ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የነገውን ቀዳሚ ጨዋታ በዳሰሳችን ለመመልከት ሞክረናል።

በሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ የሚገኙት ቡድኖችን የሚያገናኛው ጨዋታ ውጤት ለሁለቱም የተለያየ ትርጉም ይኖረዋል። ለፋሲል ከነማ ከተከታዩ ጋር ያለውን ልዩነት ይበልጥ አስፍቶ በጊዜ ዋንጫውን በእጁ ለማስገባት የሚያደርገው ጥረት ውስጥ የሚከወን ጨዋታ ነው። በተቃራኒው አዳማ ከተማ ቢያንስ ከበላዩ ያለው ጅማ አባ ጅፋር ጋር በነጥብ ለመስተካከል እና ላለመውረድ በሚደርገው ፍልሚያ ውስጥ ተስፋን የሚያልምበት ጨዋታ ይሆናል።

ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት አዳማዎች ከሽንፈት መራቃቸው ከከባዱ ጨዋታ በፊት በሥነ ልቦናው ጠንክረው እንዲቀርቡ የሚያደርጋቸው ጉዳይ ነው። ከነገው ጨዋታ ውጤት ማግኘት መቻል ደግሞ በዚህ ረገድ ለቡድኑ ከውጤትም በላይ ፋይዳ ይኖረዋል። በውድድሩ ከቀሩት ጊዜያት ጋር ሲተያይ አጠያያቂ ቢሆንም ቡድኑ ላይ እየታየ የሚገኘው አንፃራዊ መሻሻልም እንዲሁ ለአዳማ ተስፋ ይሆነዋል። ነገር ግን የነገ ጨዋታ ዕቅዱ ትኩረት ምን ላይ ይሆናል የሚለው ጉዳይ ነገሮችን የሚወስን ይመስላል። እንደ ወልቂጤው ጨዋታ ጥንቃቄ የመረጠ አቀራረብን ይዞ መግባት ከተጋጣሚው ስብስብ ጥራት አንፃር ይበልጥ ጫና ውስጥ ይከተዋል። አጥቅቶ በመጫወት ድፍረት ውስጥ ሆኖ ወደ ሜዳ ከገባም በእንቅስቃሴ ለሚፈጠሩ ክፍተቶች ሁነኛ መፍትሄ ማግኘት ከአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚጠበቅ ይሆናል።

ወረቀት ላይ ሲታይ ጨዋታው ለፋሲል ከነማ ፈታኝ መስሎ ላይታይ ይችላል። ነገር ግን እንደመጀመሪያው ዙር አዳማን ያለብዙ ፈተና ማሸነፍ ቀላል የሚሆን አይመስልም። በዚህም አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ቡድናቸው የዘወትር ትኩረቱ ላይ እንዲገኝ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ባለፈ ከመጀመሪያው ቅፅበት ጀምሮ ከፍ ባለ የማጥቃት ፍላጎት ጨዋታውን መጀመር ከፋሲል ይጠበቃል። ቡድኑ በመጨረሻው የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ብዙ ጉልበት ከማውጣቱም አኳያ ነገ በጊዜ መሪ ሆኖ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያለጫና ለመጨረስ መሞከር የተሻለ ይሆንለታል። ከቀደሙት ጊዜያት አንፃር ቀነስ ብሎ የሚታየው የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች ደጋግሞ የመፍጠር ሂደት ደግሞ በነገው ጨዋታ አፄዎቹ በዋነኝነት ሊያሻሽሉት የሚገባ ነጥብ መሆኑ ይታመናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ተጋጣሚዎቹ እስካሁን በሊጉ በስምንት ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ከእነዚህ መሀል አምስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ፋሲል ከነማ ሁለት አዳማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። ፋሲል 7 አዳማ 3 ግቦችንም አስቆጥረዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ