የሀዋሳ ዝግጅት ወቅታዊ ሁኔታ

የ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎችን የምታስተናግደው ሀዋሳ ከተማ እና ሠላሳ ጨዋታዎች የሚደረጉበት የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ከነገው ጅማሮ በፊት ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚከተለው ተመልክተናል፡፡

በአራት የተለያዩ ከተሞች ሲካሄድ የቆየው ውድድር የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰ ሲሆን አስተናጋጇ ከተማ ሀዋሳ ሠላሳ የሊግ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ዝግጅቷን አጠናቃለች፡፡ ፋሲል ከነማን ሻምፒዮን ለማድረግ የአንድ ጨዋታ ዕድሜ የቀረው እና ወራጆቹን እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀውን ለመለየት ከ22ኛ ሳምንት ጀምሮ ነገ በሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል፡፡

* ሁለት አይነት የአየር ፀባይ እየተፈራረቀባት የምትገኘው ሀዋሳ ከተማ ለወትሮው ከነበራት ሙቀታማ ባህሪ ባሻገር ቅዝቃዜ ከመጠነኛ ዝናብ ጋር አጣምራ ውላለች፡፡ ምንም እንኳን ሀዲያ ሆሳዕና እና ሰበታ ከተማ ወደ ውድድሩ ቦታ ከተጫዋቾች ገንዘብ ክፍያ ጋር በተያያዘ ያልደረሱ ቢሆንም ሌሎች ክለቦች ግን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ገብተዋል፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን ደግሞ በነገው ዕለት ወደ ከተማው ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ምንም እንኳን እንደ አስተናጋጅ ከተማ አቀባበል ለክለቦቹ ያልተደረገ ቢሆንም ክለቦቹ በጥሩ ሁኔታ ዝግጅት እያደረጉ ቆይተዋል፡፡

* ዛሬ ሶከር ኢትዮጵያ በስታዲየሙ ተገኝታ እንደታዘበችው የውድድሩ የበላይ አካላት የሊግ ካምፓኒው ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ፣ የውድድር ስነ ስርአት ኮሚቴ ሰብሳቢው ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ እና ሌሎች በርካታ ውድድሩን የሚመሩ አካላት ከረፋድ ጀምሮ በስታዲየሙ ተገኝተው የተለያዩ ምልከታዎችን ሲያደርጉ ውለዋል።

* ዛሬ ለመታዘብ እንደቻልነው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ለጨዋታ ምቹ ሆኖ ለማቅረብ ማሻሻያ የሚጠይቁ ቦታዎች ላይ ጥገና ሲደረግ የተመለከትን ሲሆን የሜዳ ማስመር እና የመረብ መስቀል እንዲሁም ለሜዳው የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮች ሲከወኑ ተመልክተናል፡፡

* በኢትዮጵያ ዳኞች ኮሚቴ 13 ዋና፣ 13 ረዳት በድምሩ 26 ዳኞች እንዲሁም አምስት ኮሚሽነሮች ለዚህ ውድድር ተመድበው ሀዋሳ ደርሰዋል። ካለፉት ጨዋታዎች አንፃር ምንም እንኳን ሊጉ ሻምፒዮኑን ለማሳወቅ የተቃረበ ቢሆንም ወራጅ ቡድኖች ግን ያልተለዩ በመሆኑ በአመዛኙ በድሬዳዋ የነበሩ ዳኞች ተካተውበታል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሰባቱን ኢንተርናሽናል ዳኞች በአምላክ ተሰማ፣ ቴዎድሮስ ምትኩ፣ በላይ ታደሰ፣ ኃይለየሱስ ባዘዘው፣ አማኑኤል ኃይለሥላሴ፣ ብሩክ የማነ ብርሀን እና ለሚ ንጉሴ ለዚህ ውድድር ተመርጠው ሀዋሳ ይገኛሉ፡፡ ከረዳት ኢንተርናሽናል ዳኞች ደግሞ ክንዴ ሙሴ፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ ፋሲካ የኃላሸት፣ ይበቃል ደሳለኝ እና ሸዋንግዛው ተባበል ሲሆኑ ቀሪዎቹ በሙሉ ፌዴራል ዳኞች ናቸው፡፡

* ጨዋታውን በቀጥታ ስርጭት የሚያስተላልፈው የሱፐር ስፖርት ባለሞያዎች ማምሻውን ወደ ከተማዋ ገብተዋል። የቴክኒክ ባለሞያዎቹ ደግሞ ከ10፡00 ጀምሮ ከነገ ጀምሮ ለሚደረገው ጨዋታ የካሜራ ተከላ እና ገጠማ ቦታዎችን ሲያመቻቹ አስተውለናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእንግሊዘኛ የጨዋታ አስተላላፊዎቹ በርናንድ ኦቴኖ እና ጊልበርት ሰልብዋ እንዲሁም ለአማርኛ ስርጭት ሰዒድ ኪያር፣ መኮንን ኃይሉ እና ማርቆስ ኤልያስ በስፍራው ተገኝተዋል፡፡

* በድሬዳዋ ከተማ ሲደረግ በነበረው ውድድር ላይ ከኮቪድ 19 ውጤት ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲነሳ የተስተዋለ ሲሆን በሀዋሳ በሚኖረው ውድድር ላይ ካለፈው ልምድ ተወስዶ በጥንቃቄ ለመፈፀም እንደተዘጋጁ የህክምና ኮሚቴ ገልጿል። ሆኖም ተጫዋቾች ሀዋሳ ከደረሱበት ጊዜ ጀምሮ ከተዘጋጀላቸው ሆቴሎች ውጪ በከተማዋ መታየታቸው ሥጋት እንደፈጠረባቸው ገልፀውልናል ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ