ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 21ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በመጨረሻው ትኩረታችን ሌሎች መዳሰስ የሚገባቸው ነጥቦችን ያሰናዳንበት የመጨረሻውን ፅሁፋችንን እነሆ።

👉የድሬዳዋ ቆይታ ሲጠቃለል

ላለፉት ስድስት የጨዋታ ሳምንታት በድሬዳዋ ሲካሄድ የነበረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ምዕራፍ ተጠናቋል። በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ የተለየ መልክ በነበረው ውድድሮች ከተወሰኑ የሚጠበቁ ክፍተቶች ውጭ ውጤታማ መሰናዶ ነበር ብሎ መግለፅ ይቻላል።

የከተማዋና ሞቃታማ የአየር ፀባይን ምክንያት በማድረግ ከሌሎች ከተሞች በተለየ የተጫዋቾችን ውጤታማነትን ለመጨመር በማሰብ ጨዋታዎች ከተለምዶው የአራት እና ዘጠኝ ሰዓት በተለየ ከሰዓት በአስር እና ምሽት አንድ ሰዓት እንዲደረጉ የተደረገበት ውሳኔ በትልቅነት ከድሬዳዋው ውድድር የሚወሳ ጉዳይ ሆኖ አልፏል።

ሌላኛው የሊጉ የድሬዳዋ ቆይታ ከእስካሁኖቹ ውድድሮች በኮቪድ ክፉኛ የተደቆሰው ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። በቁጥር ውስን የነበሩትን ደጋፊዎችን በማገድ ጅማሮውን ያደረገው ውድድር አሰልጣኞች በቫይረሱ በመያዛቸው ቡድናቸውን ያልመሩበት፣ ወደ ግማሽ ደርዘን የተጠጉ ተጫዋቾች በቫይረሱ የተያዙበት ብሎም በቁጥር በርከት ያሉ የጨዋታ ዳኞች እንዲሁ በቫይረሱ የተጠቁበት ነበር። በዚህም የተወሰኑ ዳኞች በተከታታይ ቀናት በመስመር ዳኝነት እና በመሀል ዳኝነት ያጫወቱበት፣ ቡድን መሪ ቡድን እየመራ ወደ ጨዋታ የገባበት እንዲሁም ሁለት ግብጠባቂዎች በሜዳ ላይ ተጫዋችነት ሁሉ ሲጫወቱ የተመለከትንበት ቆይታ ነበር።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላው የሚነሳው የኮቪድ ምርመራ ውጤት ጉዳይ ነው። የድሬዳዋ ህብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት እና በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የምርመራ ውጤቶች መካከል የነበረው የውጤቶች ልዩነት ሌላው መነጋገርያ የነበረ ጉዳይ ነበር።

በጥቅሉ ከልምምድ ሜዳ አመቺነት እና የድሬዳዋ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ በተለይ ዝናብ ከጣለ በኃላ የነበረው ፍፁም አመቺ ያልነበሩ ሁኔታዎች ከፈጠሩት የተወሰነ አሉታዊ ርዕሰ ዜና ውጭ ድሬዳዋ የተጣለባትን የማስተናገድ ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥታለች ብሎ መውሰድ ይቻላል።

👉 ወቅታዊ የአየር ሁኔታ እና ቀጣይ የሊግ መርሐግብሮች

በሀገሪቷ የተለያዩ ክፍሎች ሰሞኑን ከበድ ያለ ደመናማ የአየር ንብረት ብሎም የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ እየተስዋለ ይገኛል። በተጨማሪም እንደ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ትንበያ ከሆነ በቀጣዮቹ ቀናት በደቡብ ምዕራብና የደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለዉ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ታድያ በዚህ ሒደት ውስጥ ደካማ የፍሳሽ አወጋገድ ባላቸው ስታዲየሞቻችን መነሻነት ውድድሮችን ለማካሄድ ምን ያህል ፈታኝ እየሆኑ መጥተዋል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የማስተናገድ ተራዋተ ባበቃው የድሬዳዋ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች ከሰሞነኛ ዝናብ ጋር በተያያዘ ጨዋታዎች እጅግ ፈታኝ በሆነ ጭቃማ ሜዳ ላይ ሲደረጉ ተስተውሏል። በቀጣይ የማስተናገዱን ኃላፊነት የሚረከበው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምም በሊግ ካምፓኒው ሰዎች ከሰሞኑ በተጎበኘበት ወቅትም አንዳንድ የሜዳው ክፍሎች ላይ ውሃ የማስተኛት አዝማሚያ ስላለ በአፋጣኝ እንዲስተካከሉ አቅጣጫ መሰጠቱ ይታወቃል።

በመሆኑም ዝናቡ በዚሁ አያያዙ በቀጣዮችም ቀናት የሚቀጥል ከሆነ ላለመውረድ እና በሁለተኝነት ለማጠናቀቅ በሚደረጉት እና በጉጉት በሚጠበቁት ጨዋታዎችን ለቡድኖች ፈታኝ ከማድረጉም ባለፈ በጨዋታ ቀናት መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ቡድኖች ተጫዋቾቻቸውን በምን መልኩ ድካም ሳያዝላቸው በሚፈልጉት መልኩ አዲስ እና ብርቱ አድርገው ሊጠቀሙባቸው ይችላል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉51 ጥፋቶች የተመዘገቡበት ጨዋታ

ባህር ዳር ከተማ ከሰበታ ከተማ ያገናኘው የ21ኛ ሳምንት የመክፈቻ ጨዋታ ጭቃማ በነበረው ሜዳ ላይ የተከወነው ጨዋታ 51 ጥፋቶች ሰሲመዘገቡበት የሰበታው አዲሱ ተስፋዬም በቀይ ካርድ (ሁለት ቢጫ) ከሜዳ የወጣበት ሆኖ አልፏል። ይህም በሊጉ እስካሁን ከተደረጉ ጨዋታዎች በርካታ ጥፋቶች የተፈፀሙበት ሆኗል።

ከሜዳው ጭቃማነት መነሻነት በርካታ ቅብብሎች በሜዳው ያለመመቸት ለታለመላቸው አላማ ሳይውሉ የሚቀሩበት ሒደት ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ጥፋቶች እንዲሰሩ በአይነተኛ ምክንያትነት ቢቀርብም በሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች ላይ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ይስተዋል የነበረው ስሜታዊነትም አብሮ ሊነሳ የሚገባ ጉዳይ ነበር።

👉ከሊግ ኮሚቴው በስተጀርባ የማይታየው ግለሰብ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካሳለፍነው የተሰረዘው የውድድር ዘመን አንስቶ በክለቦች በተቋቋመ የአክሲዮን ማህበር መተዳደር ከጀመረ ወዲህ በርካታ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል። ከዚህ ቀደም የነበሩ ተደጋጋሚ ቅሬታ ይነሳባቸው የነበሩ የመርሃግብር አወጣጥ፣ የውድድር መቆራረጥ፣ የውድድሩ መጀመሪያ ወቅት አስቀድሞ አለመታወቅ እና መሰል ወቀሳዎች አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉ በሚባል በመልኩ በግልፅ የሚታዩ መሻሻሎችን እየተመለከትን እንገኛለን።

ውድድሩን ወደ ላቀ ከፍታ ለመውሰድ እየተጋ ከሚገኘው የሊግ ካምፓኒው ጀርባ ብዙም ምስጋና እየተቸረው የማይገኝን አንድ ግለሰብን ልናስተዋውቃችሁ ወደድን። ቅደማቸው ፀሐይ ይሰኛል፤ የሊግ ኮምፓኒው የአይቲ ባለሙያ ነው።

ከቀደሙት ዓመታት በተሻለ በፍጥነት እና ጥራት ለቡድኖች ከሚደርሱት ኮሚኒኬዎች፣ ለመገናኛ ብዙሀን አካላት ከጨዋታ ሳምንቱ መጠናቀቅ በኃላ በፍጥነት ከሚደርሱ የዲሲፕሊን እና ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ኃላ ቀር የነበረውን እና የተጫዋቾች ስም እና የቴሴራ ቁጥር ብቻ ከሰፈረበት እና በጨዋታ ዕለት ለመገናኛ ብዙሀን አካላት ይደርስ የነበረውን የተጫዋቾች ዝርዝር መግለጫን በጣም በተሻሻለ እና ሁሉን አቀፍ መረጃን ከስዕላዊ መግለጫ ጋር ካካተው አዲሱ የተጫዋቾች ዝርዝር ማሳወቂያ ጀርባ የሚገኘው ቁልፍ ሰው እሱ ነው።

ኃላ ቀር የመረጃ አያያዝን በማዘመንና እና አጠቃላይ አስራሩን ዘመናዊ ለማድረግ በሚደረጉ ተቋማዊ ሥራዎች ውስጥ እንደ ቅደማቸው ፀሐይ ያሉ ግለሰቦች ባልተደራጀ የሰው ኃይል እና ግብዓት ለሚሰሩት ተስፋ ሰጪ ተግባር አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል።



👉በአንድ ጨዋታ ሁለት መለያ

በሊጉ በመለያዎች ረገድ በድሬዳዋ ከተማ ደረጃ አማራጮችን ያበዛ ቡድን የለም። ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በጭቃማው ሜዳ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ባደረገው ጨዋታ የተለየ ነገርን አስመልክቶናል።

ጭቃማ በነበረው ሜዳ በቅድሚያ አዲሱን ነጭ በብርቱካናማ ዳማ መለያ የለበሰው ቡድኑ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ተጫዋቾቹ በጭቃ የተለወሰውን መለያ አውልቀው በሌላኛው ወደ ወርቃማ ቀለም የሚያደላ መለያ ለብሰው የተመለከትንበት ሳምንት ነበር።

👉 የቀድሞው አሰልጣኝ በተንታኝነት

በዚህ የውድድር ዘመን ድሬዳዋ ከተማን ሲያሰለጥኑ ቆይተው አጋማሽ ላይ ከክለቡ ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ ፍስሐ ጥዑመልሳን ውድድሩ በድሬዳዋ መካሄዱን ተከትሎ ጨዋታዎችን በስታዲየም ተገኝተው ሲከታተሉ ተስተውለዋል።

ከጨዋታ በፊት በኋላ በሚሰጧቸው አስተያየቶች የብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰብ ትኩረት ስበው የነበሩት አሰልጣኝ በዚህ ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና ባደረጉት ጨዋታ ላይ በተንታኝነት ብቅ ብለው ታይተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ