የአሠልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 2-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በወላይታ ድቻ አሸናፊነት ከተገባደደው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ለሱፐር ስፖርት ሰጥተዋል።

ዳዊት ሀብታሙ (ምክትል አሠልጣኝ) – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው እንቅስቃሴ?

አስበን የነበረውን ነገር ከሞላ ጎደል አሳክተናል። ያሰብነውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ እንዳናሳካ እና የሀሳብ ለውጥ እንዲኖር ያደረገን የሜዳው መጨቅየት ነው። የሜዳውንም ገፅታ አይተን ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ጎል ደርሰናል። አጥቂዎቻችንም ቦታ አያያዛቸው እና እይታቸው ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ እንደ ሜዳው ባህሪ ተጫውተናል።

ስለ ስንታየሁ መንግሥቱ ብቃት?

ስንታየሁ ወጣት እና ገና እየመጣ ያለ ተጫዋች ነው። ወደፊትም ለሀገር የሚጠቅም ተጫዋች ነው። እንደታየው በድሬዳዋ በነበሩን ጨዋታዎች ከጓደኞቹ ጋር በመሆን እና በግል ጥረቱ ጎል እያስቆጠረ ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ እየረዳ ነው። ከዚህም በላይ ግን የተሻለ ደረጃ ደርሶ ሀገር መጥቀም የሚችል ተጫዋች ነው።

ቡድኑ በድሬዳዋ ስለነበረው ቆይታ?

ለድሬዳዋው ውድድር የተለየ ዝግጅት አላደረግንም። ባህር ዳር ላይ የነበረን ጥሩ ስኬት እንዳናስቀጥል እዚህ ስንመጣ የኮቪድ ችግሮች ነበሩብን። ይህንንም ተከትሎ ጨዋታዎችን ስንሸነፍ ነበር። ዛሬ ግን አሸንፈን ከድሬዳዋ መውጣት እንዳለብን ተነጋግረን ገብተን ነበር። ይህም ተሳክቶልን አሸንፈናል። በአጠቃላይ ተጫዋቾቻችን ለፍተው ፍፃሜያችን እንዲያምር አድርገዋል። በዚህም ደግሞ ደስተኞች ነን።

ፍራንክ ናታል – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በጊዜ ግብ ስለማስተናገዳቸው?

ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ ነበር የጀመርነው። ነገርግን ግብ አስተናገድን። ግብ ካስተናገድን በኋላም ትንሽ ከበድ ብሎን ነበር። ይህ ቢሆንም ግን የማሸነፍ ፍላጎታችን አልጠፋም ነበር። ወደ ጨዋታውም ለመመለስ ጥረት አድርገን ነበር።

የፍፁም ቅጣት ምት ስላለመሰጠቱ?

ስለዚህ ጉዳይ ምንም ማለት አልፈልግም።

ስለ ሜዳው ጭቃማነት?

ይህ ለሁለቱም ቡድኖች ይሰራል። በዛሬውም ጨዋታ የነበረው የአየር ሁኔታ ሜዳው ለሁለታችንም ቡድኖች አመቺ እንዳይሆን አድርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ