ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በአዳማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የ2013 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ሲካሄድ ሰንብቶ ዛሬ በማጠቃለያ ጨዋታ አደማ ከተማ አሸናፊ በመሆን ተጠናቋል።

ለወራት በአዳማ ከተማ እና በአሰላ ከተማ በሁለት ምድብ ተከፍሎ አስራ አራት ቡድኖችን አሳትፎ ሲካሄድ የቆየው የ2013 የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በአዳማ ከተማ ማጠቃለያውን አድርጓል። የአዳማ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተወካዮች እና ሌሎች የክብር እንግዶች በታደሙበት ሁለት ጨዋታዎች የመዝግያው መርሐግብር ተካሂዷል።

አስቀድሞ ጠዋት ሦስት ሰዓት ከየምድባቸው ሁለተኛ ሆነው ያጠናቀቁት ኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ያገናኘው ጨዋታ አንድ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ በተሰጠው መለያ ምት ኢትዮጵያ ቡና 5-4 አሸናፊነት ተጠናቋል። ምንም እንኳን ለጎል የቀረቡ ሙከራዎችን እንብዛም በሁለቱም ቡድኖች በኩል መመልከት ባንችልም ጥሩ የእግርኳስ ፉክክር እና በግላቸው የተሻለ አቅም ያላቸው በርከት ያሉ ልጆች ተመልክተናል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የነበራቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች በ15ኛው ደቂቃ የወደፊት ተስፈኛ አጥቂ ከድር ዓሊ የግል ጥረት የታከለበትን ጎል ቡናማዎቹ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ጨዋታውን የተቆጣጠሩ በሚስልም መድኖች 34ኛው ደቂቃ አፀፋዊ ምላሽ በመስጠት በአብዱልከሪም አማካኝነት አቻ መሆን ችለዋል። ከዕረፍት መልስ በሁለቱም በኩል ኳሱን መነካካት በመሀል ሜዳ ላይ ብቻ በመደገደብ ጠንካራ የጎል ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጎዜ በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርተው የኢትዮጵያ ቡናው ግብጠባቂ ዳዊት ባህሩ በአስደናቂ ሁኔታ ባዳናቸው ኳሶች ቡናማዎቹ ውደድሩ ሦስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተገኘውና በውድድሩ ሰባት ጎል በማስቆጥ ወደፊት ጥሩ አጥቂ እንደሚሆን ያስመለከተን ከድር አሊ እና የአስኮ ፕሮጀክት ፍሬ የሆነው አማካይ ሙሴ ከበላ በውድድሩ ያሳዩት አቋም መልካም የሚባል ነበር። ኢትዮጵያ መድን ለታዳጊዎች ቡድን የምሰጠው ትኩረት እንዳለ ሆኖ ከ20 ዓመት በታች ቡድኑ ዘንድሮ አጀማመሩ ቀዝቀዝ ያለ ቢመስልም ከጨዋታ ጨዋታ እየተሻሻለ መጥቶ ውድድሩን በአራተኛ ደረጃ ከማጠናቀቃቸው ባሻገር እንደ ቡድን እንቅስቃሴያቸው መልካም የሚባል ነበር።

ረፋድ አምስት ሰዓት ከየምድባቸው አንደኛ በመሆን ባጠናቀቁት በአዳማ ከተማ እና በሲዳማ ቡና መካከል የተካሄደው ጨዋታ እንደ ጠዋቱ ሁሉ በመደበኛው ጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ መጠናቀቁን ተከትሎ በመለያ ምት አዳማ ከተማ 4-3 አሸናፊ በበመሆን ተጠናቋል። ከጨዋታው አስቀድሞ ሲዳማ ቡናዎች በቅርቡ በአሳዛኝ ሁኔታ ህይወቱ ያለፈውን የሀዋሳ ተስፋ ቡድን ግብጠባቂ የሆነውን በማሰብ ባነር ይዘው ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን በጨዋታው ጅማሬም በህሊና ፀሎት ታስቧል።

በሜዳቸው ጨዋታቸውን እንደማድረጋቸው በርከት ባሉ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው መጫወታቸው በእንቅስቃሴ ብልጫ አወንዲወስዱ የረዳቸው አዳማዎች ሙሉ ለሙሉ ብልጫ በወሰዱባቸው ደቂቃዎች ጎል እና የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በ19 ኛው ደቂቃም በጥሩ ቅብበሎሽ የተቀበለውን ኳስ ፍራኦል ጫላ በድንቅ አጨራረስ አደማን ቀዳሚ የምታደርግ ጎል አስቆጥረዋል። አዳማዎች ጨዋታውን መቆጣጠር እና የበለጠ የጎል መጠናቸውን ማስፋት የሚችሉበትን ዕድል ቢንያም አይተን ፍራኦል ጫላ እና ዮሐንስ ፋንታ አማካኝነት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል። በሒደት ራሳቸውን ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የከተቱት ሲዳማ ቡናዎች እንደ ቡድን በመጫወት ያለቸው አቅም ከፍያ ያለ ቢሆንም የቆሙ ኳሶችን ወደ ጎል ነት ለመቀየር ያደረጉት ጥረት እምብዛም የተሳካ አልነበረም።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች ተቀዛቅዘው ሲቀርቡ በአንፃሩ በከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ወደ ሜዳ የተመለሱት ሲዳማዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ያድጉት ጥረት ጊዜ ወስዶባቸውም ቢሆን 66ኛው ደቂቃ በሲዳማ ቡና የዘንድሮ ዓመት ጉዞ ውስጥ ትልቅ አስተዋፆኦ የነበረው የመስመር አጥቂው የሆነው ፈጣኑ ተጫዋች ዳመነ ደምሴ ሲዳማን አቻ ማድረግ ችሏል። በጨዋታው የነበረው ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር ወደ ኃይል አጨዋወት ተቀይሮ የፍፃሜ ጨዋታውን አደብዝዞት የተለየ ነገር ሳንመለከት መደበኛው ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቆ በተሰጠው የመለያ ምት አዳማ ከተማ 4-3 በማሸነፍ የማጠቃለያ ውድድሩ ቻምፒዮን ሆኗል።

በማስከተል የሽልማት መርሐግብር በዕለቱ እንግዶች አማካኝነት የተበረከተ ሲሆን ከአንድ እስከ ሦስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ ቡና እንደየደረጃቸው የሜዳልያ ተሸላሚ ሲሆኑ የውድድሩ አዘጋጅ ከተማ አዳማ ልዩ የዋንጫ ተሸለሚ ሆናለች። የስፖርታዊ ጨዋነት አሸነፊ ሀድያ ሆሳዕና ሆኗል።

– ኮከብ አሰልጣኝ ተጫዋች ግብጠባቂ እና ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ምርጫ ወደፊት በሚገለፅ ቀን እና ቦታ የሚገለፅ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ