ከ17 ዓመት በታች ውድድሮች በክልሎች እየተደረጉ ይገኛል

በሐምሌ ወር መጀመሪያ በሀዋሳ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ላይ ተሳታፊ የሚሆኑ ክለቦችን ለመለየት ይረዳ ዘንድ በተለያዩ ክልሎች የውስጥ ውድድሮች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከ2006 እስከ 2010 ድረስ ሲካሄድ ቆይቶ አብዛኛዎቹ የየክለቦቹ ተጫዋቾች ተማሪ በመሆናቸው በጉዞ ምክንያት ከትምህርታቸው እንዳይስተጓጎሉ በሚል ምክንያት በየክልሎቹ እንዲደረጉ መመሪያን ቢቀመጥም ተግባራዊ ባለመደረጉ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ተጫዋቾች ከትምህርታቸው ጋር በማይጋጭ ሁኔታ ካጠናቀቁ በኋላ በሀዋሳ ከተማ ለማካሄድ እንደታሰበ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ፍራንኮ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ቴዎድሮስ ገለፃ ፌዴሬሽኑ ለየክልሎቹ በላከው ደብዳቤ የውስጥ ውድድራቸውን እንዲያደርጉ በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ክልሎች ለውድድሩ የሚሆኑ ቡድኖችን በፕሪምየር ሊጉ ይዞ ለመቅረብ ውድድሮቻቸውን ጀምረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ በየክልሎቹ እየተገኙ ውድድሮችን እየተከታተሉ ሲሆን ታዳጊዎችን ለማበረታታት እንደ ፌዴሬሽንም ሆነ በግላቸው ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑን መታዘብ ችለናል፡፡

በደቡብ ክልል በስምንት ክለቦች መካከል በሀላባ ከተማ ሲደረግ የነበረውን ውድድር በዛሬው ዕለት ያጠናቀቀ ሲሆን የሲዳማ ክልልም በተመሳሳይ በትናንትናው ዕለት በስምንት ቡድኖች መካከል በሀዋሳ ውድድሩን ጀምሯል፡፡ የሶማሌ ክልል ባሳለፍነው ሳምንት ሲካሄድ የቆየውን ውድድር ያጠናቀቀ ሲሆን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ የአማራ፣ ጋምቤላ፣ አፋር እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ማካሄድ የሚጀምሩ መሆኑን አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል። በቀጣዮቹ ቀናትም ሌሎች ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ውድድራቸውን እንደሚያካሂዱ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ እግርኳስ ፌዴሬሽንም በተጠናከረ መልኩ ያለፉትን ዓመታት በወጥነት እያወዳደረ እንደሆነ ይታወቃል።

በየክልሎቹ እና ከተማ አስተዳደሮቹ በተካሄዱት ውድድሮች አንደኛ ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በሀምሌ ወር በሀዋሳ በሚደረገው ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆኑ ፌዴሬሽን በነገው ዕለት ከክልል እግርኳስ ፌድሬሽን አመራሮች ጋር የፕሮጀክት ድጎማ ለማድረግ እና ለመወያየት ቀጠሮን ይዟል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ