ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባ ጅፋር

የ23ኛውን ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንዲህ አንስተናል።

የውድድር ሳምንቱ በመልካም ቁመና ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻን በሊጉ የመቆየት ተስፋው ከተመናመነው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ያገናኛል። ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ነጥቦችን የሰበሰቡት ወላይታ ድቻዎች በሰንጠረዡ አጋማሽ ቢገኙም ቀሪዎቹ ጨዋታዎች ደረጃቸውን ይበልጥ አሻሽለው ለመጨረስ ስለሚረዷቸው ካለብዙ ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ለማሳካት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ከድል ውጪ ምንም አማራጭ የሌላቸው ጅማ አባ ጅፋሮች በአንፃሩ ከበላያቸው ካለው ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የስምንት ነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ማጥበብ በሊጉ የመቆየት ፈተናቸው የዚህ ሳምንት ግብ ይሆናል።

የጨዋታ አቀራረቡን ከተጋጣሚው አንፃር ሲቃኝ የሚታየው ወላይታ ድቻ በነገው የጅማ ግጥሚያ የማጥቃት ፍላጎቱ ከፍ ብሎ እንደሚታይ ይጠበቃል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የተመለከትነው የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ምርጫም ከኳስ ጋር የተሻለ በመቆየት እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በመሞከር ሊየካ ይችላል። ነገር ግን በቡናው ጨዋታ የታየው ተጋጣሚ የተሻለ ክፍተት በፈጠረባቸው ቅፅበቶች በስኬታማ ቅብብሎች ሰብሮ መግባት ላይ መቸገሩን ነገ አርሞ መቅረብ ይጠበቅበታል። ቡድኑ በአጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ የኋልዮሽ እንቅስቃሴ በመታገዝ ወሳኝ በሆነው ከተጋጣሚው የተከላካይ መስመር ፊት ባለው ቦታ ላይ የተሻለ አደጋ የሚፈጥሩ ቅብብሌችን በመከወን ቀደም ባሉ ጨዋታዎች ያሳየውን ብቃት መልሶ እንዲያገኝ ማድረግ የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ዋና ትኩረት የሚሆን ይመስላል።

ከሁለቱ የመዲናዋ ከለቦች ጋር በተከታታይ ነጥብ መጋራት የቻለው ጅማ አባ ጅፋር በእንቅስቃሴ እየተሻሻለ መምጣቱን በነገው ጨዋታ በውጤት የማጀብ ደረጃ ላይ መድረስ ይኖርበታል። በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስር የመከላከል ሪከርዱ ተሻሽሎ የታየው ጅማ ከቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግድ መውጣቱ ለነገው ጨዋታ ሊያስቀጥለው የሚገባው ጠንካራ ጎኑ ነው። እርግጥ ነው ወላይታ ድቻን በጥልቅ ተከላክሎ ለመጫወት ዕቅድ ላይኖረው ቢችልም ከኳስ ውጪ በሚሆንባቸው ጊዜያት ሁሉ የተጋጣሚውን ወቅታዊ አቋማቸው መልካም የሆኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎች በአግባቡ መቆጣጠር ይጠበቅበታል። በተለይ በውድድር ዓመቱ በጨዋታ ከሁለት በላይ ግብ አስቆጥሮ አለማወቁ ሲታሰብ ነገ የሚያገኛቸውን የግብ ዕድሎች መጠቀም ላይ ያለበትን ድክመት አሻሽሎ ግብ ቢያስቆጥር እንኳን በመከላከሉ ረገድ ሙሉ ትኩረቱ ላይ መገኘት እጅግ አስፈላጊው እንደሆነ ይታመናል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለአምስት ጊዜያት ተገናኝተው ወላይታ ድቻ (አንድ ፎርፌ ጨምሮ) ሦስቱን ሲያሸንፍ በአንዱ አቻ ወጥተው ጅማ አባ ጅፋር አንድ አሸንፏል።

– በአራቱ ግንኙነት 12 ጎሎች (የድቻ ሦስት የፎርፌ ጎሎችን ጨምሮ) ሲቆጠሩ ድቻ ሰባቱን ጅማ ደግሞ አምስቱን አስመዝግበዋል።

* ወቅታዊው የኮቪድ ወረርሺኝ በቡድኖቹ የስብስብ ምርጫ ላይ እያሳደረ ካለው ተለዋዋጭነት አንፃር ግምታዊ አሰላለፍ ለማውጣት አዳጋች በመሆኑ የወትሮው የአሰላለፍ ትንበያችን በዳሰሳው ያልተካተተ መሆኑን እንገልፃለን።

© ሶከር ኢትዮጵያ