ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ ቡና ከ ወላይታ ድቻ

ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻን ጨዋታ እንደሚከተለው ተመልክተነዋል።

ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ እና የአፍሪካ የክለቦች የውድድር መድረክ (የኮንፌዴሬሽን ካፕ) ላይ ተሳታፊ የሚያደርገውን የሁለተኛ ደረጃ አጥብቆ ለመያዝ ሦስት ነጥብን አልሞ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይታሰባል። የድሬዳዋ ቆይታውን በጥሩ አፈፃፀም ያገባደደው ወላይታ ድቻ በበኩሉ አሁንም በአሸናፊነት ለመዝለቅ እና ሌላኛውን የሸገር ክለብ (በ21ኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፎ ነበር) ረቶ በደረጃ ሠንጠረዡ ከበላዩ ከሚገኙ ክለቦች ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ድልን እያሰበ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይገመታል።

እስከ 22 የጨዋታ ሳምንት ድረስ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ (36) ክለብ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ነገም በአስፈሪው የአጥቂ መስመሩ ለድቻ ተጫዋቾች የራስ ምታት ሆኖ እንደሚጫወት ይገመታል። ከምንም በላይ ደግሞ 22 ጎሎችን በ19 ጨዋታዎች ያስቆጠረው አቡበከር ናስር ፍጥነት እና ቅልጥፍናውን ተጠቅሞ የሚያደርጋቸው የጎል ፊት እንቅስሳሴዎች ለቡድኑ በጎ ነገሮችን ይዞ ብቅ ሊል ይችላል። ከአቡበከር በተጨማሪም የቡድኑ የመስመር ላይ ተጫዋቾች (የመስመር አጥቂዎች እና ተከላካዮች) ጠንካራውን የድቻ የኋላ መስመር ለመዘርዘር ፈጣን ሩጫዎችን በተሰለፉበት መስመር ላይ እንደሚያደርጉ ይገመታል። በዋናነት ግን ቡና በነገው ጨዋታ ከፍተኛ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንደሚኖረው ይገመታል። በዚህም ከኋላ ጀምሮ ኳስን በትዕግስት በመቀባበል የተጋጣሚውን ጎል ለማግኘት እንደሚታትር ይታሰባል።

ከላይ እንደገለፅነው ኢትዮጵያ ቡና የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቡድን ቢሆንም ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ላይ ግን ኳስ እና መረብን ማገናኘት ተስኖት ታይቷል። በተለይ ደግሞ እንደ ጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ በቁጥር በዝቶ የሚከላከል ቡድን በሚጋፈጥበት ጊዜ ቡና መፍትሄዎችን ለማግኘት ሲቸገር ሲታይ አዲስ አደለም። ስለዚህም ነገ በተቃራኒ ቡድን በኩል ሊገጥመው የሚችለውን ጥብቅ የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ ለመግባት ከፍተኛ ዝግጁነት ይጠይቃል።

ታትሮ በመጫወት የማይታማው የአሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ቡድን ነገም በዚህ ተግቶ የመጫወት ፍላጎት ላይ ሆኖ ጨዋታውን እንደሚከውን ይገመታል። በተለይ ቡድኑ ግጥግጥ ብሎ በመከላከል የተጋጣሚን አጨዋወት በመመከት ከዛም ደግሞ ፍጥነት የታከለባቸው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሲጫወት ይታያል። ከዚህም በተጨማሪ ዘለግ ያለ ቁመት ያለውን እና እጅግ ምርጥ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ስንታየሁ መንግስቱን ዒላማ ያደረጉ ረጃጅም ኳሶች በመላክ የግብ ማግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ይሞክራል። ይህንን መነሻ በማድረግ ነገም ቡድኑ በተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን የኳስ ቅብብሎች በራሱ ሜዳ ላይ ሆኖ በማቋረጥ እና ብዙ ጊዜ በቁጥር በዝቶ ለማጥቃት በሚል የራሳቸውን የግብ ክልል ለቀው የሚወጡትን የቡና ተጫዋቾች ጀርባ የሚገኘውን ሜዳ በማጥቃት አደጋ ለመፍጠር እንደሚሞክር ይታሰባል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሌላው ምርጥ ብቃቱ ላይ የሚገኘው ቸርነት ጉግሳ የሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች ለቡናዎች ፈተና ሊሆን ይችላል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ስድስት ጊዜ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው ወላይታ ድቻ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ላይ መጠነኛ መዳከም በመከላከሉ ረገድ አሳይቷል። መሻሻል ላይ እንደነበር ሲታይ የነበረው የቡድኑ የኋላ መስመርም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች አስር ግቦችን በማስተናገድ መጠነኛ መዳከም አሳይቷል። ከዚህም መነሻነት ቡድኑ ነገ የሚገጥመው የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለብ መሆኑ ሲታሰብ ይህ የኋላ መስመሩ የሚገጥመውን ፈተና ለማለፍ በጥሩ ደረጃ ላይ መገኘት እንደሚሻው ይታመናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ በሊጉ ለ13 ጊዜያት ተገናኝተዋል። በግንኙነታቸውም የተሻለ ሪከርድ ያለው ወላይታ ድቻ ነው። በዚህም ድቻ አራት ጊዜ ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ሦስት ጊዜ ድል አግኝቷል። በቀሪዎቹ ስድስት ግንኙነቶች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው ኢትዮጵያ ቡና 11 ወላይታ ድቻ ደግሞ 10 ግቦችን አስቆጥረዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ