ኢትዮጵያ ቡና በአራት ተጫዋቾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ አሳለፈ

ኢትዮጵያ ቡና በዲሲፕሊን ጥሰት ምክንያት አራት ተጫዋቾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ አስተላለፈ።

አዲስ ፍስሀ ታፈሰ ሰለሞን ሚኪያስ መኮንን እና ኃይሌ ገብረተንሳይ በክለቡ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅመዋል ተብለው ቅጣት የተላለፈባቸው ተጫዋቾች ሲሆኑ ክለቡ ይፋ ያደረገው መግለጫ ይህንን ይመስላል:-

ክለባችን የኢትዮጵያ ቡና በዘንድሮ ዓመት በሚካሄደው ቤት ኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ስኬታማ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ለውጤቱ መገኘትና ስኬታማ ቆይታ ሁሉም የክለቡ አባላት፣ ባለድርሻዎች፣ ተጨዋቾች፣ አሰልጣኞችና ድጋፍ ሰጪዎች ሁሉ የላቀ ሚና ነበራቸው፡፡ለዚህም ነው ችግር ሳያንገዳግደው፣ መላ እያበጀ፣ መፍትሄ እየሠጠ ከዕለት ዕለት ደጋፊውን እያስደሠተ የዘለቀው፡፡ የክለባችን ትልቁ ዕሴት ችግሮች ሲፈጠሩ በመነጋገር መፍትሄ መስጠት መቻሉ ነው፡፡ መፍትሄው የሚመነጨው ከሁሉም መሆኑ ደግሞ በሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ጥያቄም ሆነ ቅሬታ አያስነሳም፡፡ ጥፋት የፈፀሙ እንኳ መሳሳታቸውን ተገንዝበው ክለባቸውንና ደጋፊያቸውን ለመካስ የሚተጉበት እንጂ ቅራኔና ቁርሾ የሚታይበት አይደለም የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ፡፡ ለዚህ ማሳያ ባለፉት ዓመታት የታዩ እውነታዎች ናቸው፡፡

ዘንድሮም በክለባችን ውስጥ የሚከሰቱ የዲስፕሊን ጥሰቶች በምክርና በተግሳፅ እየታለፉ የነበሩ ቢሆንም አንዳንዶቹን ለሌሎች መማሪያ በሚሆን መልኩ መቅጣት ግን ተገቢ ነው፡፡ በተለይ በኮቪድ ምክንያት ክለቦችም ሆኑ ፕሪሚየር ሊጉ በሚታመስበት በዚህ ወቅት ልዩ ጥንቃቄና ትኩረት ያሻል፡፡ በመሆኑም ከጅማ ጀምሮ በክለባችን ተጨዋቾች ላይ የታዩ የተለያዩ የዲስፕሊን ጥሰቶችን በምክር እየታለፉ ቆይቷል። በሂደቱ የቡድኑ አሰልጣኞች፣ ቡድን መሪ፣ የፅ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም የክለቡ ፊዚቴራፒስት ይስሃቅ ሽፈራው ጭምር ተሳትፈዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በድሬዳዋ ያለው ከፍተኛ የሆነ የኮቪድ ስርጭት ከምንም ጊዜ በላይ ለራስና ለክለቡ ብሎም ለአጠቃላይ ቤተሰቡ መጨነቅና መጠንቀቅ የሚያስፈልግበት ወቅት፤ ይህንን ማድረግ የክለቡን ታላቅነትና ከፍታ ማስጠበቅ ሲገባ ከዚህ በተቃራኒ መቆም ለግልም ለቡድን ያለማሰብ እንደሆ ክለባችን በፅኑ ያምናል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግና በተግሳፅ ትምህርት ለመስጠት ብሎም ተጨዋቾቻን ከችግራቸው እንዲማሩ በማሰብ ሚያዚያ 14/2013 ዓ.ም ድሬዳዋ የክለቡ ተጨዋቾች ከሚያድሩበት ሆቴል በመውጣት ባልተገባ መልኩ አልባሌ ቦታ የተገኙ አራት ተጨዋቾችን ክለቡ የደመወዝ ቅጣትና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሠጥቷል።

በዚህ መሠረት፡-

ታፈሰ ሰለሞን
ሚኪያስ መኮንን
አዲስ ፍስሐ
ኃይሌ ገ/ተንሳይ

የደመወዝ ቅጣትና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ክለቡ ያሳውቃል፡፡ እነዚህ ጨዋቾች ከችግራቸው ወጥተው ክለቡን እንዲጠቅሙ፣ የሚወዱትን ክለብ ስምና ዝና እንዲያስጠብቁና ደጋፊውን በመልካም ስነ-ምግባርና በውጤት እንዲክሱ በማሰብ የተወሰነ ውሳኔ ነው፡፡ በሂደቱም ከላይ እንደተገለፀው የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተሳትፈውበታል፡፡

ስለሆነም በቀሪው የውድድር ጊዜ በተለመደው ጨዋነትና መልካም ስነ-ምግባር ለክለቡ ውጤታማነት ሁሉም የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ እምነታችን የጸና ነው፡፡ለዚህ መሳካት ቦርዱ፣ፅ/ቤቱና ሌሎች አጋሮች ያላሰለሰ ድጋፍና ጥረት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የድሬደዋውን ቆይታ አጠናቀን ሀዋሳ ላይ የሚኖረንን ወሳኝና ስኬታማ ቆይታ ለመጀመር በስነ-ልቦና፣በፋይናስና በሞራል ተገቢውን ዝግጅት ማድረጉን እንቀጥልበታለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ