የ2013 የኢትዮጵያ የአንደኛ የማጠቃለያ ውድድር በቡራዩ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ስድስት ቡድኖችን ለመለየት በአስራ ስድስት ክለቦች መካከል በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

3:00 ላይ የጀመረው የደረጃ ጨዋታ አምቦ ከተማን ከእንጅባራ ከተማ አገናኝቶ አምቦ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 4-1 አሸናፊነት ሆኗል። በጨዋታው ጅማሬ ኳሱን ተቆጣጥረው ወደ ፊት በመሄድ እና ተከታታይ የጎል እድሎችን መፍጠር የቻሉት እንጅባራዎች በተለይ ፀጋሰው ሰለሞን ከግብጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ጎል አስቆጠረ ሲባል በግቡ አግዳሚ ወደ ውጭ የሰደዳት ኳስ በጣም የምታስቆጭ ነበረች። በዚህም ስህተቱን መታገስ ያልቻሉት አሰልጣኙ ብዙም ሳይቆዩ ተጫዋቹን ለመቀየር ወስነዋል።

የእንጅባራ ግልፅ የጎል አጋጣሚ ከመከነ በኃላ የተነቃቁት አምቦዎች በ11ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ ጫላ ከበደ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ ወደ ጎልነት ተቀይሮ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። አምቦዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል በተደጋጋሚ ከትኩረት ማጣት ስህተት ሲሰራ የቆየው የአንጅባራው ግብጠባቂ ቅዱስ ዳኘው ቢፈጥርላቸውም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። እንደነበራቸው ብልጫ ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚገባቸው አምቦዎች በ35ኛው ደቂቃ በግምት ከ30 ሜትር ዕርቀት በክሪ ዘይን የግብጠባቂ ቅዱስ ዳኘው ከግብ ክልሉ ውጭ መቆሙን አይቶ መጥኖ የላካት ኳስ በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አርፋ ሁለተኛ ጎል ተመዝግቧል።

በሁለተኛው አጋማሽ እጅጉን ተሻሽለው የቀረቡት እንጅባራዎች በተደጋጋሚ ወደ አምቦ የሜዳ ክፍል በመመላለስ የፈጠሩት ጫና በ54ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቶ ከማዕዘን ምዕየት የተሻማን ኳስ አበባው አድማሱ ወደ ጎልነት ቀይሮት የጎል ልዩነቱን ማጥበብ ችለዋል። ወደ ጨዋታ የሚመለሱበትን እንቅስቃሴ ጎል በማስቆጠር የተነቃቁት እንጅባራዎች ይህን እንቅስቃሴያቸውን ማስቀጠል ተስኗቸው እየተቀዛቀዙ መጥተው ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። አምቦች ላይ በ74 ኛው ደቂቃ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ኢብሳ ጥላሁን አስቆጥሮ የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል። ወደ ጨዋታው መገባደጃ ላይ ራሱ ኢብሳ ጥላሁን በጥሩ ሁኔታ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ አራተኛ ጎል አስቆጥሮም ጨዋታው በአምቦ የበላይነት ተጠናቋል።

በአምቦ ቡድን ውስጥ በመከላከሉ ረገድ ገላን ደንቦባ፣ በአማካይ ቦታ ላይ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ፍራኦል እና በማጥቃቱ ረገድ በክሪ ዘይን የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር።

አምስት ሰዓት የውድድሩ መዝጊያ ጨዋታ በቡራዩ እና በዳሞት መካከል ተካሂዶ እጅግ ሳቢ የሆነ የፍፃሜ ጨዋታ አስመልክቶን በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንድ አቻ በሆነ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ መለያ ምት አምርቶ በቡራዩ ከተማ 5-3 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር ባስመለከተን በዚህ የፍፃሜ ጨዋታ የጎል ዕድል በመፍጠርም ሆነ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የሆኑት ቡራዩዎች በ11ኛው ደቂቃ በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ በተመለከትነው በክሪ አህመድ ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በእንቅስቃሴ ብልጫ የነበራቸው ዳሞቶች ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ካለመረጋጋት የተነሳ እየባከኑ በሚመለሱ ኳሶች ቡራዮዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ጎል ማስቆጠሩበት ዕድል አለመጠቀማቸው በኃላ ላይ ዋጋ ሊያስከፍላቸው እንደሚችል በሚገመትበት ሰዓት የአቻነት ጎል አስቆጥረዋል።
በማጠቃለያ ውድድሩ ላይ የዛሬውን ጨምሮ በድምሩ አምስት ጎል በማስቆጠር ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ሙሉጌታ መኮንን በ38ኛው ደቂቃ የአቻነት ጎሉን አስቆጥሯል።

በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ ተጋግሎ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሁለት መልክ የነበረው ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ እንጅባራዎች ብልጫ ሲወስዱ ግልፅ የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ቡራዩዎች የተሻሉ ነበሩ። በተለይ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ የቡራዩ አጥቂ ካሚል አህመድ በግንባሩ ገጭቶ ግብጠባቂው እንደምንም ያዳነበት የሚያስቆጭ ነበር። በጨዋታው ደቂቃዎች በእየገፉ በሄደ ቁጥር ወደ ጥንቃቄ አጨዋወት ያመሩት ሁለቱም ቡድኖች ብዙም የተለየ ነገር ሳያስመለክቱን መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በአንድ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወደ መለያ ምት አምርተው ቡድኑ ወደ ከፍተኛ ሊግ እንዲያድግም ሆነ የውድድሩን ዋንጫ እንዲያነሳ ትልቅ አበርክቶ የነበረው ልማደኛው የፍፁም ቅጣት ምት ቀበኛ ወንድወሰን ገረመው ሁለት ምቶችን በማዳን ጨዋታው 5-3 በቡራዩ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በቡራዩ በኩል ከግብጠባቂው ወንደሰን ገረመው በተጨማሪ በቡድኑ ውጤት ውስጥ የአጥቂዎቹ ጫላ በንቴ እና ከሚል አህመድ አስተዋፆኦ ከፍተኛ ነበር።

በመጨረሻም ከአንድ እስከ ሦስት ለወጡት ክለቦች የሜዳልያ አሰጣጥ ስነ ስርዓት ከተካሄደ በኃላ በስፖርታዊ ጨዋነት አምቦ ከተማ ተሸለሚ በመሆን ከዕለቱ እንግዳ ዋንጫው ሲረከብ የውድድሩ አሸናፊ ቡራዩ ከተማ በአንበሉ አማካኝነት ዋንጫዋን ከፍ አድርጎ በማንሳት የዕለቱ መርሐግብር ተፈፅሟል።

*ውድድሩ ላይ ባልተገኘንባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሙሉ መረጃ በፍጥነት በመስጠት የተባበረን የአንደኛ ሊግ የኮሚቴ አባል የሆነው የሸዋስ በቀለን ሶከር ኢትዮጵያ ታመሰግናለች።