የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 1-2 ሰበታ ከተማ

በ21ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ ሰበታ ከተማዎች ከመመራት ተነስተው ባህር ዳር ከተማን ከረቱበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አብርሃም መብራቱ – ሰበታ ከተማ

በእረፍት ሰአት ወደ መልበሻ ክፍል እያሰበ ስለገባው ጉዳይ

“ወደ መልበሻ ክፍል ስገባ በሁለተኛው አጋማሽ የግድ አጨዋወታችንን መቀየር እንዳለብን እና ውጤቱ ያስፈልገን ስለነበረ ተጭነን መጫወት እንደነበረብን ብቻ ነበር የነገርናቸው። ሁለተኛ ደግሞ በመስመር በኩል ለማጥቃት የነበረን ሙከራ ስላልተሳካልን ናትናኤል ጋንቹላን ከስወጥተን መሀሉን አጠናክረን ወደፊት ለመጫወት ሞክረናል ይህን ነው እረፍት ላይ ተነጋግረን የገባነው ያው እንዳያችሁት ተግባራዊ ሆኖ ውጤት አምጥተን ወጥተናል።”

ሰለተሰጣቸው ፍፁም ቅጣት ምት

“ዳኛው ቅርብ ስለነበር ያ ጥፋት ከሳጥን ውጭ ቢሰራም መነፋቱ የማይቀር ነበር። ስለዚህ ዳኛው ለእንቅስቃሴው ቅርብ ስለነበር የእሱን ውሳኔ አከብራለሁ።”

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ስለቀየረችው ቅፅበት

“መሀል ክፍላችንን ማጠናከራችን እና ለማሸነፍ ቁርጠኛ ሆነን መግባታችን ነበር። ከሁሉም በላይ ደግም እነሱ በመጀመሪያ አጋማሽ ይጠቀሙ የነበሩትን ከጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን መዝጋታችን ውጤታማ አድርጎናል።”

ስለ ዱሬሳ ሹቢሳ

“ዱሬሳ ብዙ ጊዜ ቀይረን ስናስገባው ውጤቱን ለመቀየር ያለው ጥረት ዛሬ ብቻ የታየ አይደለም በተደጋጋሚ ታይቷል። ድሬዳዋ ከመጣን ወዲህ በህመም እስካሁን አልተሰለፈም ነበር። የመሰለፍ እድሉን ሲያገኝ የሚገባውን አድርጎ ውጤቱን ቀይሯል። እንደነዚህ አይነት ታዳጊ ወጣት ተጫዋቾች እድሉ ሲመቻች እያስገቡ መጠቀም የነገዎቹን ተተኪዎች ማዘጋጀት ነው።”

ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ከእረፍት በፊት የነበረው እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር

“በሁለቱም አጋማሾች በፈለግነው መንገድ እየተጫወትን ነበር ብዬ አስባለሁ። ሜዳ ላይ ተጫዋቾች ለማሸነፍ የሚችሉትን በሙሉ አድርገዋል። ጥሩ ታግለዋል በሁለተኛው 45 የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች የነበረን የትኩረት ችግር እነሱ እንዲያጠቁን እና እድሎችን እንዲፈጥሩ አስችሏል። እስከመጨረሻው አጥቅተን ተጫውተን እድሎችን ብንፈጥርም አሸንፈን መውጣት ሳንችል ቀርተናል።በዚህም ተጋጣሚያችንን እንኳን ደስ አላችሁ ልላቸው እፈልጋለሁ።”

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ስለተለወጠበት ቅፅበት

“በመጀመሪያው 10 ደቂቃ የተነጋገርነውን በሙሉ ተግባራዊ አላደረግንም። በእነዛ ደቂቃዎች ተጭነው ወደ እኛ ሜዳ እንደሚመጡ አውቀናል ይህንንም ደጋግመን ተነጋግረንበታል ነገርግን ቀላል የሚመስሉ ስህተቶችን ደጋግመን በመስራታችን ዋጋ ከፍለናል ብዬ አስባለሁ።”

የፍፁም ቅጣት ምቱ ስለተሰጠበት መንገድ አሳማኝነት

” ሁልጊዜም ቢሆን ስለ ዳኛ ማውራት አልፈልግም ፤ ግን ዳኞች ሁልጊዜ ለሁለቱም ቡድኖች እኩል ቢያጫወቱ የተሻለ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።አንደኛው ጋር ፍፁም ቅጣት ምት ከሰጠህ እዛኛውም ጋር ተገቢ ከሆነ መሰጠት አለበት ፤ ግን ዳኞች ሰዎች ናቸው እና እንደ ሰው ይሳሳታሉ።”

ለሁለተኝነት ስላላቸው ተስፋ

“ይህን ቦታ ለመያዝ እስከመጨረሻው እንፋለማለን ፤ ሜዳልያ ውስጥ ሆነን ለመጨረስ የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን።ዛሬም ሜዳ ላይ መጥፎ ቡድን አልነበርንም የምንችለውን ሁሉ አድርገናል አንዳንድ ጊዜ እግርኳስ እንደዚህ ነው እንቀበላለን።”

ፍፁም ዓለሙ ላይ ስለሚፈፀሙ ተደጋጋሚ ጥፋቶች

“በጣም ብዙ ጊዜ ተናግሬያለሁ። እንደ ፍፁም አይነት በክህሎት የታደሉ ተጫዋቾች በዳኞች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል። የተሰራው ጥፋት ግልፅ ነው ፍፁምን ከሜዳ የማስወጣት ሥራ ነው የተሰራው ስለዚህ ይህን እንግዲህ ለሚመለከተው አካል እተዋለሁ።”


© ሶከር ኢትዮጵያ