እግድ ላይ የነበሩት አራቱ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች ውሳኔ ተላልፎባቸዋል

ከቀናት በፊት አራት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ያገደው የ27 ጊዜ የሊግ ሻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾቹ ላይ አዲስ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ከአምስት ቀናት በፊት የዲሲፕሊን ግድፈት ፈፅመዋል ያላቸውን ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን ከክለቡ በጊዜያዊነት እንዲታገዱ አድርጎ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ መወሰኑ ይታወሳል። በትላንትናው ዕለት ይህንን ጉዳይ ሲመለከት የነበረው የክለቡ የስራ አመራር ቦርድም ተጫዋቾቹ ላይ አዲስ ውሳኔ ማሳለፉት የክለቡ ሊቀ-መንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል በክለቡ ልሳን በሆነው የምን ጊዜም ጊዮርጊስ የሬድዮ ፕሮግራም ገልፀዋል።

አቶ አብነት የክለቡ ቦርድ ትናንት (ሚያዚያ 19) ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባም በተጫዋቾቹ የተፃፈውን ደብዳቤ፣ በሲሲ ቲቪ የተቀረፀውን ምስል እንዲሁም የክለቡ የልብ ደጋፊዎች የላኩትን አስተማማኝ ማስረጃዎች ከተመለከተ በኋላ የክለቡን ስም፣ ክብር እና ዝና ለማስጠበቅ እንዲሁም የቀሪ ተጫዋቾችን ሰላም ለማረጋጋት እና በክለቡ የወጣውን የዲሲፕሊን መመሪያ ለማስከበር ይቻል ዘንድ ተጫዋቾቹ ላይ ሁለት ውሳኔዎች መወሰናቸው አስረድተዋል። በዚህም አራቱም ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 20 ሺ ብር እንዲቀጡ እና ተጫዋቾቹ ከክለቡ ጋር ያላቸው ስምምነት እስኪጠናቀቅ ድረስ ታግደው እንዲቆዩ ተወስኗል።

የክለቡ ሊቀ-መንበር ጨምረውም ፊልሞች እና ፎቶግራፎች የላኩ ደጋፊዎችን አመስግነዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ