ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በሊጉ ለመቆየት እየታተሩ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመሳተፍ እየተፋለሙ ከሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የሚያደርጉትን የነገ ከሰዓት ጨዋታ እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ድል ያገኙት ሲዳማ ቡናዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ነጥብ ጥለዋል። ቡድኑም በሊጉ የሚያቆየውን ውጤት ለማስመዝገብ እና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በነገው ጨዋታ ሦስት ነጥብን እያሰበ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታም። ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ዳግም የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በበኩላቸው ያገኙትን የአሸናፊነት መንፈስ ለማስቀጠል እና 2ኛ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ ድልን እያሰላሰሉ ለጨዋታው እንደሚቀርቡ ይታሰባል።

ድሬዳዋ ላይ በነበረው ቆይታ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ እጅግ ተሻሽሎ የታየው የአሠልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ቡድን በቀጣይ ዓመት በሊጉ ለመቆየት እያንዳንዱን ጨዋታዎች እንደ ፍፃሜ በመቁጠር መቅረብ ይኖርበታል። እርግጥ ቡድኑ ነገ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከገጠመ በኋላ በአንፃራዊነት በሊጉ ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ የሚገኙትን ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻን እንዲሁም እንደ ራሱ ላለመውረድ እየተፍጨረጨረ የሚገኘውን ጅማ አባጅፋርን መግጠሙ ሲታሰብ ፈተናው እንደሚከብድበት ይገመታል። ነገርግን በድሬዳዋ ቡድኑ ላይ ከታየው መነቃቃት አንፃር ነገሮች በአዎንራዊ መንገድ ሊሄዱለት እንደሚችሉ ይገመታል።

በሀዋሳ ያለውን ቆይታ በአቻ ውጤት የጀመረው ሲዳማ ቡና በሰበታው ጨዋታ የማጥቃት እንቅስቃሴው ተገማች ሆኖ ታይቷል። በተለይ ደግሞ በተደጋጋሚ በኦኪኪ አፎላቢ እና ማማዱ ሲዲቤ ጥምረት ላይ የተንጠለጠለ የማጥቃት እንቅስቃሴው ለተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮች ቀላል ሆኖ ነበር። በነገው ጨዋታ ላይም ተጫዋቾቹ የትኩረት መሐከል ሊሆኑ ስለሚችሉ ሌሎች የቡድኑ ተጫዋቾች የማጥቂያ አማራጭ ሊሆኑ ይገባል። ከዚህ ውጪ በሊጉ ጅማሮ ላይ ጎል የማስተናገድ አባዜ ይዞት የነበረው የተከላካይ ክፍሉ መሻሻል ለጊዮርጊስ ተጫዋቾች ፈተናን ሊሰጥ እንደሚችል ይታሰባል።

በቀጣይ ዓመት ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመሳተፍ እየጣረ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በደረጃ ሰንጠረዡ ቀጥተኛ ተፎካካሪው የሆነው ባህር ዳር ከተማን አሸንፎ ለነገው ጨዋታ ይቀርባል። ወጣ ገባ አቋም የሚያሳየው የፍራንክ ናታል ቡድንም በባህር ዳሩ ጨዋታ ወደ አሸናፊነት መመለሱ በነገው ጨዋታ ጥሩ ስንቅ ሊሆነው ይችላል። ከምንም በላይ ደግሞ ቡድኑ ከ7 ጨዋታዎች በኋላ ሁለት እና ከዛ በላይ ጎሎችን ያስቆጠረበትን ሁነት መፍጠሩ መልካም ነው። እርግጥ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቹ አሁንም በወጥነት ጎሎችን ባያስቆጥሩም የአማካይ እና የተከላካይ መስመር ተጫዋቾቹ እንደ ባህር ዳሩ ጨዋታ ሌላ የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ ሆነው መቅረባቸው ጥሩ ነው።

ፈረሰኞቹ የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎን ማግኘት የሚሹ ከሆነ የነገውን ጨምሮ በቀጣይ የሚያደርጉትን አራት ጨዋታዎች ማሸነፍ የግድ ይላቸዋል። እርግጥ ቡድኑ 2ኛ ደረጃን ለመያዝ የራሱን ውጤት ብቻ ባይጠብቅም በቀጣይ የሚገጥማቸው ቡድኖች ወይ ላለመውረድ (አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ) አልያም ቡድኑ የሚያስበውን ደረጃ ለመያዝ የሚፎካከር (ሀዲያ ሆሳዕና) መሆኑ ሲታሰብ ለእያንዳንዱ ጨዋታ በጥሩ ሁኔታ መቅረብ እንደሚጠበቅበት ያሳብቃል። ከምንም በላይ ደግሞ ከቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ጌታነህ ከበደ (አሁን በእግድ ላይ ነው ያለው) በመቀጠል ለቡድኑ በርከት ያሉ ግቦችን በወጥነት የሚያስቆጥር ተጫዋች አለመኖሩ ቡድኑን ሊጎዳ ይችላል። ይህ ጉዳይም ከጨዋታ ጨዋታ የኋላ መስመሩን እያሻሻለ በሚገኘው ሲዳማ ቡና የኋላ መስመር ይበልጥ እንዳይጋለጥ ያሰጋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 21 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 14 ጊዜ በማሸነፍ ሰፊ የበላይነት ያለው ሲሆን ሲዳማ ቡና አንድ ጊዜ ብቻ አሸንፏል። በቀሪዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል።

– በግንኙነቶቹም ቅዱስ ጊዮርጊስ 30 ኳሶችን ከመረብ ሲያሳርፍ ሲዳማ ቡና ደግሞ 8 ጎል አስቆጥሯል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ