ሁለት ተከታታይ ጨዋታ ቡድናቸውን በሜዳ ተገኝተው ያልመሩት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ስላሳለፉት አስቸጋሪ ጊዜ እና አሁን ስላሉበት ሁኔታ ይናገራሉ።
በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ያለው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ደርሷል። ውድድሩ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በኮቪድ 19 ምክንያት በርከት ያሉ ተግዳሮቶች ተከስተዋል። በተለይ ወረርሽኙ የውድድሩ ወሳኝ አካላቶች ሲፈታተን እና ከእንቅስቃሴ ሲገድባቸው ቆይቷል። በአሰልጣኞች በኩል በአንድ ጨዋታ ቡድናቸውን በሜዳ ተገኝተው ባለመምራት ሦስት አሰልጣኞች ስማቸው ቢጠራም የባህር ዳር ከተማው ዋና አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ደግሞ በኮቪድ ምክንያት ከድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጋር በተደረጉት ጨዋታዎች መገኘት አልቻሉም።
አሰልጣኙ ዛሬ 10:00 ላይ ከሰበታ ከተማ ጋር በሚያደርጉት የድሬዳዋ የመጨረሻ ጨዋታቸው ቡድኑን ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጠዋል። ” የምታሰለጥነውን ቡድን በሜዳ ሳይገኙ መመልከት በጣም ከባድ ነው። ቡድኑ እየተጫወተ ሆቴል ተቀምጦ መመልከት አስቸጋሪ ነው። ጥሩ ያልሆነ ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። ከምክትሎቼ ጋር እንነጋገር ነበር። ቡድኑ መሆን ስለሚገባው ነገር፤ ምን ማድረግ እንዳለብን እየመከርን ቆይተናል። ግን አስጨናቂ ነው። ቦታው ላይ ተገኝቼ ተጫዋቾቼን የቡድኑ አባላት ጓደኞቼን መርዳት ስላልቻልኩ ጥሩ ስሜት ላይ አልነበርኩም። ከባዱን ጊዜ አሳልፌ ዛሬ ቡድኔን እየመራሁ ወደ ሜዳ የምመለስ መሆኑ መልካም ዜና ነው።” ብለዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ