ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በሀዋሳ የሚደረገውን የመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።

በታችኛው የሰጠረዡ ክፍል ፉክክር ውስጥ ያሉትን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ ለአንዳቸው ተስፋን ለሌላኛቸው ደግሞ የመጨረሻ ዕድልን ይዞ የሚመጣ ነው። በሊጉ የመቆየት ተስፋው በእጁ ያለው ድሬዳዋ ከተማ ሙሉ ነጥቦችን ካሳካ በጊዚያዊነትም ቢሆን ከአደጋው ቀጠና በአራት ነጥቦች መራቅ ይችላል። እስካሁን ዘጠኝ ነጥብ ላይ የቆሙት አዳማዎች ግን ከጨዋታው ምንም ውጤት አለማግኘት በሊጉ ለመቆየት ያላቸው ብቸኛ ዕድል የትግራይ ክለቦች ወደ ውድድር አለመመለስ እና በከፍተኛ ሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ከያዙ ቡድኖች ጋር የሚደረገው ጨዋታ ብቻ ይሆናል።

በአመዣኙ ደካማ የውድድር ጊዜን ያሳለፉት የነገዎቹ ተጋጣሚዎች በተለይም በውድድሩ የድሬዳዋ ቆይታ ላይ ለውጦችን አሳይተው ተመልክተናቸዋል። ነገር ግን ተፈላጊውን መሻሻል በውጤት ከማጀብ አንፃር ድሬዳዋ ከተማ በብዙ ርቀት የተሻለ ነበር። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ድሎችን ያሳኩት ብርቱካናማዎቹ ሽንፈት ያገኛቸውም በአንድ ጨዋታ ብቻ ነበር። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በአጠቃላይ እንቅስቃሴው እና በተጫዋቾች የግል ብቃት ላይም በጎ ለውጦችን አሳይቶ ተመልክተነዋል። ይህ መሆኑም የቀጣይ ዓመት ዕጣ ፈንታውን በሚወስነው የሀዋሳው ውድድር ላይ ይበልጥ ጠንክሮ እንዲመጣ መንገዱን የሚያመቻችለት ይመስላል። በተለይም በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱን በማሰብ እንደቡድን የሚከላከልበት መንገድ ላይ ያሉትን ለውጦች መናገር ይችላል። በዕረፍቱ ቀናት የቡድኑ የማጥቃት ሂደትን ዕድሎችን ደጋግሞ ከመፍጠር እና ተረጋግቶ ከመጨረስ አንፃር ያደረገው ዝግጅት ደግሞ የሚፈተነው ከደካማ ተጋጣሚ ጋር በመሆኑ ቡድኑን ዕድለኛ የሚያደርገው ይመስላል።

በአዳማ ከተማ የቡድን መዋቅር ውስጥም መልካም ለውጦች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ነገር ግን ቡድኑ በሙሉ በራስ መተማመን ከጨዋታዎች ውጤት ይዞ ለመውጣት አለመቻሉ ሲታይ አሁንም የሽግግር ጊዜውን እንዳልጨረሰ መገንዘብ ይቻላል። እርግጥ ነው ከዚህ በኋላ ምንም የሚያጣው ነገር አለመኖሩ ሲታሰብ በነገው ጨዋታ በተለይም የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የተሻለ ድፍረት ኖሮት የሚያጠቃ ቡድን ከአዳማ ከተማ ይጠበቃል። ሀዋሳ ከተማ ላይ ካሳካው ድል በኋላ ውሉ ውጤት ማስመዝገብ ተስኖት የቆየው አዳማ በጨዋታ የሚቆጠርበትን ግቦች ቁጥር መቀነሱ እንደ ስኬት ይታይ እንደሆን እንጂ መረቡን ሳያስደፍር መውጣት ካለመቻሉ በተጨማሪ አልፎ አልፎ ብልጭ ከሚሉ የግብ ዕድሎች በቀር በተደጋጋሚ በተጋጣሚዎቹ ሳጥን ዙሪያ መገኘት አለመቻሉ ደካማ ጎኖቹ ሆነው ቀጥለዋል። ነገም በነጥብ ቢርቀውም በደረጃ ከሚቀራረበው ተጋጣሚው ውጤት ለማግኘት ይበልጥ ደፍሮ የሚያጠቃ በስነ ልቦናው ታድሶ የሚገባ ቡድን ማቅረብ የግድ ይለዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ክለቦች በሊጉ 17 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ ስምንት ጨዋታዎችን በድል ሲያጠናቅቅ ድሬዳዋ ስድስቱን አሸንፏል ፤ 3 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። አዳማ 17 ፣ ድሬዳዋ 15 ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ