ወደ ከፍተኛ ሊግ የሚያድጉ ስድስት ቡድኖች የሚለዩበት የ2013 የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በአዳማ ከተማ ሲጀምር ሰንዳፋ በኬ፣ ዳሞት እና ድሬዳዋ ፖሊስ ድል ቀንቷቸዋል። ሞጆ እና ጎጃም ደ/ማርቆስ ነጥብ ተጋርተዋል።
አስራ ስድስት ቡድኖች በአራት ምድብ ተከፍለው ወደ ከፍተኛ ሊግ ለማደግ የሚካሄደው ዓመታዊው የአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በአዳማ ከተማ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። አቶ ኢሳይያስ ጅራ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት እና አቶ ባህሩ ጥላሁን የፅህፈት ቤት ኃላፊ በክብር እንግድነት ተገኝተው የውድድሩ መጀመርን ያበሰሩ ሲሆን በዛሬው የመክፈቻ ጨዋታ ሰንዳፋ በኬ ከጎፋ ባሬንቼ ያደረጉት ጨዋታ በሰንዳፋ በኬ 3–2 አሸናፊነት ተጠናቋል። በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው የሁለቱም ቡድኖች ስብስብ ጥሩ ፍክክር አስመልክቶን ሊጠናቀቅ ችሏል።
በጨዋታው ገና ጅማሬ ላይ የማጠቃለያው ውድድር የመጀመርያው አስቆጣሪ በመሆን ስሙን ያስመዘገበው የሰንዳፋ በኬ አጥቂ እና በዕለቱ ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቅዱስ ተስፋዬ በጥሩ ሁኔታ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ለውድድሩ ተሳታፊዎች ያልጠበቁት ክስተት በሚመስል ሁኔታ መልካም የሚንቀሳቀስ ቡድን መሆናቸውን ያሳዩት ሰንዳፋ በኬዎች ባለ ግራ እግሩ እና ተፈጥሯዊ ክህሎት እንዳለው ተቀይሮ እስኪወጣ ድረስ ሲያስመለክተን በቆየው አቤል ታምራት አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል።
በ20 ደቂቃ ውስጥ በተከላካዮቻቸው መዘናጋት ሁለት ጎል መቆጠሩ ድንጋጤ ውስጥ የገቡት የጎፋ ባሬንቺው አሰልጣኝ የቀድሞ አርባምንጭ ከተማ ተጫዋች መኮንን ገላነህ (ዊሀ) ሁለት ተከላካዮችን ቀይረው በምትኩ በማስገባት በተወሰነ መልኩ ክፍተቱን ለመድፈን ጥረት አድርገዋል። ግልፅ የማግባት የጎል አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የተቸገሩት ጎፋ ባሬንቺዎች ወደ ዕረፍት መዳረሻ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በተከላካዮች የተደረበውን ቴዎድሮስ ደበበ አግኝቶ ወደ ጎልነት በመቀየር የጎል መጠናቸውን አጥብበው የነበረ ቢሆንም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሬ ላይ ሰንዳፋ በኬዎች በመልሶ ማጥቃት የዕለቱ ኮከብ ተጫዋች ቅዱስ ተስፋዬ ከግራ መስመር የተሻገረለትን በአስደናቂ ሁኔታ የተረከዝ ጎል አስቆጥሮ ውጤት ለመቀልበስ ተነቃቅተው የመጡትን ጎፋ ባሬቺዎችን ቅንቅስቃሴ አቀዝቅዞታል።
ከነበራቸው ጥሩ የማጥቃት መንገድ እየወረዱ ውጤት ለማስጠበቅ እያፈገፈጉ የመጡት ሰንዳፋዎች ጎፋዎች ብልጫ እንዲወስዱባቸው በመፍቀዳቸው በተደጋጋሚ በተለይ የቀይ መስመር አጥቂ በሆነው እንደሻው አማካኝነት የሚጣሉ ኳሶች አጥቂዎቹ መጠቀም አልቻሉም እንጂ አደጋ መፍጠር ችለው ነበር። ይሁን እንጂ የመጀመርያወረን ጎል ባስቆጠሩበት መንገድ በሰንዳፋ ተከላካዮች ስህተት ሳጥን ውስጥ ተደርቦ የቀረውን ኳስ አንዱዓለም በቀለ አግኝቶ ለጎፋ ሁለተኛ ጎል ቢያስቆጥርም ውጤቱን መቀየር ሳይችል ቀርቶ ጨዋታው በሰንዳፋ በኬ 3–2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አምስት ሰዓት በቀጠለው የዕለቱ ሁለተኛ ጫዋታ በሞጆ ከተማ እና ጎጃም ደ/ማርቆስ መካከል ተካሂዶ በሁሉም ረገድ ጠንካራ የመሸናነፍ ፉክክር ታይቶበት በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ምንም እንኳ የመጀመርያ አጋማሽ ጎል ያልተቆጠረበት ሆኖ ቢጠናቀቅም የጨዋታው እንቅስቃሴ ሳቢ ነበር። በተለይ በወጣት ተጫዋቾች የተገነባው ሞጆ ከተማዎች በምስጋናው ግርማ እና አቤል ማሙሽ አማካኝነት የጎል እድል ቢፈጥሩም የጎጃም ደ/ማርቆስ ግብጠባቂ የሆነውና በብዙ ክለቦች ሲጫወት የምናቀው ዘውዱ መሰፍን አማካኝነት ይመክንባቸው ነበር። በአንፃሩ ጎጃም ደ/ማርቆሶች በተለያዩ ክለቦች የምናውቃቸው ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በርከት ብለው የሚገኙ በመሆናቸው ጥንቃቄ ያለው አጨዋወትን በመከተል አጥቂዎቻቸውን መሠረት ያድጉ ረጃጅም ኳሶችን ቢጠቀሙም ብዙም የተሳኩ አልነበረም።
ከዕረፍት መልስ የነበረው የጥንቃቄ አጨዋወት ከፈት ብሎ መታየቱ ጎሎች እንድንመለከት ዕድል የፈጠረ ሲሆን ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ መሆን የቻሉት ሞጆዎች ነበሩ። አቤል ማሙሽ ባስቆጠራት ጎል መምራት የጀመሩት ሞጆዎች ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ቢፈጥሩም አሁንም ልምድ ባለው ግብጠባቂ ዘውዱ መስፍን በአስደናቂ ሁኔታ አምክኖባቸዋል። በቀኝ መሰረመር አስፍቶ በሚቀበለው ኳስ ተከላካዮችን አጥብቦ በማለፍ ድንቅ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ወጣቱ ተጫዋች አብርሀም አሰፋ ጎጃም ደ/ማርቆስ በኩል የሚፈጥረው ጫና ተሳክቶ ከመዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ትዕዛዙ ደ/ማርቆስን አቻ በማድረግ ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከሰዓት በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ፖሊስ በጫላ አብዱራህማን ብቸኛ ጎል ሾኔ ከተማን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ዳሞት ከተማ በሙሉጌታ ካሣሁን አማካኝነት ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ቡራዩ ከተማን ማሸነፍ ችሏል።
የነገ ጨዋታዎች
03:00 ሐረር ከተማ ከ ጉለሌ
05:00 አወረሥኮድ ከ አንቦ ከተማ
08:00 ኤጀሬ ከ አዲስ ከተማ
10:00 እንጅባራ ከተማ ከ ጎባ ከተማ
© ሶከር ኢትዮጵያ