ሪፖርት | ሰበታ ከተማ ወደ ሦስተኝነት ከፍ ብሏል

ሰበታ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 1-0 በማሸነፍ ለኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ደረጃ ሲቀርብ ወልቂጤ አንድ እግሩ ከሊጉ ተንሸራቷል።

ወልቂጤ ከተማ ከሀዋሳ አቻ ከተለያየው ስብስብ አሜ መሐመድ (ቅጣት) ፣ አልሳሪ አልመሐዲ እና አህመድ ሁሴንን በሄኖክ አየለ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ያሬድ ታደሰ በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ ከአዳማው ድል አራት ለውጦች ሲደረጉ ዓለማየሁ ሙለታ ፣ አንተነህ ተስፋዬ ፣ መስዑድ መሐመድ እና ታደለ መንገሻን በማሳረፍ በምትካቸው ፍፁም ገብረማርያም፣ ጌቱ ኃይለማርያም፣ ቡልቻ ሹራ እና መሳይ ጳውሎስ ተካተዋል።

ጥቂት የሚባሉ የግብ ሙከራዎችን ባስመለከተን ቀዳሚው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከፍተኛውን የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ለማግኘት መሀል ሜዳ ላይ ብርቱ ፉክክር አድርገዋል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ክሪዚስቶም ንታንቢን በጉዳት አጥተው አብዱልባስጥ ከማልን ያስገቡት ሰበታ ከተማዎች ጨዋታ ወደ ውሀ እረፍት እስኪያመራ ድረስ እስከ ተጋጣሚያቸው ሜዳ ይዘልቅ የነበረ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ማሳካት ችለዋል። ነገር ግን የተሻለው ቀዳሚ የግብ አጋጣሚ የተፈጠረው በወልቂጤዎች በኩል ነበር። 13ኛው ደቂቃ ላይ አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር የሰበታን ተከላካዮች እንደቀልድ አልፎ ወደ ግብ ለመሞከር ቢጥርም ምቱ ጠንካራ ሳይሆን በጎን ወጥቷል።

የሰበታዎች ብልጫ ጫን እያለ በሄደባቸው ቀጣይ ደቂቃዎች ቡድኑ ጥሩ ሙከራዎችን አድርጓል። 20ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ ወደ ሳጥን ከተላከ እና ዳዊት እስጢፋኖስ በጥሩ ንክኪ ባደረሰው ኳስ በግንባሩ የሞከረው ኦሴ ማዉሊ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። 24ኛው ደቂቃ ላይም ወደ ኋላ በመመለስ ከአማካይ ክፍሉ ጋር ጥሩ ቅብብሎችን ሲከውን የነበረው ማዉሊ በረጅሙ ያደረሰውን ኳስ ተጠቅሞ ቡልቻ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራ በጀማል ጣሰው ድኖበታል።

በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ላይ ለመቆየት ተገደው የነበሩት ሰራተኞቹ ከወሀው ዕረፍት በኋላ በሰበታ አጋማሽ ላይ የታዩባቸው ቅፅበቶች በርከት ብለዋል። 32ኛው ደቂቃ ላይ እንደሁል ጊዜው ልዩ ጥረት ሲያደርግ ከነበረው አብዱልከሪም ወርቁ የግል ብቃት መነሻንውን ባደረገ ጥሩ የማጥቃት ዕድል ሳጥን ውስጥ ቢደርሱም ሂደቱ ያሬድ ታደሰ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ላይ ጥፋት ሰርቶ ተጠናቋል። አብዱልከሩም ከአንድ ደቂቃ በኋላም ከሳጥን ውጪ ለግብ የቀረበ የርቀት ሙከራ አድርጎ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ሌላኛው የአጋማሹ አደገኛ የማጥቃት አካሄድ 37ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ዳዊት እስጢፋኖስ በተከላካዮች መሀል ያሾለከው ድንቅ ኳስ የመጨረሻ የግብ ዕድል ለመሆን ቢቃረብም ቡልቻ በአግባቡ አልተቆጣጠረውም። ቡድኖቹ ወደ ዕረፍት ከማምራታቸው በፊትም ኦሴ ማዉሊ እና ሄኖክ አየለ በግንባር የሞከሯቸው ኳሶች ኢላማቸውን ሳይጠብቁ ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ሰበታዎች ዳግም ብልጫውን ይዘው ታይተዋል። በተለይም ፈጠን ባሉ ሽግግሮች ወደ ወልቂጤ ሳጥን የደረሱባቸው አጋጣሚዎች ቢታዩም በኦሴ ማዉሊ ውና ፍፁም ገብረማርያም የተደረጉ ሙከራዎች ደካማ ሆነው አልፈዋል። ወልቂጤ ከተማዎችም በበኩላቸው ኳስ ይዘው ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ቢታዩም ከመሀል ሜዳ ከማለፍ ውጪ አደገኛ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። የአጋማሹ ንፁህ የግብ ዕድል 73ኛው ደቂቃ ላይ ሲታይ ከቀኝ መስመር የታላከለትን ኳስ ፉዓድ ፈረጃ በግቡ አፋፍ ላይ ቢያገኘውም መጠቀም ሳይችል ቀርቷል።

ወልቂጤዎች በሁለተኛው አጋማሽ ሳጥን ውስጥ የገቡበት የመጀመሪያው ጥሩ ዕድል በአቡበከር ሳኒ ተሞክሮ ከተሳተ በኋላ ወዲያውኑ ግብ አስተናግደዋል። 81ኛው ደቂቃ ላይ ሰበታዎች በግራ በኩል ዳቂት እስጢፋኖስ ከቀማው ኳስ መነሻነት ሳጥን ውስጥ የገቡበት አጋጣሚ በማዎሊ አማካይነት ወደ ግደ ውስጥ ሲላክ ቶማስ ስምረቱ ለማውጣት ባደረገው ጥረት በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል። በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ወልቂጤዎች ቀጥተኛ ካሶችን ወደ ፊት በመላክ አቻ ለመሆን ያደረጓቸው ጥረቶች በጭማሪ ደቂቃ ከታየው የአህመድ ሁሴን ጠንካራ የረቀት ምት በቀር ሌሎች አጋጣሚዎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው ተገባዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ሰበታ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና በአንድ ነጥብ አንሶ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሲዳማ ቡና አንድ ነጥብ ካሳካ ወልቂጤ ከተማ ከሊጉ የሚያሰናብተውን ሽንፈት አስተናግዷል።