ጥቂት ነጥቦች ፍፃሜውን ባገኘው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዙርያ

ከቀናት በፊት በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በሁለት ከተሞች ሲካሄድ በነበረውና በአዳማ ከተማ አሸናፊነት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዙርያ በተከታዩ ፅሁፍ የተወሰኑ ነጥቦችን ለማንሳት ወደናል።

አስራ አራት ተሳታፊ ቡድኖች በአዳማ እና አሰላ ከተማ ላለፉት ወራት ሲያደርጉት የቆየው ውድድር በርከት ያሉ ሁነቶችን አስመልክቶን በሳምንቱ መጨረሻ ተጠናቋል። በየምድብ ውድድሮች ብሎም በማጠቃለያው ውድድር የታዘብናቸው ነጥቦችንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

👉በተወሰኑ ከተማዎች የተገደበው ውድድር

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር ከምስረታው አንስቶ የማጠቃለያ ውድድሮቹ እንዲሁም ዘንድሮ በሁለት ከተሞች ተከፍሎ የተደረገው ውድድር በጥቂት ከተሞች ብቻ የተገደበ ይመስላል።

አዳማ፣ አሰላ እና ሀዋሳ ከተሞች ውድድሩን በተደጋጋሚ የማስተናገድ እድሉን ያገኙ ከተሞች ናቸው። ነገርግን ውድድሩ ወደ ሌሎች ከተሞች የሚወጣበት እድል ቢመቻች የታዳጊዎችን እግርኳስ በተለያዩ ከተሞች በማስፋፋት እና ከማነቃቃት አንፃር የሚኖረው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ ውድድሩን በበላይነት የሚመራው አካል ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ ሌሎች አማራጮችን ሊያጤን ይገባዋል።

በተለይ በርካታ እምቅ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ይወጡባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ አካባቢዎች ተለይተው ውድድር ቢካሄድባቸው በበጀት እጥረት ምክንያት ወደሌሎች ከተሞች ተጉዘው ለመጫወት ለሚቸገሩ ወጣት ቡድኖች የመወዳደር እድል ሊሰጥ የሚችል ነው። በተጨማሪም የዋና ቡድን ውድድሮች ላይ በሚካሄዱባቸው ከተሞች ወይም አቅራቢያ አካባቢዎች ማካሄድ ለምልመላ አመቺ ሊሆን ስለሚችል ወደፊት ከግምት ቢገባ መልካም እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን ።

👉 የተጫዋቾች የዕድሜ ተገቢነት ጉዳይ

ውድድሩ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ያለ መቆራረጥ እንዲሁም በተቻለ መጠን ውድድሩን በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተቀመጠው የኮቪድ ፕሮቶኮል መሠረት ለማስኬድ የተደረገው ጥረት ለአዘጋጆቹ አካላት ምስጋና የሚያስቸር ነው። ነገርግን ዘንድሮም እንደወትሮው ሁሉ የተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነት ጉዳይ አሁንም ውድድሩ ሊሻገረው ያልቻለው ተግዳሮት ሆኖ ተመልክተናል።

በሀገራችን እግርኳስ ውስጥ የታዳጊ ቡድኖችን በተመለከት ያለው የተዛባ አረዳድ አሁንም ድረስ ብዙ ችግሮች ያለበት ይመስላል። ቡድኖች የዕድሜ እርከን ቡድኖችን የሚያቋቁሙት መሠረታዊ ግብ መሆን የሚገባው በጊዜ ሒደት በዋናው ቡድን መጫወት የሚችሉ የክለቡን እሴት ጠንቅቀው የተረዱ ተጫዋቾችን ማፍራት መሆኑ ይታመናል። በዚህም ሂደት ክለቦች ለዝውውር እና ደሞዝ የሚወጡ የተጋነኑ ወጪዎችን መቀነስን ጨምሮ ፈርጀ ብዙ ጥቅሞች ማግኘታቸው አይቀሬ ነው።

ነገርግን እንዳለመታደል ሆኖ በእኛ ሀገር እግርኳስ ስልታዊ ውጥኖችን ነድፎ ነገን አሻግሮ በመመልከት ከመንቀሳቀስ ይልቅ የዕለት የዕለቷን ፈተና መወጣት ላይ ብቻ ተጠምደናል። በተለይ በታዳጊዎች እግርኳስ ላይ ያለው እውነታም የዚህ ነፀብራቅ ነው።

ቡድኖች ውድድሩ በሚፈቅደው መልኩ በተቀመጠላቸው የዕድሜ ገደብ ተጫዋቾችን መልምሎ የሚገባቸው ስልጠና እየሰጡ ተጫዋቾቹን ከማጎልበት ይልቅ በውድድሩ አውድ የበቁ ብሎም እድሜያቸው ያለፉ ተጫዋቾችን በመሰብሰብ በውድድሩ ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ ለመቅረብ ስለመሆናቸው በግልፅ የሚያስታውቁ ተጫዋቾችን የተመለከትንበት ውድድር ነበር።

ቡድኖች ከዚህ በአቋራጭ መንገድ ወደ ጊዜያዊ ስኬት ከሚያደርሰው ኃላቀር አካሄድ ወጥተው የነገውን የሀገራችን እግርኳስ ተተኪ ተጫዋቾች በትክክለኛው መንገድ ለማፍራት መታተር ይገባቸዋል። በመሆኑም ተሳታፊ ቡድኖች በቀጣዩ የውድድር ዘመን ይህን ጉዳይ ከወዲሁ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩበት ይገባል።

👉አዲስ ገቢው ሀዲያ ሆሳዕና

በእግርኳሳችን ውስጥ በግልፅ ተለይተው የተቀመጡ እምቅ የእግርኳስ የተሰጥኦ ቀጠናዎች /Potential Talent Areas/ ባይኖሩም በተምዶ የሚጠሩ ከተሞች እና አካባቢዎች ግን አሉ። የዘንድሮው የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ግን ያለመሥራት ጉዳይ እንጂ እምቅ ያላቸው ተጫዋቾች በየአካባቢው እንደሚገኙ ዳግም ያመላከተ ነበር።

ለኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ውድድር አዲስ የሆኑት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አካባቢያቸው እምቅ አቅም ያላቸው ተጫዋቾች ስለመኖራቸው የሚያስመሰክር የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ከማሳየት ባሻገር በመጀመሪያ ተሳትፏቸው በምድባቸው ጠንካራ ፉክክርን አድርገው በሁለተኝነት ለማጠናቀቅ በቅተዋል።

ይህም በሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ እርከን ከፍተኛ በጀትን እየመደቡ ከሌሎች ክለቦች ብቻ በሚዘዋወሩ ተጫዋቾች ህልውናቸው መሠረት ላደረጉት እንደነ ፋሲል ከነማ ፣ ባህር ዳር ከተማ ፣ ጅማ አባ ጅፋር ፣ ወላይታ ድቻ እና ሰበታ ከተማ የመሰሉ ቀሪ የሊጉ ተወዳዳሪ ክለቦች ጥሩ ትምህርት የሚሰጥ አጋጣሚ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የወጣት ቡድን የሌላቸው ከላይ የተጠቀሱት ቡድኖች በሊግ ካምፓኒው እና በክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት አማካኝነት ቡድን እንዲኖራቸው ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለፍ ሲልም ማስገደድ ይገባል።

👉በቸልተኝነት ከውድድሩ የወጡት ቡድኖች

ነገ በትልቅ ደረጃ እግርኳስን የመጫወት ውጥን ሰንቀው በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች አልፈው በተለያዩ ክለቦች ታቅፈው የእግርኳስ ህይወታቸውን ለማቃናት ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት በጥቂት እግርኳስን ጠንቅቀው ባልተረዱ የክለብ አመራሮች የታዳጊዎች ጥረት መና ሲቀር እንደመመልከት ልብ የሚሰብር ጉዳይ የለም።

በዘንድሮው ውድድር በተለይ የአሰላ ህብረት እና ወላይታ ድቻ ጉዳይ ግን ብዙ የሚያነጋግር ነበር። አሰላ ኅብረቶች ለአካባቢው ተስፋ የሚሆኑ ተጫዋቾችን ቢያስመለክቱንም በውድድሩ ብዙም መዝለቅ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ቡድን እግርኳሳዊ ባልሆነ መንገድ በክለቡ አመራሮች ቸልተኝነት ሳቢያ በቀረበ የተሳሳተ የኮቪድ ውጤት መነሻነት በቀጥታ ከውድድሩ ለመሰናበት ተገደዋል። በሌላ በኩል ምድቡን በአንደኛው ዙር አንደኛ በመሆን ያጠናቀቀው እና በሁለተኛው ዙር ውድድሩን በአሸናፊነት ማጠናቀቅ የሚያስችለው ቁመና ላይ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች የፋይናስ እጥረት በሚል አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ከውድድሩ ውጭ የሆኑበት መንገድ የውድድሩ አሳዛኝ ክስቶች ሆነው አልፈዋል።

በሁለቱም ክለቦች ከውድድር መወጣት በስተጀርባ እጅግ ደካማ የሆነ እና ፍፁም እግርኳሳዊ ያልሆኑ ጉዳዮች በምክንያትነት ቢቀርቡም ጉዳዩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ ብዙ ተስፋ አድርገው ውድድሩን እየተካፈሉ የነበሩት ታዳጊዎች ባላወቁት እና ፍፁም ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ከውድድር እንዲወጡ የሆነበት ሒደት ከዕድሜያቸው እንዲሁም ከእግርኳስ ጉዟቸው አንድ ዓመት የተሰረቁት ተጫዋቾች ላይ የሚያደርሰው የስነልቦና ድቀትን ማሰብ ከባድ አይሆንም።

👉ድሬዳዋ ከተማ …

ምንም እንኳን የዚህ ውድድር ተቀዳሚ አላማ ተተኪ እግርኳሰኞችን ማፍራት መሆኑ ቢታመንም በድሬዳዋ ከተማ ደረጃ ግን ፍፁም የወረደ የውድድር ዘመን ያሳለፈ ቡድን ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው።

በቀድሞው ድንቅ ተጫዋች አህመድ ጁንዲ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በውድድሩ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ሳይችል በሁለተኛው ዙር ከውድድሩ ከተገለለው ወላይታ ድቻ ባገኘው የፎርፌ ውጤት ብቻ ውድድሩን መጨረሱ ይታወቃል።

በቀደሙት ዓመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀው አካባቢው አሁን ላይ ብዙ ስራ መስራት እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው።

👉 የአዳማ ከተማ ሁለት ገፅታ

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተካፈለ የሚገኘው አዳማ ከተማ እጅግ ደካማ የውድድር ዓመት አሳልፎ በከፍተኛው የሊግን እርከን የነበረው ቆይታ ሊጠናቀቅ ከጫፍ ደርሷል። በአንፃሩ በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ የነበረው ከ20 ዓመት በታች ቡድናቸው ደግሞ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቋል።

ከዋናው ቡድን በሊጉ ከመቸገር በስተጀርባ በዋነኝነት የሚቀርበው ምክንያት የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የነበሩት እና በቅርብ ዓመታት ከቡድኑ የእድሜ እርከን ቡድኖች ወደ ዋናው ቡድን ያደጉ ተጫዋቾች ወደ ሌሎች ክለቦች መኮብለላቸው እንደሆነ ይታወቃል። ቡድኑም እነሱን ለመተካት የሄዱበት መንገድም ውጤታማ ሳያደርጋቸው ቀርቷል።

እንደነ ቢኒያም አይተን ( ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ በሁለተኛ ግብ አስቆጣሪነት ያጠናቀቀ) ጨምሮ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ወደ ዋናው ቡድን ቢያሳድግም ይህ ነው የሚባል የመሰለፍ እድል ሳያገኙ ቀርተዋል። ቢሆንም ግን ቡድኑ ከሊጉ የመሰናበቱ ነገር የሚቀር ባይመስልም ቡድኑ በቀጣዩ ዓመት ዳግም ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት የ20 ዓመት በታች ቡድኑ ፍሬዎች ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ይመስላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ