የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ያለግብ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የቡድኖቹ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት ሀሳባቸውን አካፍለዋል።
አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ካሉሻ አልሀሰንን ቀይረው አስገብተው መልሰው ስለማስወጣታቸው

ስም እና ብቃት ይለያያል ። ሜዳ ላይ ምንም ካልሰራልህ ፣ የተሰጠውን ስራ ካልሰራልህ ምንም ልታደርገው አትችልም። ለእኔ ትልቅ ተጫዋች ነው ፤ ግን ትልቅነቱን ሜዳ ላይ ሲያሳይ ነው። በዚህ ምክንያት ከቡድን ስለማይበልጥ ውሳኔዬ ትክክል ነው።

በቅያሪው የሚፈልጉትን ለውጥ ስለማየታቸው

ጊዜው አጠበረኝ እንጂ እንደሚታወቀው የሀዲያ ቡድን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ለውጦች እናደርጋለን። እሱ ባለቀ ኳስ አጥቂዎችን እንዲያገኝ ነው የምንፈልገው። እሱ ንክኪ አልፈለገም። ጨዋታው ደግሞ የጉልበት ጨዋታ ነው። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ምንም ልታደርገው አትችልም።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ኳሶች ስለመቆራረጣቸው

ሜዳው ለእኛም ለእነሱም እንደልብ ለመጫወት አልተመቸንም። ለማደራጀት ፍፁም የሚታሰብ አይደለም። ያለን አማራጭ ኳሶችን ጥሎ መጫወት ነው ፤ መቆራረጦች ተከስተዋል ጉጉቱም አለ። ምክንያቱም ማሸነፍ ለእኛ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው። ተጋጣሚያችንም የሞት የሽተት ትግል ነው የሚያደርገው ላለመሸነፍ። ከዚህ አኳያ መቆራረጦች በእኛም በእነሱም በኩል ነበሩ።

ስለውጤቱ

ከምንም አንድ ይሻላል። ይቆጨኛል ግን ውድድር ነው እና በፀጋ እቀበላለሁ። ያው እነሱንም እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ።

አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ – ድሬዳዋ ከተማ

ሙኸዲን ሙሳን ስላለመጠቀማቸው

ሜዳው እንደሚታየው ጉበት ይፈልጋል። ሜዳውን ካየሁ በኋላ ነው የወሰንኩት። እሱ ደግሞ ፆመኛ ነው። ስለዚህ ጉልበት ያላቸው ተጫዋቾች ለመጠቀም ሞክሪያለሁ። እንደ አጠቃላይ ቡድናችን የነበረው እንቅስቃሴ ብዙ አያስከፋም። እኛ ጫና ፈጥረን ነበር የምንጫወተው። የዛሬው ጨዋታ ደግሞ ጉልበት ይፈልጋል። እንደዛም ሆኖ ግን ተከላካዮቼ ዛሬ ላሳዩት መስዕዋትነት ሳላደንቃቸው አላልፍም። በተጫዋቼቼ በጣም ደስተኛ ነኝ።

ስለድሬዳዋ ውድድር ቆይታቸው

ስልጀምር አሸንፈናል ስንጨርስም ብናሸነፍ የሚል ዕቅድ ነበረን። እንደ አጠቃላይ የልጆቹ እንቅስቃሴ ግን በጣም ጥሩ ነው። ባህር ዳር ከነበረው ወቅት የተወሰነ ጊዜ ስለነበርም ልምምዶች ለመስራት ሞክረናል። ደረጃ በደረጃ ያለው መሻሻል ጥሩ ነው። በቀጣይ ጨዋታዎች ይህንን አስተካክለን መሄድ ከቻልን የተወሰኑ ተስፋዎች ይታያሉ ብዬ አስባለሁ።

ስለመውረድ ስጋት

በእንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ ያሉትን መሻሻሎች ስናይ የመትረፍ ተስፋ አለን ብለን እናስባለን። ነገር ግን ሁሉም ክለቦች ላለመውሩድ ስለሚጫወቱ ፉክክሩ ከዚህም ከፍ ያለ ነው የሚሆነው። ከዚህም በላይ መሻሻል ያስፈልገናል ሀዋሳ ላይ ባለው ውድድር። እያንዳንዱ ጨዋታ የፍፃሜ እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል። ያቅማችንን እናደርጋለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ