በመጨረሻው የሳምንቱ ትኩረታችን ሌሎች መዳሰስ የሚገባቸው ነጥቦችን ያሰናዳንበት ፅሁፍ አነሆ።
👉የምሽት ጨዋታዎች እና ትሩፋታቸው
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛዋ ተረኛ አዘጋጅ ከተማ ድሬዳዋ ከተማ ከሌሎች ከተማዎች በተለየ የምሽት ጨዋታዎችን ዳግም ወደ ሊጋችን መመለስ ችለዋል።
በተለይ እንደ ድሬዳዋ ባሉ ሞቃታማ ከተሞች በምሽት የሚደረጉ ጨዋታዎች በንፅፅር ከቀትሯ ፀሐይ መጥለቅ ጋር በተያያዘ የተሻለ ነፋሻማ እና ቀዝቀዝ ያለ አየር በመመኖሩ ለእግርኳስ ጨዋታዎች ምቹ የአየር ፀባይ እንደሆነ ይነገራል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በድሬዳዋ ስታዲየም በተለይ በምሽት በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ለወትሮው በጨዋታዎች ከምንመለከታቸው ቀርፈፍ ካሉ ጨዋታዎች በተሻለ በፍጥነታቸው ከፍ ያሉ እና ጥሩ ፉክክር የሚደረግባቸውን ጨዋታዎች በተደጋጋሚ እየተመለከትን እንገኛለን። በዚህም የተነሳ የጨዋታዎች የአሰልቺነት ባህሪ እየቀነሰ መምጣቱን በድሬዳዋው ውድድር በስፋት እየተመለከትነው እንገኛለን።
በመሆኑም አወዳዳሪው አካል ይህን በመነሻነት በመውሰድ በቀጣይ በሚኖሩ የውድድሩ ሒደቶች ላይ አማራጮችን በደንብ በማጤን፣ የውድድሩን የሜዳ ላይ ፉክክር መንፈስ እና ጥራቱን ከመጨመር አንፃር እንደ ሁነኛ አማራጭ በመውሰድ የምሽት ጨዋታዎች በሊጉ በስፋት የሚደረጉበትን አግባብ መፍጠር ላይ መሥራት ይኖርበታል።
👉ለሌሎች ተምሳሌት የሚሆነው የድሬዳዋ ስታዲየም እድሳት
በሀገራችን በተለየ በትላልቅ ከተሞች የሚገኙ ስታዲየሞች ከተሞች የደረሱበትን የእድገት ደረጃ የሚመጡ ስላመሆናቸው ይነገራል። ዘመናዊ ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ብሎም ለጎብኚዎች በቂ እና ምቹ የሆነ መሰረተ ልማቶች እንደሚያስፈልጋቸው ግልፅ ነው። የስፖርት መሠረተ ልማትም የዚሁ ሒደት አንድ አካል መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።
በቀደሙት ዓመታት ከአዲስ አበባ ስታዲየም ቀጥሎ የሚጠራው ይህ ጥንታዊ ስታዲየም በቀደሙት ዓመታት በርከት ያሉ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ውድድሮች ያስተናገደ መሆኑ ይታወሳል። ታድያ ይህን ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ተስኖት የነበረውን ስታዲየምን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ባለፉት ጥቂት ዐዓመታት ሲሰሩ ቆይተዋል።
በዚህም የመሩጫ ትራክን ጨምሮ የመጫወቻውን ሳር ሙሉ ለሙሉ የመቀየር ብሎም የስታዲየሙን የተመልካች የማስተናገድ አቅም ለማሻሻል እና የመብራት ገጠማ በማድረግ ከመጨረሻው ምዕራፍ የደረሱ በርካታ ሥራዎች እየተከወኑለት ይገኛል።
ታድያ ቀሪ ስራዎች ቢቀሩትም በአንዳንድ ትላልቅ ከተሞች መሰረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው ያልተገነቡት ስታዲየምችን ጨምሮ ለሌሎች ከተሞች አዳዲስ ከመገንባት ጎን ለጎን የቀደሙትን ስታዲየሞች ደረጃ በደረጃ አቅማቸውን እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ፕሮጀክት ነው።
በቀጣይ የማሻሻያ ሥራዎችን ማጠናቀቅ እና የብዙዎች ቅሬታ የሆነው የመጫወቻ ሜዳውን ምቹ የማድረግ ሥሬ ከተሰራ ስታዲየሙ አሁን ካለበት የበለጠ ደረጃ ላይ መገኘት እንደሚችል እሙን ነው።
👉 ‘እኔንም ቀይሩኝ’ የምትለው የተጫዋቾች መቀየርያ
በድሬዳዋ ስታዲየም ግልጋሎት ላይ እየዋለች የምንመለከታት የተጫዋቾች መቀየርያ ከግልጋሎት ብዛት ራሷ ‘ቀይሩኝ’ እያለች ያለች ትመስላለች።
ተለዋዋጭ የቁጥር ማሳያዋ በተለይ በላይኛው ክፍሏ በኩል የተወሰኑ ክፍሎቿ ወላልቀው የምተቶታየው ይህች ቁስ በሚመለከተው አካል ማስተካከያ ሊያደርግባት ይገባል።
ዓለም LED የተጫዋቾች መቀየርያን ተግባራዊ እያደረገ በሚገኝበት በዚህ ዘመን ሀገራችን አሁንም በሰዎች ድጋፍ የሚሰራውን ይህ የተጫዋቾች መቀየርያ በቀጣይ ሊያሻሽል ይገባል።
👉 አነጋጋሪው የአባ ጅፋር አዲስ ተጫዋቾች መለያ
20ኛ የጨዋታ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ጅማ አባ ጅፋርን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘው ጨዋታ ከጨዋታው እና ውጤቱ ጎን ለጎን የጅማ አባ ጅፋር አዳዲስ ተጫዋቾች መለያ ጉዳይ ይበልጡኑ የሚያነጋግር ነበር። አንድ አቻ በተጠናቀቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በውድድር አጋማሹ ጅማ አባ ጅፋርን የተቀላቀሉት አማካዩ ዋለልኝ ገብሬ እና የመስመር አጥቂው ፕሪንስ ሰቨሪን የለበሷቸው መለያዎችን በተለይ በጀርባቸው ላይ የነበረው የልጥፍ ብዛት ለተመለከተ በአንድ በከፍተኛ ደረጃ እግር ኳስን በሚወዳደር ቡድን ይቅርና በሌሎች በደረጃቸው ዝቅ ባሉ ውድድሮች ላይ የሚካፈሉ ቡድኖች እንኳን ሊጠቀሙት በማይችል ደረጃ የወረደ ተግባርን ተመልክተናል።
እነዚሁ ሁለት ተጫዋቾቹ የለበሱትን መለያ በመጀመሪያው ዙር ይለብሱት የነበሩ የቀድሞ ተጫዋቾችን ስም እና የመለያ ቁጥር ለማስተካከል በሚል በርካታ መጠን ያለው ነጭ ፕላስተር ጥቅም ላይ ውሎ ተመልክተናል። በነጭ ፕላስተር ከተሸፈው የመለያ ክፍሎች ላይ ደግሞ በቀይ ማርከር የተጫዋቾቹ ፅሁፍ በእጅ ተፅፎ ተመልክተናል።
ይህ ከሰሀራ በታች በሚገኙ ሀገራት የቀጥታ የቴሌቪዥን ሽፋን በሚያገኝ እንዲሁም በመላው ዓለም ውድድሩ በበይነ መረብ በሚታይበት በዚህ አዲሱ ዘመን የመሆኑ ነገር ቸልተኞቹን የቡድን አመራሮች የሚያስወቅስ ነው። በተጨማሪም ቡድኑ በዕለቱ የተጠቀመበት መለያ ክለቡን የሚገልፅ የተለየ ንድፍ የሌለው እና በቀላሉ ከገበያ መገዛት የሚችል የስፖርት ቲሸርት እንደመሆኑ ቢያንስ ራሱን እንኳን መግዛት ባይቻል ተቀራራቢ አዲስ መለያን ገዝተው መጠቀም እየተቻለ የቡድኑ ኃላፊዎች ይህኛውን መንገድ መምረጣቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው።
በብዙ ሚልየኖች የሚቆጠር ዓመታዊ በጀትን እንዳሻቸው በሚያንቀሳቅሱ ቡድኖች በዚህ ደረጃ ሁለት እና ሦስት ማልያዎችን ለማሰራት የሚሆን ገንዘብ አጥተው ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ የዋህነት ቢሆንም መሰል ቀላል የሚመስሉ ነገርግን በክለብ ገፅታ ላይ ተፅዕኖ ያላቸው ድርጊቶች ላይ ክለቦች ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ጅማ አባ ጅፋርን አነሳን እንጂ በዚህ ደረጃ የጎላ ባይሆንም በወልቂጤ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ማልያዎች ላይም ይህ ችግር ተስተውሏል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የድሬዳዋ ከተማ ተግባር በበጎነት የሚነሳ ነው። ቡድኑ ከቀናት በፊት ከባህርዳር ከተማ ጋር አቻ በተለያየበት ጨዋታ በተጠቀመው ወደ ወርቃማ ቀለም በቀረበው መለያቸው በሁለኛው ዙር ክለቡን የተቀላቀለው ዳንኤል ኃይሉ በመጀመሪያው ዙር ከቡድኑ ጋር ባለመኖሩ የተነሳ በመጀመሪያው ዙር ቡድኑ ከተጠቀመው መለያ ጋር የሚመሳሰልን መለያ በሀገር ውስጥ አስመርተው ጥቅም ላይ ያዋሉበት መንገድ የፕላስተር ልጥፍን ለሚከተሉ በርካታ የሊጉ ክለቦች ትምህርት የሚሆን በጎ ተግባር ነው።
© ሶከር ኢትዮጵያ