ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 21ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በድሬዳዋ የውድድር ምዕራፍ የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ላይ ጎላ ብለው የታዩ ተጫዋቾችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አሰላለፍ: 3-2-3-2

ግብ ጠባቂ – ፋሲል ገብረሚካኤል (ሰበታ ከተማ)

የምንተስኖት አሎን ወደ ተጠባባቂ ወንበር መውረድ ተከትሎ የቋሚነት ዕድል ያገኘው ፋሲል በ21ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር ያሳየው ብቃት ለቀጣዮቹ ጨዋታዎችም በግቦቹ መካከል ቆሞ እንደሚዘልቅ የጠቆሙ ናቸው። ቀልጣፋው የግብ ዘብ ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ሦስት ነጥብ ሲያገኝም የነበረው ድርሻ ትልቅ ነበር። በተለይም በዕለቱ ከምንይሉ፣ ፍፁም እና አፈወርቅ ወደ ግብ ሲላኩ የነበሩ ኳሶችን ያከሸፈበት መንገድ ደግሞ አድናቆት የሚያስቸረው ነበር።

ተከላካዮች

ቢያድግልኝ ኤልያስ (ሰበታ ከተማ)

አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከግማሽ በላይ የተጫዋች ለውጦችን ባደረጉበት የባህር ዳሩ ጨዋታ የመሰለፍ ዕድል ያገኘው ቢያድግልኝ በጨዋታ ሳምንቱ ጥሩ ጊዜ ነበረው። ከኋላ ክፍሉ ተጣማሪዎቹ በተሻለ በግሉ ያሳለፈው ጊዜ መልካም ሲሆን ከምንም በላይ ደግሞ ጊዜያቸውን የጠበቁት ሸርተቴዎቹ እና ፈጣኖቹን የባህር ዳር አጥቂዎች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት እንዲሁም ከአደጋ ዞን ኳስ በማጥራት ረገድ የተሳካ ጊዜ ማሳለፉ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ እንዲያስገባው ሆኗል።

ያሬድ ባየህ (ፋሲል ከነማ)

ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ዋንጫ እየገሰገሰ የሚገኘው ያሬድ በዚህኛውም የጨዋታ ሳምንት ያሳየው ብቃት ጥሩ ነበር። ተጫዋቹ ቡድኑ እንዳይጋለጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴም የአዳማ ከተማ ተጨዋቾች ምቾት ሲሰማቸው አልታየም። ከምንም በላይ ደግሞ ሰይፈ ዛኪር ወደ ሜዳ ከገባ በኋላ በጥሩ መነቃቃት ላይ የነበሩት አዳማዎች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ኳስ በ71ኛው ደቂቃ ያመከነበት መንገድ እጅጉን ቡድኑን የጠቀመች ነበረች። ከዚህም በተጨማሪ በቆሙ ኳሶች ቡድኑን ለመጥቀም (ግብ በማስቆጠሩ ረገድ) የሚያደርገው ጥረት ለአዳማዎች ከባድ ነበር።

ፍሬዘር ካሣ (ድሬዳዋ ከተማ)

በድሬዳዋ ድንቅ ጊዜ ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል ፍሬዘር ካሣ አንዱ ነው። ተጫዋቹ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በተደረገው ጨዋታ ፈጣኖቹ የነብሮቹ አጥቂዎችን በተለይም ዳዋ ሆቴሳን የተቆጣጠረበት መንገድ አድናቆት የሚያስቸረው ነበር። ከአጣማሪው በረከት ሳሙኤል ጋር በግሩም መናበብ እየተጫወተ የሚገኘው ፍሬዘር በሁለት አጋጣሚዎች አደገኛ ኳሶችን በስኬታማ ሸርታቴ ያስቆመ ሲሆን በራስ መተማመኑ ከፍ ያለ ደረጃ እየደረሰ መሆኑንም በአጨዋወቱ አሳይቷል። በዚህም ለተከታታይ ሳምንት በምርጥ አስራ አንድ ተካቷል።አማካዮች

ጋቶች ፓኖም (ወላይታ ድቻ)

ወላይታ ድቻ እጅግ ምርጥ ጊዜን ባሳለፈበት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ ከታዩ ጥሩ ተጨዋቾች መካከል አንዱ ጋቶች ነው። ተጫዋቹ በጨዋታው በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የተዋጣለት ሆኖ አሳልፏል። በተለይ ደግሞ የተጋጣሚ ተጫዋቾች የኳስ ቅብብሎችን እያቋረጠ የሚያስጀምራቸው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ለቡድኑ ወሳኝ ነበሩ። በተጨማሪም በተከላካዮች እና አማካዮች መካከል ባለው ቦታ እየገባ ኳሶችን ከርቀት የሚሞክርበት እና ለቡድን አጋሮቹ የሚያመቻችበት መንገድ አድናቆት የሚያስቸረው ነበሩ።

ዮናስ ገረመው (ሲዳማ ቡና)

ሲዳማ ቡናን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ መልካም እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው አማካዩ ቡድኑ ሀዋሳ ከተማን በረታበት ጨዋታ ላይ የማጥቃት እንቅስቃሴ በማስጀመር ረገድ ውጤታማ ምሽት ያሳለፈ ሲሆን የአማካይ ክፍል የበላይነት እንዲኖራቸው የነበረው ሚናም ከፍተኛ ነበር። በጭቃማው ሜዳ ላይ በርካታ ቦታዎችን በማካለል ጥሩ የተንቀሳቀሰው ዮናስ በሳምኝቱ ምርጥ ቡድን ሲካተት ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከታዩ እና ምርጥ ቡድን ውስጥ ከተካተቱ ተጫዋቾች መካከል የቸርነት መኖር ብዙም የሚያስገርም እና የሚያጨቃጭቅ አይደለም። ምክንያቱም ከጨዋታ ጨዋታ ተመልካቾችን እያስደመመ የመጣው ቸርነት ቡድኑ ጊዮርጊስ ላይ ጣፋጭ ድል ሲቀዳጅ የነበረው ሚላ ላቅ ያለ ስለነበር። በተለይም ተጫዋቹ የቡድኑን ሞራል እጅግ ከፍ ያደረገችው የስንታየሁ መንግስቱ የመጀመሪያ ጎል እንድትቆጠር የመጨረሻውን ኳስ ያመቻቸበት መንገድ ድንቅ ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በዛ ጭቃማ ሜዳ ኳሶችን እየገፋ በመስመር ላይ ሲፈጥረው የነበረው አደጋ ለጊዮርጊስ ተጫዋቾች የራስ ምታት ነበር።

በዛብህ መለዮ (ፋሲል ከነማ)

በፋሲል ከነማ አሰላለፍ እና የጨዋታ ምርጫ ውስጥ የራሱን ቦታ ያገኘው በዛብህ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን ዳግም አስመስክሯል። በአዳማው ጨዋታ የቡድኑን ድል ያረጋገጠች ድንቅ ጎል ከማስቆጠሩ ባለፈ ሱራፌል ዳኛቸው በቅጣት ባልነበረበት ጨዋታ የቡድኑን የፈጠራ ኃላፊነት ከመከወኑ ባለፈ በትጋት የመከላከል ሽግግሩ ላይም ተሳታፊ ሆነ ይታይ ነበር።

ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)

የፋሲል ከነማው የመስመር አጥቂ ታታሪነት አሁንም እንደቀጠለ ነው። የቡድኑ የማሸነፍ ሥነ ልቦና መገለጫ የሆነው ሽመክት አዳማ ከተማን 2-1 ባሸነፉበት ጨዋታ ከመስመር በመነሳት የቡድኑ የማጥቃት ሂደት ሲያቀላጥፍ ውሏል። በተለይም እጅግ አስፈላጊ የነበረችው የሙጂብ ቃሲምን ጎል ከኳስ ጋር በተከላካዮች መሀል ሾልኮ ያመቻቸበት መንገድ ልዩ ነበር።

አጥቂዎች

ኦኪኪ አፎላቢ (ሲዳማ ቡና)

በሲዳማ ያለመውረድ ትግል ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተወጣ ያለው ናይጄሪያዊው አጥቂ በ20ኛውም ሳምንት ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሲዳማ ቡናን ቀዳሚ ያደረገው የማማዱ ሲዲቤ ጎል ሲቆጠርም መነሻ የነበረው አፎላቢ በግራ መስመር በመግባት አክርሮ የመታው እና በሶሆሆ ሜንሳህ የዳነው ኳስ ነበር። በሁለቱ ግቦች ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከማድረጉ ባለፈ ኦኪኪ በጨዋታው የሀዋሳን የኋላ ክፍል ሲፈትን አምሽቷል።

ስንታየሁ መንግሥቱ (ወላይታ ድቻ)

እንደ ቸርነት ሁሉ በየጨዋታ ሳምንቱ የሚያስገርም ብቃት የሚያሳየው ሌላኛው ተጫዋች ስንታየሁ መንግስቱ ነው። ቁመታሙ የመሐል አጥቂ ዘለግ ያለ አካላዊ ቁመናውን ተጠቅሞ ከሚያደርጋቸው የአየር ላይ ፍልሚያዎች በተጨማሪ ከኳስ ጋር ያለው ፍጥነት ለተከላካዮች ፈተና ሆኗል። ከምንም በላይ ደግሞ ጎል ፊት አይምሬ መሆኑ የድቻን የፊት መስመር አስሎታል። በጊዮርጊሱ ጨዋታም ቡድኑ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ ሁለት ኳሶችን ከመረብ አገናኝቷል። ይህንን ተከትሎ የምርጥ ቡድናችን አጋፋሪ አድርገነዋል።

አሰልጣኝ – ዳዊት ሀብታሙ (ወላይታ ድቻ)

የወላይታ ድቻው ምክትል አሰልጣኝ ለሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች የአሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው አለመኖርን ተከትሎ የወሰዱትን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥተዋል። በተለይም በዚህ ሳምንት ወላይታ ድቻ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲረታ እንደወትሮው ሁሉ በተጋጋለ መንፈስ ጨዋታውን ከከወነው ቡድን ጀርባ ጥሩ አመራር በመስጠት እና ውጤታማ ቅያሪዎችን በማድረግ ምክትል አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ ላቅ ያለ ሚና ነበራቸው። በምክትል አሰልጣኝነት የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሆነው የተመረጡ የመጀመርያው መሆንም ችለዋል።

ተጠባባቂዎች

መሐመድ ሙንታሪ (ሀዲያ ሆሳዕና)
ሥዩም ተስፋዬ (ጅማ አባ ጅፋር)
አሌክስ አሙዙ (ጅማ አባ ጅፋር)
በረከት ወልዴ (ወላይታ ድቻ)
ዋለልኝ ገብሬ (ጅማ አባ ጅፋር)
ሰይፈ ዛኪር (አዳማ ከተማ)
ዱሬሳ ሹቢሳ (ሰበታ ከተማ)
ማማዱ ሲዲቤ (ሲዳማ ቡና)


© ሶከር ኢትዮጵያ