የሀዲያ ሆሳዕና ጉዳይ ወዴት ያመራ ይሆን ?

ከውድድር ዘመኑ ጅማሮ እስከ መጠናቀቂያው ድረስ እየተንከባለለ እዚህ የደረሰው የሀዲያ የተጫዋቾቹና የክለቡ ውዝግብ ወዴት ያመራ ይሆን ?

በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ አስደናቂ የውድድር ጉዞ በማድረግ አጀማመሩን አሳምሮ የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና ከሜዳ ውጭ በሚፈጠሩ የተጫዋቾቹ ‘የፊርማ ገንዘብ ይከፈለን’ እና ክለቡ ‘ቆይ ታገሱን እንከፍላለን’ ውዝግብ 22 የጨዋታ ሳምንታትን በአሰልቺ ሁኔታ አልፈዋል። ከወራት በፊት ዘዋይ በነበረ ዝግጅታቸው ጠንከር ብሎ የተነሳው የተጫዋቾች ተቃውሞ በሽምግልና እና አንዳንድ ማማለያዎችን በመስጠት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈፀምላቸው ተስፋ በማድረግ ጨዋታ ከሚያደርጉበት አራት ሰዓት በፊት የቡድኑ አባላት ድሬዳዋ መድረሳቸው ይታወቃል።

የድሬዳዋ ቆይታቸውን በአንፃራዊነት በተሻለ ውጤት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ የመጡት ሆሳዕናዎች ማረፊያቸውን ብሉ ስካይ ሆቴል በማድረግ ሲዘጋጁ ቢቆይም ችግሩ አገርሽቶ በዛሬው ዕለት የፊርማው ክፍያ ያልተፈፀመላቸው 15 ተጫዋቾች ‘ ውድድሩን ከጨረስን በኃላ ጥያቄ ብናቀርብ የሚሰማን አካል አናገኝም ‘ በማለት በአንድ ድምፅ ስብሰባ አድርገው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል ወጥተዋል።

በዚህም መሠረት 15 ተጫዋቾች የኮቪድ ምርመራ ዛሬ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ አሻፈረኝ በማለት ሳይመረመሩ ሲቀር 9 ተጫዋቾች ብቻ ምርመራውን አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ባገኘነው መረጃ ካረፉበት ብሉ ስካይ ሆቴል ተበታትነው እንደወጡ ሰምተናል። አሰልጣኝ አሸናፊም በሁኔታው ግራ እንደተጋቡና ያሉትን ቀሪ ዘጠኝ ተጫዋቾችም ቢሆን ነገ ጠዋት ወደ ሀዋሳ ሊያቀኑ እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን የቀሩት ግን ጥያቄው እስካልተመለሰ ድረስ ወደ ሀዋሳ እንደማይጓዙ አቋም ይዘዋል። የክለቡ የበላይ አካል የሆኑት ፕሬዝደንቱ አቶ መላኩ ማደሮ ጋር ስለ ሁኔታው ለመጠየቅ ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለማንሳት ምክንያት ከዚህ ዜና ጋር ማካተት አልቻልንም።

ሀዲያ ሆሳዕና 22ኛ ሳምንት ጨዋታውን የፊታችን ዓርብ ረፋድ አራት ሰዓት ላይ ከሀዋሳ ከተማ ጋር እንዲጫወት መርሐግብር ተይዞለታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ