ሪፖርት | ቀዝቃዛው ጨዋታ ያለግብ ተቋጭቷል

ምሽቱን በጅማ አባ ጅፋር እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የተደረገው ጨዋታ 0-0 ተጠናቋል።

ጅማ አባ ጅፋር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ላይ ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል። ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ከሸገር ደርቢ አንፃር ተክለማርያም ሻንቆን በአቤል ማሞ ፣ ኃይሌ ገብረትንሳይን በየአብቃል ፈረጃ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በዊሊያም ሰለሞን እንዲሁም አማኑኤል ዮሃንስን በታፈሰ ሰለሞን በመለወጥ ጨዋታውን ጀምሯል።

ዝግ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት ቀዳሚው አጋማሽ በጥቂት የግብ ዕድሎች ብቻ የታጀበም ነበር። በተለመደው አጨዋወታቸው ኳስ መስርተው ለመውጣት ጥረት ያደርጉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው ብቻ ሳይሆን ከሜዳውም ጭምር የገጠማቸው ፈተና ከብዷቸው ታይተዋል። ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ ወደ ግብ የደረሳባቸው ቅፅበቶችም በቁጥር ሁለት ብቻ ነበሩ። 9ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተነሳ እና በጅማ የመከላከል ግንብ የተደረበን ኳስ አቡበከር ናስር ለሚኪያስ መኮንን አድርሶት ሚኪያስ ቢሞክርም አቡበከር ኑሪ የጨዋታው መጀመሪያ ካሱን አድኗል። 32ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል አቡበከር እና አማኑኤል ዮሃንስ ሳጥን ውስጥ የተገኙበት አጋጣሚም እንዲሁ ለወጣቱ ግብ ጠባቂ ፈታኝ ሳይሆን ቀርቷል። በአጋማሹ የቡናዎች ቅብብል መሀል ሜዳ ላይ የሚበላሹባቸው አጋጣሚዎች ደጋግመው ቢታዩም ቡድኑ በጅማ ሳይቀጣ መቅረቱ ግን ዕድለኛ ያደርገዋል።

በጨዋታው ብልጫ ባይወስዱም ጅማ አባ ጅፋሮች ያለቀላቸውን ዕድሎች በማግኘት ከቡና ተሽለው ታይተዋል። በተለይም ዋለልኝ ገብሬ በ11ኛው ደቂቃ ለተመስገን ደረሰ ከግራ መስመር ተሻጋሪ ኳስ 25ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ለራሂም ኤስማኖ የመጨረሻ የግብ ዕድሎች ፈጥሮ አጥቂዎቹ ስተዋቸዋል። በተለይም የኦስማኑ ሙከራ የግቡን አግዳሚ ታካ የወጣች ነበረች። አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተቃረበባቸው ደቂቃዎች ጅማዎች ይበልጥ ወደ ጥንቃቄው አመዝነው ተጋጣሚያቸው ከሜዳው እምብዛም እንዳይወጣ ቢወጣም አደጋ እንዳይጥልባቸው አድርገው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ ኢትዮጵያ ቡና ፈጠን ባሉ ጥቃቶች ጨዋታውን ጀምሯል። 49ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ከተከላካዮች አምልጦ የገባበትን አጋጣሚ ለግብ ለማመቻቸት ሞክሮ በሞክሼው ግብ ጠባቂ የተያዘበት ሁኔታም አደገኛ ነበር። ከዚህ በኋላ ግን ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ታይቷል። ጅማዎች ይበልጥ በራሳቸው ሜዳ ላይ ቀርተው የቡናን ቅብብሎች በማቋረጥ ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን አድርገዋል። ቡድኑ ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን አይፍጠር እንጂ በመከላከሉ ረገድ ተጋጣሚውን ገድቦ መቆየት ችሏል።


ቡድኖቹ ያደረጓቸውን ቅያሪዎች ተከትሎ ግቦች ለማግኘት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። ኢትዮጵያ ቡና እንዳለ ደባልቄን ካስገባ በኋላ አቡበከርን ከግራ መስመር እንዲነሳ አድርጎ ብበዛው አቅጣጫ ተደጋጋሚ ጫና ለመፍጠር ሞክሯል። ጅማም ሳዲቅ ሴቾ እና ሱራፌል ዐወልን በማስገባት የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ያም ቢሆን ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ሊጠናቀቅ የግድ ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ