ፕሪምየር ሊጉን የሚያስተናግደው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የማሻሻያ ሥራዎች መጠናቀቃቸው ተገለፀ

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻውን ዙር ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ገልጿል።

በአዲስ አበባ ጅማሮውን አድርጎ እና በጅማ፣ ባህር ዳር አሁን ደግሞ በድሬዳዋ እየተከናወነ 20ኛ ሳምንቱ ላይ የደረሰው ይህ ውድድር ከሚያዝያ 26 በኋላ አምስተኛ አስተናጋጅ ሆና በተመረጠችው ሀዋሳ ከተማ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎችን የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ፕሪምየር ሊጉን በሚመሩት የሊግ ካምፓኒ የበላይ አካላት አማካኝነት ሁለት ጊዜ የቅድመ ዝግጅት ሒደቱ የተገመገመ ሲሆን በምልከታቸውም ወቅት መሻሻል እና መስተካከል አለባቸው ያሏቸው ጉድለቶችን የማረም ሥራ ላይ መጠመዳቸውን የሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አንበስ አበበ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ አንበስ አበበ ሊግ ካምፓኒው በተለየ መልኩ የመጫወቻ ሜዳው መሻሻል እንዳለበት ማሳሰቡን ገልፀው ይህን የማስተካከል ስራ እንደተሰራ ብሎም የመታጠብያ፣ መፀዳጃ እና የትጥቅ መቀየሪያ ክፍሎችን በማዘጋጀት ያለፉትን ጊዜያት እንዳሳለፉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ የሲዳማ ክልል እና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመሆን የሊግ ካምፓኒው ፍቃደኛ የሚሆን ከሆነ ጨዋታዎችን በምሽት ለማካሄድ የመብራት ገጠማ ተከናውኖ መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡ የምሽት ጨዋታዎች ስታዲየሙ እንዲያስተናግድ ይሁንታን ከሊግ ካምፓኒው የሚያገኙ ከሆነም መብራት እንዳይቋረጥ ቅድመ ዝግጅት እንዳጠናቀቁ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

ከስታዲየሙ ዝግጅት በተጨማሪ ክለቦች ሊያርፉባቸው የሚችሉባቸው አስራ ስምንት ሆቴሎች እና ለልምምድ የሚረዱ ስድስት ሳር ለበስ ሜዳዎች የተዘጋጁ ሲሆን የሊግ ካምፓኒው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ላይ ወደ ሀዋሳ በመጓዝ የመጨረሻ የዝግጅቱን ቅድመ ምልከታን ከተመለከቱ በኋላ የመጨረሻ ውሳኔን እንደሚያስተላልፉ ለማወቅ ችለናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ