ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

ነገ በሁለተኝነት የሚከናወነውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን አንስተናል።

ከቻምፒዮንነት ውጪ ባሉት የሁለተኝነት እና ያላመውረድ ፉክክሮች ውስጥ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሳምንቱ ቀዳሚ በሆነው በዚህ ጨዋታ እርስ በእርስ ይገናኛሉ። ሰበታ ከተማ ካለበት የስድስተኝነት ቦታ ወደ ሦስተኝነት ለመስፈንጠር እና የሌሎቹን ውጤት ተከትሎ የአፍሪካ ኮንፌዴርሽን ዋንጫ ተሳትፎ ዕድሉ በመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ የመወሰን ሊወሰን ይችል እንደሆነ ለማወቅ ይህንን ውጤት አጥብቆ ይፈልገዋል። ከዚህም በላይ ግን ጨዋታው ለወልቂጤ ከተማ እጅግ አስፈላጊው ነው። ከዚህ ጨዋታ ምንም ነጥብ ማግኘት ካልቻለም በዚሁ የጨዋታ ሳምንት ሊጉን ሊሰናበት ይሚችልበት ዕድል ይኖራል።

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ያሉበት የቡድን መንፈስ እና የአሸናፊነት ሥነ ልቦና እንዲሁም እስካሁን የመጡበት መንገድ እጅግ የተለያየ ነው። የሊጉ ባህሪ ነገሮችን ቶሎ የሚቀያይር ከመሆኑ ባሻገር በተከታታይ ጨዋታዎች አስፈላጊውን ውጤት እየያዘ ከሜዳ መውጣቱ ሰበታ የውድድር ጉዞው ሌላ መልክ እንዲይዝ ሆኗል። ከሳምንታት በፊት ላለመውረድ በሚደረገው ፍልሚያ ውስጥ የነበረው ቡድን አሁን ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ወደ አህጉራዊ ውድድር ለመብቃት እየጣረ ይገኛል። ይህ በውድድር ውስጥ ያለው የቡድኑ ዓለማ በበጎ ጎኑ መቀየሩ በተከታታይ ካሳኩት ድል ጋር ተዳምሮ በነገው ጨዋታ የተለየ ተነሳሽነት እንደሚፈጥርላቸው ይገመታል። የወልቂጤ ከተማ ሁኔታ ደግሞ ከዚህ ፍፁም ተቃራኒ ነው። ድንገት ለደረጃ መፎካከር ቢከብደው እንኳ ከሰንጠረዡ ወገብ በላይ ሆኖ ዓመቱን እንደሚጨርስ ብዙዎች በእርግጠኝነት ይናገሩለት የነበረው እና በውጤትም ሆነ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ይህንኑ ዕውነታ ያሳይ የነበረው ቡድን ዛሬ ላለመውረድ እያጣጣረ ይገኛል። ከዚህም አንፃር በተሸናፊነት መንፈስ ውስጥ ሆኖ የተሻሻለው ተጋጣሚውን ለማፋለም ይገደዳል።

ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንፃር ሁለቱም ቡድኖች ኳስ መቆጣጠር ላይ የሚያተኩሩ ቡድኖች እንደመሆናቸው የተለየ አቀራረብ ከሌላቸው በቀር በነገው ጨዋታ አማካይ ክፍል ላይ የበላይነት ለመውሰድ የሚያደርጉት ትግል ወሳኝነት ይኖረዋል። በዚህ ሂደት ውስጥም በሁለቱም በኩል ጨዋታን የማደራጀት ብቃት ያላቸው እንደ አብዱልከሪም ወርቁ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ያሉ አማካዮች የሚኖራቸው የዕለታዊ ብቃት ለቡድኖቹ ስኬት ወሳኝ መሆኑ አይቀርም። በሁለቱ ሳጥኖች ውስጥ የሚደርሱ የመጨረሻ ኳሶችን አስበን የሚኖሩትን ፍልሚያዎች ስንመለከት ደግሞ ነገሮች ለሰበታ የሚያደሉ ሆነው ይገኛሉ።

እዚህ ላይ በዋነኝነት የሰበታው ኦሴይ ማዎሊን ወቅታዊ ብቃት ከግምት ማስገባቱ ተገቢ ይሆናል። እርጋታ የማይታይበት እና በቀላሉ ጎል የሚቆጠርበት የወልቂጤ የኋላ ክፍል በድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው ይህን ጋናዊ አጥቂ እንዴት ይቆጣጠራል የሚለው ጉዳይም ከሰራተኞቹ ምላሽ የሚጠብቅ ይመስላል። በተቃራኒው ብንመለከተውም የጎል ዕድሎችን እንደነገሩ የሚያባክነው የወልቂጤ የፊት መስመር ከፍሬው ሰለሞን እገዳ ፣ ከአሜ መሀመድ የአምስት ቢጫ ቅጣት እና ከቀድሞው የሰበታ አጥቂ እስራኤል እሸቱ ጉዳት ጋር ተደምሮ በምን መልኩ ጎሎችን አስቆጥሮ ወደ ድል ይመለሳል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ነው። ከሁለቱም አቅጣጫ የተሻለ ተገማችነትን የሚያገኘው ሰበታ ከተማም ግን አልፎ አልፎ የሚታይበት ለጨዋታ ተገቢውን ትኩረት ያለመስጠት ችግር ነገም ካገረሸበት በተጋጣሚው ላይ ያለውን ወረቀት ላይ ብልጫ ሁሉ ሊያጣ እንደሚችል ለመገመት የሀዲያ ሆሳዕናውን ጨዋታ ማሰብ ብቻ በቂ ይሆናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱን ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ያገናኘው ጨዋታ በሰበታ ከተማ 1-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ነበር።