የረፋዱ ጨዋታ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞች ለሱፐር ስፖርት የሰጡት አስተያየት ይህንን ይመስላል።
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ፋሲል ከነማ
ስለቻምዮንነት ስሜት
ፋሲል ከነማ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ይህን ዋንጫ ሲያገኝ። የተለየ የሚያደርገው ደግሞ ጨዋታዎች በ ዲ ኤስ ቲቪ መታየት ሲጀምሩ መሆኑ ነው። በዚህ ዘመን የመጀመሪያውን ዋንጫ በማግኘቴ እጅግ ነው ደስ ያለኝ። እንዴት አድርጌ መግለፅ እንዳለብኝ ይከብደኛል።
የልጅነት ህልማቸው ስለመሆኑ
በልጅነቴ በወሎ ምርጥ ውስጥ ድንቅ ከሚባሉ ተጫዋቾች ውስጥ ነበርኩ። በጊዮርጊስም በእኔ ውጤት ብዙ ድል ያገኘንበት አጋጣሚ ነበር። ነገር ግን የተጫዋችነት ዘመኔን በጉዳት ነው ያቆምኩት። እንዲያም ቢሆን ከሥራ ዓለም ጀምሮ ስፖርት ኮምሽንም ቴክኒክ ኃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ። ከዛ ጊዜ ጀምሮ የሥልጠና ትምህርት ዕድሎችን በሀገር ውስጥም በውጪም አግኝቻለሁ። ያንን እያሰፋሁ ነው የሄድኩት። የተለያዩ ድሎች ገጥመውኛል የዛሬው ደግሞ የተለየ ስሜት የሚሰጠኝ በክለቡ ታሪክ የመጀመሪያው በመሆኔም ነው።
ስለዓመቱ ውጣ ውረዶች
ሥልጠና ዓለም ላይ ከባድ ከሚባሉ ሥራዎች አንዱ ነው። አዲስ አበባ ላይ በነበረው ውድድር ከፍታ እና ዝቅታ ነበረው። በዛ መካከል ውስን ደጋፊዎች ያደርጉት የነበረው ጫና ለሥራችን ብዙ እንቅፋት ነበረው። ያን ተወጥተን ግን ዛሬ ላይ ደርሻለሁ። በዚህ አጋጣሚ በጣም የደገፋችሁኝም የተቃወማችሁኝም አሁን አንድ ላይ ለፋሲል ሁላችንም የታሪክ ባላደራ ስለሆንን ሁላችሀንም እንኳን ደስ ያላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።
በልዩነት ስለሚነሱ ተጫዋቾች
ሁሉም በዓመቱ ያሳዩት ብቃት ደስ የሚል ቢሆንም በተለይ አምበሎቻችን እነ ያሬድ እነ ሳኛ ዓይነቶቹ ቡድኑን በማያያዝ በማፋቀር እኛ ጋር ሳይደርስ ነገሮችን እየያዙ ለቡድኑ መንፈስ የከፈሉት ዋጋ በጣም ትልቅ ነው። የእነዚህ ድምር ውጤት ሁሉ ለቡድኑ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል ብዬ አስባለሁ።
ስለሊጉ ምርጦች
እኔ የመረጥኳቸው ውስጥ ያሬድ አቡበከር እና ሀብታሙ አሉ።
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረት – ሀዋሳ ከተማ
ለአሰልጣኝ ከማል አህመድ ስላበረከተው ማስታወሻ
ምክንያቱ ግልፅ ነው ፤ ከልጅነቴ ጀምሮ አሁን እስካለሁበት ጊዜ ድረስ መሰረቴ እሳቸው ስለሆኑ ነው። አጋጣሚውም አብሮ ሄዶልኛል ፤ ቡድናችን ሁለት ጊዜ ቻምፒዮን ሲሆን ከእሳቸው ጋር ነው። ዛሬም ፋሲል ቻምፒዮን ሲሆን በውቧ ከተማ ላይ ስለሆነ ነው። ለእሳቸው ያለኝን ክብር ለመግለፅ ነው። እኔን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ እነ ዘውዱ በቀለ ፣ ገረሱ ፣ አፈወርቅ ፣ ሹሬ ፣ አዳነ ፣ ሽመልስ ፣ በኃይሉ በጣም ብዙ ተጫዋቾችን ያፈሩ ናቸው። እና በእኔ አቅም በዚህ መድረክ ላይ ከእሳቸው ጋር ለመገናኘት ፈልጌ ነው።
ቡድኑ አቻ ሲሆን ስላሳየው ደስታ አገላለፅ
አንደኛ እንደ መጀመሪያ ዓመቴ የተሻለ ቦታ ላይ መቀመጥ እፈልጋለሁ። ሁለተኛ ለክለቡም ደግሞ ደጋፊ ባለበት ጨዋታ ላይ ማየት ስላለባቸው ተጫዋቾች አቅማቸውን አውጥተው እንዲጫወቱ እፈልጋለሁ። ያ ደግሞ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር ብዬ ነው ማስበው። ምክንያቱም የተሟላ ቡድን አይደለም በጉዳት የሌሉ ተጫዋቾችም ስላሉ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው።
ከመቼ ጀምሮ ፋሲል ቻምፒዮን እንደሚሆን እንዳሰበ
የፋሲል ስብስብ አብሮ በመቆየቱ ትልቅ ተፎካካሪ እንደሚሆን ግምቱ ነበረን። ከጅማ በኋላ ግን ዕድሉ እንዳላቸው እንገምት ነበር። ደግሞ ይገባቸዋል ፤ ጥሩ ቡድን ፣ ጥሩ ደጋፊ ፣ ጥሩ የአሰልጣኞች ቡድን አላቸው ፤ የተደራጀ ቡድን ነው። እና እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ በውቢቱ ከተማ ላይ ዘና እንዲሉ ነው ምኞቴ።
ከፋሲል ተጫዋቾች መሀል ምርጡ
ሁሉም ዘንድሮ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። የማልደብቀው ነገር ሀብታሙን እወደዋለሁ። ያሬድ ፣ ሽመክት እና ሱራፌልም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ናቸው። ሦስቱን ብመርጥ ደስ ይለኛል።
ስለሊጉ ምርጦች
መምረጥ ከባድ ነው። የእኔ ምርጫ ግን የሆነው ሀብታሙ ነው። ቻምፒዮንም ስለሆነ እሱ ምርጥ ቢባል ደስ ይለኛል ግን ከአቡበከር ናስር ጋር ግን ከባድ ፉክክር ይጠብቀዋል።