“ይህ ጅምር ነው፤ በቀጣይ ብዙ ዕቅዶች ናቸው ያሉን” – የተጫዋቾች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ኤፍሬም ወንድወሰን

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋቾች ማኅበር አቡበከር ናስርን የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች አድርጎ መምረጡን ተከትሎ  ስለ ምርጫው አካሄድ እና በቀጣይ ስለሚያስቡት የማኅበሩ ዋና ፀሐፊ ይናገራል።

ለመጀመርያ ጊዜ የዓመቱ ኮከቡን ምርጫውን ያደረገው ማኅበሩ የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርን የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች አድርጎ መምረጡን ከሰዓታት በፊት ማሳወቁ ይታወቃል። ይህ ተከትሎ የምርጫው ሒደት በምን መንገድ ተካሄደ? በቀጣይ በምን መልኩ ይቀጥላል? አባላቱ መላ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች እንደመናቸው ከፕሪምየር ሊጉ ውጪስ ምን ታስቧል? በፆታ ረገድስ ታሳቢ የተደረገ ነገር አለ ወይ? ስንል የማኀበሩን ዋና ፀሀፊ የቀድሞ ተጫዋች ኤፍሬም ወንደሰን ጥያቄ አቅርበንለት ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶናል።

” ይህ ምርጫ ለማኀበሩ የመጀመርያ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለመደ ቢሆንም ለኛ የመጀመርያ ነው። በሊጉ ለሚወዳደሩ አስራ ሦስቱም ክለብ አንበሎች መጠይቅ አዘጋጅተን በትነን ከአንድ ክለብ ውጭ አስራ ሁለቱ ምርጫቸውን አሳውቀውናል። በዚህም መሠረት አስሩ ክለቦች አቡበከር ናስን ሲመርጡ ሁለቱ ምርጫቸው ሌላ ሆኗል። እኛም ምንም የኮሚቴ ድምፅ ሳንጨምር አቡበከርን የማኅበሩ የመጀመርያው የዓመቱ ኮከብ ተጫዋች አድርገነው መርጠናል። አሁን ስሜቱ ሳይቀዘቅዝ ምርጫውን እናሳውቅ እንጂ ወደፊት ሰፋ ያለ የዕውቅና አሰጣጥ መድረክ ይኖረናል።

” በሴቶቹም ረገድ በተመሳሳይ መጠይቅ አዘጋጅተን ለክለቦቹ የበተንን ቢሆንም እስካሁን ምላሻቸውን ሊያሳውቁን አለመቻላቸው እንጂ በሴቶችም ዘርፍ በቀጣይ ኮከቦችን መርጠን የምናሳውቅ ይሆናል። ሽልማቱንም ከወንዶቹ ጋር በአንድ መድረክ የምናዘጋጅ ይሆናል።

” ይህን የዕውቅና ምርጫ በዚህ የሚቆም አይደለም። ይህ የመጀመርያችን ነው። በቀጣይ ብዙ ዕቅዶች ነው አሉን። የኮከብ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ለሀገር የለፉ የደከሙ ግለሰቦች በተለየ ሁኔታ የሽልማት እና የዕውቅና አሰጣጥ ፕሮግራም እናስባለን።

” ይህ በፕሪምየር ሊጉ ብቻ ተገድቦ የሚቆም አይደለም። በከፍተኛ ሊግ፣ በአንደኛ ሊግ፣ ከ20 ዓመት በታች ውድድር ጨምሮ ከታች ወርደን ለመስራት ቢከብደንም ከነዚህ ጥሩ ብቃት ያላቸውን ተስፋ ሰጪ ነገር ያሳዩትን መርጠን የመሸለም የማበረታታት ተነሳሽነትን ለመፍጠር እውቅና የመስጠት ሰፊ ዕቅድ አለን። ይህን የማድረግም ኃላፊነት ስላለብን በረጅም ጊዜ ዕቅዳችን እየተገበርን እንሄዳለን። ”