንደ አስተያየታቸው በጨዋታው ላይም ፋሲልን በሚገባ የፈተነ ቡድን ይዘው የቀረቡ ሲሆን እስከመጨረሻው ደቂቃ ተፋልመው አቻ ውጤት ይዘው ወጥተዋል። ቡድኑ የፋሲልን እንቅስቃሴ ለመግታት የሞከሩበት መንገድ ጥሩ የነበረ ሲሆን በተደጋጋሚ በቆሙ ኳሶች የፈጠሯቸው አደጋዎች ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዘው እንዲወጡ ረድቷቸዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየትም “ዋንጫዋን ፋሲል ወስዶታል ማለት ይቻላል። ፋሲል እንደሚታወቀው የ 44 ደብር ባለቤት ነው። የፋሲልን ሀገር እንዲያደምቁት ነው የምፈልገው። ስለዚህ ቀጣይ ጨዋታቸውን አሸንፈው ደስታቸውን ያከብራሉ ብዬ ነው የማስበው። ” ብለዋል።

👉 ያለ ዋና አሰልጣኝ የገቡት ቡድኖች

በኮቪድ ምክንያት ባለፉት ሁለት ሳምንታት አሰልጣኞች ቡድኖቻቸውን መምራት ያልቻሉ ሲሆን በዚህ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከቀደሙት በተጨማሪ ወላይታ ድቻም ሰለባ ሆኗል።

በድሬዳዋ ቆይታው የኮሮና ውጤት አብዝቶ የፈተነው ወላይታ ድቻን ግብ ጠባቂን በተጫዋችነት ጭምር በማሰለፍ ወደ ሜዳ የገቡት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው በዚህ ሳምንት ሰበታ ከተማን የሚገጥመው ስብስባቸውን በተሟላ ሁኔታ ማግኘታቸው እፎይ ቢያስብላቸውም ራሳቸው የዚሁ ሰለባ ሆነው ቡድናቸውን ሳይመሩ ቀርተዋል። ቡድኑ በምክትል አሰልጣኙ ዳዊት ሀብታሙ እየተመራ ከሰበታ ጋር ያደረገውን ጨዋታ 2-0 ከመመራት ተነስቶ በአስገራሚ ትግል አንሰራርቶ አቻ ተለያይቷል።

ከአሰልጣኞች አለመገኘት ጋር በተያያዘ ባህር ዳር ከተማ በሀዋሳ ከተማ በተሸነፈበት እንዲሁም ወልቂጤ ከተማ ከአዳማ ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ የባህር ዳር እና ወልቂጤ ምክትል አሰልጣኞች ቡድናቸውን መርተዋል።

👉 የዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የደስታ ስሜት

በ20ኛው የጨዋታ ሳምንት በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ባገናኘው ጨዋታ ድሬዎች በሙኅዲን ሙሳ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አሸንፈው ወሳኝ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ታድያ የጨዋታውን መጠናቀቅ የምታበስረው የዳኛው ፊሽካ በተሰማበት ቅፅበት የድሬዳዋ ከተማው ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ደስታቸውን የቀለፁበት አካላዊ እንቅስቃሴ ውጤቱ ምን ያህል ይፈልጉት እንደነበር የሚያሳይ ነበር።

በተደጋጋሚ አየሩን በቡጢ እየቀዘፉ የተሰተዋሉት አሰለጣኞቹ ከፍ ባለ ስሜት የአሰልጣኞች ቡድን አባላት እና ተጠባባቂ ተጫዋቾችን ሲያቅፉም እንዲሁ ተስተውለዋል።

👉 ዓበይት አስተያየቶች

*ታደሰ ጥላሁን ባህር ዳር ከተማ እና የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቦታ ይዞ ለመጨረስ ስላለው ህልም

“ከቦታው እየሸሸ ነው ማለት አይቻልም። ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ስታየው ይህ ጨዋታ ወሳኝ ነበር። ነገር ግን ወጣን የሚያስብል አይደለም። ወደፊት ብዙ ቻሌንጅ ይጠብቀናል። በዛ ውስጥ የምንፈልገውን ነገር አሳክተን እዛ ላይ እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ።”

*አብርሀም መብራቱ ከመመራት ተነስተው ስለተሸነፉበት ጨዋታ

“ከሁለተኛው ጎል ይልቅ የመጀመሪያው በጣም አበሳጭቶኛል። ምክንያቱም 2-0 እየመራን ነው። የተካላካዮቻችን ትኩረት ማነስ እና የግብ ጠባቂያችን የጊዜ አጠባበቅ ነው። አምስት ከሀምሳ ውስጥ ነው በግንባር ገጭቶ ያገባው ስለዚህ እዛ ጋር የተፈጠረ ችግር ነው። ሁለተኛው ላይ ግን ተጭነውን ፣ የሚችሉትን አድርገው ያስቆጠሩት ግብ ስለሆነ እሱ ብዙም አላበሳጨኝም። በተረፈ ግን ጨዋታውን የተቆጣጠርንበት መንገድ በጣም ጥሩ ነበር። ሁለተኛው አጋማሽ ውጤት ለማስጠበቅ ወደ ኋላ ማፈግፈጋችን ዋጋ አስከፍሎናል ። ይህንን በቀጣይ አስተካክለን እንደምንመጣ አስባለሁ።”

*ዳዊት ሀብታሙ ከተከላካዮች ጀርባ በነበሩ ክፍተቶች በሰበታው ጨዋታ ስላስተናገዷቸው ግቦች

“ክፍተት የመስጠት ጉዳይ ሳይሆን ጊዜው እና እንቅስቃሴው የፈጠረው ነው። ቅጣት ምት ተገኝቶ እሱን ለመሻማት በሄደበት ሰዓት እኛ መልዕክት እያስተላለፍን ነበር። ምክንያቱም እነሱ ፊታቸውን አዙረው ወደኛ ግብ ነው ያሉት እኛ ደግሞ ጀርባችንን ሰጥተን ነው። እና ትርፍ ሰዎች አንድ ለአንድ ሩጫ በሚደረግበት ሰዓት ነግረን ነበር ። በመልዕክቱ የመግባባት ችግር ስለነበር ሰበታ ያንን ጎል ማስቆጠር ችሏል።”

*ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ስለአማካይ ክፍላቸው

“ኳስ ስናጣ የመስመር አጥቂዎቻችን ወደ ኋላ ተመልሰው አምስት ያደርጉልን ነበር አማካዩን። እነጁኒያስ ይህ ዓይነት ባህሪ ስላላቸው ነው መስመር ላይ ያወጣናቸው እንጂ ፊት መስመር ላይ የመጨረሻ አጥቂ ሆነው መጫወት ይችላሉ። ነገር ግን ዛሬ ውጥረት ነበረው እና የምንጫወትበት መንገድ ይህ ነበር ከማለት በላይ ማሸነፉ አስፈላጊ ነበር ለእኛ።”

*ገብረመድህን ኃይሌ ከአሸናፊነት መንገድ ስለመውጣታቸው እና የወራጅነት ስጋት

አንወጣም። ምክንያቱም ከዚህ በኋላ ብዙ ጨዋታዎች አሉ። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ጠንክረን ሰርታን ከመውረድ ስጋት እንወጣለን ብዬ አስባለሁ። ዛሬ ተጫዋቾቼ የምንፈልገውን ማድረግ አልቻሉም። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ዝግጁ አልነበሩም። እኔ አልገባኝም ፤ ለራሴም ሚስጥር ነው የሆነብኝ። ተጋጣሚ እንደልቡ እንዲጫወት መፍቀድ ፣ ተነሳሽነቱም ወርዷል ለምን እንደሆነ አልገባኝም። በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ቀርበናል ነገር ግን ብዙ ነገሮች ምቹ አልነበሩም። ውሳኔዎቹ ፣ የነበረው የኃይል አጨዋወት ፣ ብዙ ነገሮች ምቹ አልነበሩም። ከዚህ አንፃር ተሸንፈን ወጥተናል። ግን ለሚቀጥለው ስድስት ጨዋታ ጊዜ አለን ። ጠንክረን ሰርተን ነፃ እንሆናለን ብዬ አስባለሁ።

*ፀጋዬ ኪዳነማርያም ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሰከንዶች ውስጥ ግብ ስለማስቆጠራቸው እና መልበሻ ክፍል ስላወሩት ነገር

ባለፈውም ከሀዋሳ ከተማ ጋር ስንጫወት በተመሳሳይ ደቂቃ ጎል አስቆጥረናል። ብዙ ጊዜ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች ክለቦች እንጠንቀቅ ነው የሚሉት። እኛ ግን የራሳችን ስትራቴጂ አለን። ብዙ ጊዜም ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ተጋጣሚዎች ትኩረት የሚያጡበት የተለመደ ነገር አለ። ይህንንም ነገር ብዙ ጊዜ ለመጠቀም እንፈልጋለን። ዞሮ ዞሮ ግን ብዙ መሻሻል ያሉብን ነገሮች አሉ። ድክመቶቻችንንም ማስተካከል አለብን። በተለይ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴያችን ቅርፁን የጠበቀ እንዲሆን ማድረግ አለብን። በአጠቃላይ ግን በመሻሻል እና በጥረት ላይ ነው የምናተኩረው።

*ዘርዓይ መሉ ስለበላይ ዓባይነህ ቅያሪ እና ስለማስቆጠሩ

መጀመሪያም አስነስተነው ነበር፤ አጥቂ ለመጨመር። በዝግጅት ላይ እያለን ቅጣት ምት አገኘን፤ ወዲያው ነው ያስገባነው። ምክንያቱም ቅጣት ምት መቺ ስለሆነ ያንን ይጠቀማል የሚል ነገር ነበረን። ልምምድ ላይም ይመታል። የተሻለ በመሆኑም ያንን ዕድል ተጠቅሞበታል።

© ሶከር ኢትዮጵያ

Happy
Happy
0 %
Sad
Sad
0 %
Excited
Excited
0 %
Sleepy
Sleepy
0 %
Angry
Angry
0 %
Surprise
Surprise
0 %
ያጋሩ
error: Content is protected !!