ከፍተኛ ሊግ | የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታዎች መደረግ ጀምረዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፌድራል ፖሊስ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል፡፡

መከላከያን ተከትሎ ምድቡን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የመጨረሻ ጨዋታውን ከከፍተኛ ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠውን ወሎ ኮምቦልቻን ገጥሞ 4-1 አሸንፏል። ተመጣጣኝነት ያለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያየንበት ነገር ግን የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን ለመመልከት ብዙም ባልታደልንበት የመጀመሪያው አጋማሽ ወሎ ኮምቦልቻዎች ኳስን በተወሰነ መልኩ በመጫወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ባማረ መልኩ መድረስ ቢችሉም ፍፁም ደካማ በነበረው የአጥቂ ክፍላቸው ምክንያት ጎል ማስቆጠር ተቸግረዋል። በአንፃሩ በመስመር አጨዋወት አጋድለው ጥቂት የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር የጣሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በተለይ በወጣቱ የመስመር አጥቂ ፀጋ ደርቤ አማካኝነት የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ተመልክተናል፡፡

31ኛው ደቂቃ ከቀኝ በኩል ፀጋ ደርቤ ወደ ግራ ላደላው አንዳርጋቸው ይላቅ ሰጥቶት ተጫዋቹ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በቀላሉ መጠቀም ያልቻለበት እና ራሱ ፀጋ ደርቤ ከወሎ ኮምቦልቻው ግብ ጠባቂ ጀማል አሊ ጋር ተገናኝቶ የሳተበት ቅፅበት እጅጉን አስቆጪዎች ነበሩ፡፡ መደበኛው አርባ አምስት ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንድ ሲቀር ደግሞ አቤል ታሪኩ ኤሌክትሪክን ቀዳሚ የሚያደርግ ዕድል አግኝቶ ስቷታል፡፡

ከእረፍት መልስ የአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ቡድን የተጫዋቾች ለውጥ ካደረገ በኃላ ይበልጥ የማጥቃት ፍላጎቱ ጨምሮ ታይቷል፡፡ በዚህም 50ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ደርቤ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል፡፡ 56ኛ ደቂቃ ደግሞ ተከላካዮች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም የተሻ ግዛው ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ 71ኛው ደቂቃ ከግራ የማዕዘን ምት አካባቢ የተገኘውን የቅጣት ምት ተቀይሮ የገባው ሚካኤል ለማ ሲያሻማ በእንቅስቃሴ ሜዳ ላይ ጥሩ ቆይታ የነበረው ተከላካዩ ብሩክ ጌታቸው በግንባር በመግጨት ሦስተኛ ጎል አክሏል፡፡

80ኛው ደቂቃ በይሁን ደጀኔ ጎል ወደ ጨዋታ ለመመለስ የአሰልጣኝ ሻምበል መላኩ ቡድን ሙከራ ቢያደርግም የተሻ ግዛው በጭማሪ ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛ ለክለቡ ደግሞ አራተኛ ጎል ከመረብ አዋህዶ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በስተመጨረሻ 4ለ1 አሸንፎ ውድድሩን አገባዷል፡፡

ከሰዓት በቀጠለው የዕለቱ የምድቡ ሁለተኛ ጨዋታ በደሴ ከተማ እና ፌዴራል ፖሊስ መካከል ተደርጎ ፌዴራል አንድ ለምንም አሸንፏል። እጅግ ከባድ ዝናብ ባጀበው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ብዙም ሳቢ የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ማስተዋል ባንችልም 20ኛው ደቂቃ አጥቂው አንተነህ ተሻገር ያስቆጠራት ብቸኛ ጎል ፌድራል ፖሊስ 1ለ0 እንዲረታ አስችላለች፡፡

በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ዛሬ አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ደቡብ ፖሊስ ከ ወራቤ ሁለት አቻ ተለያይተዋል። ተስፋዬ ፈለቀ እና ዮናታን ወልዴ ለደቡብ ፖሊስ፣ ሀብታለም ታፈሰ እና ሙሰፋ ያሲን ለወራቤ አስቆጥረዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ