ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገው አርባምንጭ ከተማ ሽልማት ተበረከተለት

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ከምድብ ሐ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማደጉን ላረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ ሽልማት ተበረከተለት፡፡

በነቀምት ሲደረግ የነበረው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ሐ ውድድርን አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ወደ 2014 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ማለፉን ያረጋገጠው የአርባምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ትናንት የደቡብ ክልል መቀመጫ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ ሲደርስ በማርሽ ባንድ በታገዘ ደማቅ አቀባበል የተደረገለት ሲሆን አመሻሽ ላይ ደግሞ በሌዊ ሪዞርት የእራት ግብዣ እና የሽልማት ስነ ስርአት ተካሂዷል፡፡

የደቡብ ክልል ብልፅና ፓርቲ ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ የሺዋስ ዓለሙ እና የክልሉ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደመላሽ ይትባረክን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች እና የክለቡ አመራሮች በተገኙበት የምሽቱ ስነስርአት ተካሂዷል፡፡ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ጥላሁን ከበደ የእንኳን ደስ አላችሁ እና የስራ መመሪያን ካስተላለፉ በኃላ ለክለቡ ሽልማት አበርክተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ከደቡብ ክልል የ4 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማትን ለክለቡ ያበረከቱ ሲሆን በቀጣይም ክልሉ ከክለቡ ጎን በማንኛውም ነገር እንደሚሆን ቃል ገብተዋል፡፡ በመቀጠል በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ እና የጋሞ ዞን አስተዳደር በጋራ በመሆን ለክለቡ ተጫዋቾች የቤት መስሪያ ቦታ እና ለግንባታ የሚውል የቁጠባ ገንዘብ 2.6 ሚሊዮን ብር ለመክፈል ቃል የገባ ሲሆን የአርባምንጭ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው ተጨማሪ ለእያንዳንዱ ተጫዋቾች የ300 መቶ ሺህ ብር የገንዘብ ስጦታን አበርክተዋል፡፡ በሌላ ሽልማት ከክለቡ ወዳዶች እና ደጋፊዎች የተሰበሰበ 345 ሺህ ተጨማሪ የገንዘብ ሽልማት ለቡድኑ አባላት ተሰጥቷል፡፡ በመጨረሻም የኬክ ቆረሳ እና የእራት ግብዣ ከተደረገ በኃላ ፕሮግራሙ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡

ከፕሮግራሙ ጋር በተያያዘ የደቡብ ክልል ለቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ የክልሉ ቡድኖች ወልቂጤ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ሀዲያ ሆሳዕና ለእያንዳንዳቸው የሁለት ሚሊዮን ብር የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ