የአሰልጣኞች አስተያየት | ጅማ አባ ጅፋር 0-0 ኢትዮጵያ ቡና

የድሬዳዋ ስታድየም የመጨረሻ ጨዋታ ያለግብ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – ጅማ አባ ጅፋር

ስለ ጨዋታው

በመጀመሪያው 15 ደቂቃ ሦስት የግብ ዕድሎች አግኝተናል። ከዛ በኋላ በነበረው እንቅስቃሴ ግን ትልቁ ነገር የቡና ጠንካራ ጎን አለ። እኛም የራሳችንን ፈጣን የማጥቃት ሥራዎች አስበን ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ነገር ግን ሜዳው በተለይም መሀል ሜዳ ላይ ኳሱን ተቆጣጥረን ለማጥቃት ተቸግረናል። አጥቂዎቻችንን መውቀስ አንችልም፤ ወደ ጎል ለመሄድ ከመሀል ሜዳ የሚዘጋጁ ኳሶች በጣም ወሳኝነት አላቸው። መሀል ሜዳ ላይ በሁለት እና ሦስት ሜትሮች መቀባበል የማትችልበት ሜዳ ስለነበር በዚህ በኩል ሁለታችንም ተቸግረናል። ተጋጣሚያችን ኢትዮጵያ ቡና በጣም ጠንካራ ነው። ኳሱን አቅልለው በሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚያጠቃ ቡድን ነው እና ውጤት ቀያሪ ተጫዋቾችም አሏቸው። በህብረት የሚያጠቃ ቡድን ነው። ሳጥን ውስጥም ብዙ ተጫዋቾች ይገባሉ። እኛም ብንሆን ታክቲካሊ ጥሩ ነበርን። በተለይም ኳስ ስናጣ ታክቱካሉ ዲስፕሊንድ የሆነ ቡድን ነበረን። በአጠቃላይ ግን በዚህ ሜዳ ላይ ውጤት መጠበቅ ራሱ ከባድ ነበር ብዬ ነው የማስበው።

ስለ ውጤቱ

አንድ ነጥብ ሊጠቅመን ይችላል። ዞሮ ዞሮ ቡድናችን ያለበት ሂደት እንዴት ነው ?ቡድናችን እየተሰራ ያለው ድሬዳዋ ከመጣን ወዲህ ነው ማለት እችላለሁ። የጣልናቸው ውጤቶች በጣም የሚያስቆጩ ነበሩ። እንደቡድን እየተሻሻለ ነው ወይ ፣ ተጫዋቾቻን እየተናበቡ ነው ወይ ? በሚለው ግን የቡድኑን ለውጥ እያየሁ ነው። እንጂ በጣም አጥጋቢ ነው ውጤታማ ነው ማለት ያስቸግረኛል። ሜዳ ላይ ያለው የተጫዋቾች መነሳሳት ግን ጥሩ ነበር እና በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና

ስለመጫወቻ ሜዳው

የቻልነውን ያህል የምንፈልገውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረናል። ሜዳው ግን በጣም በጣም አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ሜዳ ላይ ከዚህ በላይ መጠበቅ ከባድ ነው። ማድረግ የምንፈልጋቸው ነገሮች አሉ። የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ የሜዳው ደህና የሚባለው ክፍል በኩል ኳሱን እያስኬድን እንድንጫወት ነበር ያሰብነው። ያንን በተቻለ መጠን ለማድረግ ሞክረዋል። ግን ደግሞ በሜዳው ምክንያት ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የምንፈልገውን ነገር ሁለታችንም ማድረግ የቻልን አይመስለኝም።

አቡበከር ክፍተት ስላለማግኘቱ

ሁልጊዜ ይህንን ከግምት ውስጥ እንከታለን። አቡበከር ጎል እየመራ ነው ፣ ጥሩ አቅም ያለው ተጫዋች ነው። ስለዚህ እሱ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ እናውቃለን። ስለዚህ ሌሌች ተጫዋቾቻችን ያንን ታሳቢ አድርገው ማድረግ ያለባቸውን ተነጋግረናል። አንዴንዴ በእኛም ተጫዋቾች በከል እሱ ላይ የማተኮር ነገር አለ። ከዛ መውጣት አለባቸው። ሌሎች ተጨማሪ ተጫዋቾች የሚመጡ ከሆነ የተቃራኒ ቡድን ግዴታ እሱን ለመልቀቅ ይገደዳል። እና ያንን ለተጫዋቾቻችን ደጋግመን እያሳሰብን ያለነው ነገር ነው። ምናልባት ይሄ በቀሪዎቹ ግጥሚያዎችም ሊቀጥል ይችላል ብዬ አስባለሁ።

ለፋሲል ቻምፒዮንነት ዕድል ስለመስጠታቸው

ያው ፋሲልም ሌላው በድንም በራሱ ነው የሚፈልገውን ነገር እያሳካ መሄድ ያለበት። ግን የጨዋታው ባህሪ ሆኖ ሌላ ቡድን በሚጥለው ነጥብ ተጠቃሚ የምትሆንባቸው ዕድሎች አሉ። ለእነሱ የሚከተሏቸው ቡድኖች ነጥብ መጣል ወደ ዋንጫው ለመቅረብ ይሄ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ።

ስለድሬዳዋ ቆይታቸው

ድሬዳዋ ጥሩ ነው። ሕዝቡ እንግዳ ተቀባይ ነው። ያረፍንበትም ሆቴል በጣም ተስማምቶናል፤ ጥሩ ሰዎች ናቸው። ሌላው ሙቀቱ ከባድ ነው። ልምምዳችንን እናደርግ የነበረው ብዙ ጊዜ ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ነው። ምክንያቱም ሙቀቱ ከባድ ነው፤ ብዙ ላብ ነው የምታፈሰው። ውድድሩም ያ ታስቢ ተደርጎ ይመስለኛል ወደ አስር እና አንድ ሰዓት የተደረግው፤ ያ ጥሩ ነው። ተጫዋቼ እንደልብ መንቀሳቀስ እንዲችሉ ቢያንስ በጥሩ አየር መጫወቱ ጥሩ ነው። ያ ታሳቢ መደረጉ ጥሩ ነው። ሌላው ሜዳው ዕውነት ለመናገር የልምምድ ሜዳዎቹ የአርቴፉሻል ሜዳዎች አሉ፤ እነሱ ደህና ናቸው። ሌሎቹ ግን የልምምድም የግጥሚያ ሜዳውም ግን የሚመለከተው አካል ሊያስብባት ይገባል ብዬ አስባለሁ።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ