ፋሲል ከነማ የሊጉ አሸናፊ መሆኑ በይፋ በተረጋገጠበት የ22ኛ የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸውን ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን ክፍል ናቸው።
👉የዐፄዎቹ የዓመታት ህልም ዕውን ሆኗል
ፋሲል ከነማዎች ከ2011 አንስቶ ጠንካራ ቡድን በመገንባት ሲያልሙት የነበረው የፕሪምየር ሊጉ ዋንጫ በስተመጨረሻ መዳረሻው ጎንደር ከተማ መሆኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በይፋ ተረጋግጧል።
በሊጉ ከታዩ ጠንካራ ስብስቦች አንዱ የሆነው የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ቡድን እጅግ ወጥ የሆነ የውድድር ጊዜ በማሳለፍ ተጋጣሚዎቹን ከመርታቱ በተጨማሪ አስቸጋሪ የጨዋታ ቀናት ባሳለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ የማሸነፊያ መላን የማያጣ ቡድን መሆኑን አሳይቷል። በተከታታዮቹ ተደጋጋሚ ነጥብ መጣል ሳቢያ በእጁ የነበረውን ሰፊ የነጥብ ልዩነት አስጠብቆ ዋንጫውን በይፋ የሚያረጋግጥበትን ቀን ሲጠባበቅ የቆየው ፋሲል በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱን ተከትሎ ወደ ሜዳ ገብቶ ጨዋታውን ሳይከውን የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል።
የሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ባረጋገጡበት ዕለት ባረፉበት ሆቴል በከፍተኛ ስሜት ደስታቸውን ሲገልፁ የተስተዋሉት የፋሲል ከነማ የቡድን አባላት በዛው ስሜት ውስጥ ሆነው ከሁለት ቀናት በኋላ የመውረድ ስጋት ያጠላበት ወልቂጤ ከተማን ገጥመው በሽመክት ጉግሳ ብቸኛ ግብ ደስታቸውን ይበልጥ ወደ ላቀ ከፍታ የወሰደ ድልን ማስመዝገብ ችለዋል።
ፋሲል ከነማዎች የሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ካረጋገጡ ወዲህ ባደረጉት የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ ወደ ሜዳ ሲገቡ የወልቂጤ ተጫዋቾች በሁለት ረድፍ ተደርድረው በክብር ወደ ሜዳ ያስገቧቸው የመጀመሪያ ጨዋታ ሲሆን በቀጣይ ባሏቸው ሦስት ጨዋታዎች እንደዚሁ ተጋጣሚ ቡድኖች ይህን ሲከውኑ የሚስተዋል ይሆናል።
👉 ከመውረድ ስጋት ነፃ የመሰለ እንቅስቃሴ ያሳዩት ድሬዳዋ እና አዳማ ከተማ
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመክፈቻ መርሐግብር በነበረው እና በበርካቶች ዘንድ ላለመውረድ በሚደረገው ትንንቅ ላይ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል ተብሎ የተጠበቀው የድሬዳዋ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ እጅግ ደካማ ከሆነ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር ለሁለቱም ቡድኖች እምብዛም ዋጋ በሌለው የአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።
በንፅፅር የአዳማ ከተማ የመውረድ ነገር ወደ እርግጠኝነቱ የቀረበ ቢመስልም አሁንም ቢሆን በሒሳባዊ ስሌት በሊጉ ሊቆዩበት የሚችሉበት እድል አለ። በተጨማሪም ቢወርድ እንኳ ይዞ የሚያጠናቅቀው ደረጃ በትግራይ ክለቦች እጣፈንታ ላይ የተመሰረተው የመለያ ጨዋታ የመሳተፍ ዕድል ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል። በሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ይዞ የሚያጠናቅቀው ቡድን በመለያ ጨዋታ ሊሳተፍ የሚችለው ሦስቱም የትግራይ ክለቦች ለቀጣይ ዓመት የማይሳተፉ ከሆነ ብቻ እንደሆነ ከዚህ ቀደም በተሰጠው መግለጫ እንደመብራራቱ ከመውረድ ስጋት ከመላቀቅ በተጨማሪ ደረጃን ማሻሻል ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከተማ የተረዳው አይመስልም።
በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ ጋር በተጋራት አንድ ነጥብ አጠቃላይ ነጥቡን ወደ 22 ከፍ በማድረግ ወደ ዘጠነኛ ደረጃ ከፍ ማለት ቢችልም በደረጃ ሰንጠረዡ በአስራአንደኛ ከሚገኘው ሲዳማ ቡና እስከ ዘጠነኛ ደረጃ ባሉት ሦስት ክለቦች መካከል ያለው የነጥብ ልዩነት አንድ በመሆኑ አሁንም ሦስተኛውን የሊጉን ወራጅ ቡድን ከድሬዳዋ፣ ሲዳማ እና ወልቂጤ አንዱ መሆኑ አይቀሬ ነው። (ጅማ እና አዳማ ወደኋላ መቅረታቸው ታሳቢ ተደርጎ)
በየራሳቸው አውድ ውጤቱ ያስፈልጋቸው የነበሩት ሁለቱ ቡድኖች ከጨዋታው ጅማሮ በፊት አሰልጣኞቻቸው እንደገለፁት በተቻለ መጠን አጥቅተው በመጫወት ጥሩ ፉክክር ይታይበታል ያሉትን ጨዋታ የማሸነፍ ፍላጎት እንደነበራቸው ቢያስረዱም ሜዳ ላይ የተመለከትነው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው።
እርግጥ በዚህ ጨዋታ ከማሸነፋቸው ይልቅ በጥቃቅን ስህተቶች ቢሸነፉ በሊጉ እህል ውሃቸው ላይ የሚፈጠረውን በማሰብ ሁለቱም ቡድኖች በተወሰነ መልኩ ጥንቃቄን ጨምረው መጫወታቸው ትርጉም ቢሰጥም በሁለቱም አጋማሾች ይህ ነው የሚባሉ የጠሩ ማጥቃቶችን ብሎም ሙሉ ሦስት ነጥብ ለማሳካት መጣደፎችን ሳያስመለክቱን ቀርተዋል። ይባስ ብሎ በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በሁለቱም ቡድኖች ሜዳ ላይ ያስተዋልነው ነገር ጨዋታው በሊጉ መቆየታቸው ባረጋገጡ ሁለት ቡድኖች መካከል የሚደረግ እንጂ በሊጉ ለመቆየት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ የሚገኙ ቡድኖች መካከል የሚደረግ አይመስልም ነበር።
ሊጉ ሊገባደድ የአራት የጨዋታ ሳምንታት እድሜ በቀረው በዚህ ወቅት በሊጉ የመውረድ እንዲሁም የሁለተኝነት ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ የሚፎካከሩ ቡድኖች በተለይ ሁሉንም ጨዋታዎች እንደ ፍፃሜ ጨዋታ በመመልከት ያላቸው ሁሉ ሜዳ ላይ ሰጥተው ውጤታማ ለመሆን መጣር እንጂ ለጥንቃቄ አጨዋወት ከልክ ያለፈ ትኩረት መስጠት ለቡድኖቹ የሚሰጠው ጥቅም አናሳ ከመሆኑ አንፃር ቡድኖች ሊያስቡበት ይገባል።
👉መላቅጡ የጠፋው ሀዲያ ሆሳዕና
በ22ኛ የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና ከሀዋሳ ከተማ ከሚያደርጉት ጨዋታ ቀናት አስቀድሞ አስራ አምስት የሚጠጉ የቡድኑ ተጫዋቾች የፊርማ ክፍያችን እስካሁን አልተፈፀምልንም በሚል የኮቪድ ምርመራ ላለማድረግ ብሎም ውድድሩ ወደሚካሄድበት ሀዋሳ ከተማ ላለማወራት የመወሰናቸው ዜና እጅግ አነጋጋሪ ነበር።
ተጫዋቾቹ በአቋማቸው በመፅናታቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሀዋሳ ከተማን ያለ ምንም ተጠባባቂ ተጫዋች በአስር ተጫዋቾች ብቻ ለመግጠም ሲገደዱ ከአስሩ የቡድኑ ተጫዋቾች ደግሞ አምስቱ ለቡድናቸው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉ መሆናቸው ትኩረትን የሚስብ ነበር።
ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ በአስር ተጫዋቾች ጨዋታውን የጀመረው ቡድኑ ገና ከጅማሮው ግብ ባስተናገደበት የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ተዘራ አቡቴ ጉዳት በማስተናገዱ ሳቢያ ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ ሁለተኛውን አጋማሽ በዘጠኝ ተጫዋቾች ለመጨረስ ተገደዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች በድፍረት ወደ ሀዋሳ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ያደረጉት ሆሳዕናዎች በጨዋታው በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር እንደመጫወታቸው ይህን ጉድለት ለመሙላት ተጫዋቾቹ ከፍ ያለ ጉልበትን አውጥተው ለመጫወት መገደዳቸው በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ቡድኑ በአካላዊ መመዘኛዎች እጅጉን ተዳክሞ በዚህም የተነሳ በተፈጠረ የትኩረት ማነስ ሳቢያ ተጨማሪ ግቦችን አስተናግደው ቢሸነፍም የቡድኑ ተጫዋቾች ሳጥናቸው ለመከላከል ያሳዩት ጥረት የሚደነቅ ነበር።
ሀዲያ ሆሳዕና በቀደሙት ጥቂት የውድድር ዘመናት ጅማ አባጅፋር ጋር ተያይዞ ይነሱበት እንደነበረው ወቀሳ ተደጋጋሚ አለመግባባቶች ከተጫዋቾቹ ጋር መፍጠሩን ቀጥሎበታል። በድሬዳዋው ውድድር የመጀመሪያውን ጨዋታ ከአዳማ ከተማ ጋር ከማድረጋቸው አስቀድሞ እንዲሁ ተጫዋቾች ጋር የተፈጠረ አለመግባባት በአለቀ ሰዓት እልባት አግኝቶ በቀጥታ ከአውሮፕላን እንደወረዱ ጨዋታ ለማድረግ ሲገደዱ ይህ አስተዳደራዊ ችግር ሳይስተካከል ውሎ አድሮ በጎዶሎ ተጫዋች ያለ ተጠባባቂ ተጫዋች እስመጫወት አድርሶታል።
በሀዲያ ሆሳዕና ታሪክ ዘንድሮ እጅግ የተሻለን የውድድር ዘመን እያሳለፈ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የቡድኑን መንፈስ የሚረብሹ መሰል ተደጋጋሚ ክስተቶች መፈጠራቸው ቡድኑ አሁንም ቢሆን የማሳካት እድል ወዳለው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የሚያስገኝለትን የሁለተኛ ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ የሚያደርገው ጉዞ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖችን እያሳደረ ይገኛል። በመሆኑም የክለቡ አመራሮች እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ በቀሩት ጥቂት ጨዋታዎች የቡድኑን ጉዞ በተሻለ መደላድል እንዲሄድ ለማድረግ መጣር ይኖርባቸዋል።
ቡድኑ በትናንትናው ዕለት አስር ተጫዋቾችን ወደዋናው ቡድን በማሳደግ ልምምድ እንዲሰሩ መወሰኑ የሚታወቅ ሲሆን ከተጫዋቾቹ ጋር ያለው ፍጥጫ ረግቦ ወደ ቡድኑ ካልተመለሱ በአዳዲስ ተጫዋቾች በተሞላ ስብስብ የውድድር ዓመቱን የሚያጠናቅቅ ይሆናል።
👉 ስልታዊው ወላይታ ድቻ
መጥፎ የሚባል አጀማመርን በሊጉ ያደረጉት ወላይታ ድቻ ከአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኃላ ቡድኑ ላይ በግልፅ የሚታዩ መሻሻሎችን እየተመለከትን ይገኛል። በዚህም የወራጅነት ስጋት አንዣቦበት የነበረው ቡድኑ አሁን ላይ በሊጉ ከመጀመሪያ አራት ቡድኖች ተርታ ሆነው ስለመጨረስ እያለሙ ይገኛል። ታድያ ከዚህ የማንሰራራት ጉዞ ጀርባ የቡድኑ ስልታዊ አቀራረብ ወሳኝ ድርሻን የሚይዝ ነው።
በተለይ በድሬዳዋው የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲረቱ እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ሲጋሩ ቡድኑ በዋነኝነት ተጋጣሚዎቹን በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስን እንደልብ እንዲቆጣጠሩ በመፍቀድ በተቃራኒው እነሱ ደግሞ በሁለት መስመሮች ወደ ራሳቸው የሜዳ አጋማሽ አፈግፍገው በጥንቃቄ መከላከልን ይመርጣሉ። በዚህ ሒደት የበለጠ ኳሱን የሚይዘው ቡድን ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር በተለይ ግብ ማስቆጠር ካልቻሉ ኳስ ቁጥጥራቸውን ወደ ግብ መቀየር ባለመቻላቸው መሰላቸት ውስጥ በመግባት በቁጥር በርከት ብለው ኃላፊነት ወስደው ማጥቃትን መምረጣቸው አይቀሬ ነው።
በዚህ ሒደት በተለይ በሁለተኛ አጋማሾች ድቻዎች ከመከላከሉ ባለፈ ፈጥን ያሉ የመልሶ ማጥቃቶችን የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች በሙሉ አቅም ለማጥቃተሰ ከመፈለጋቸው ጋር በሚፈጠሩ ከከላካዮች ጀርባ በሚገኙ ክፍት ሜዳዎችን ላይ በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ ይስተዋላል ፤ ይህም በመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቀዝ ባለ አጨዋወት ተጋጣሚን በማሰልቸት በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ ከፍ ባለ ፍጥነት መልሶ ማጥቃቶችን ለመሰንዘር የሚያደርጉት ጥረት ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል።
👉ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሦስት ነጥቦች በላይ
በዘንድሮው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከቀደሙት ዓመታት በተለየ የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር አለመኖሩን ተከትሎ ቡድኖች በኢትዮጵያ ዋንጫ በኩል ያገኙት የነበረው የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ለዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ በሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቀው ቡድን ይህን ተሳትፎ ማሳካት መቻሉ ከሊጉ አሸናፊነት ባልተናነሰ ለሁለተኛ ደረጃ የሚደረገው ፉክክር እጅግ አጓጊ መልክን ይዟል።
ከ23ኛ የጨዋታ ሳምንት በኃላ ባለው የደረጃ ሰንጠረዥ መሠረት ኢትዮጵያ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና ባህርዳር ከተማ እንደቅደም ተከተላቸው ይህን የሁለተኛ ደረጃ ይዞ የማጠናቀቅ እድል አላቸው። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን ከባህር ዳር ከተማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ በዚህ ፉክክር ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ አንፃር ነበር በጉጉት የተጠበቀው።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሁለቱም አጋማሾች የተሻለ የማሸነፍ ፍላጎትን ባሳየበት በዚህ ጨዋታ በሁለተኛው አጋማሽ በከነዓን ማርክነህ እና አብዱልከሪም መሐመድ ባስቆጠሯቸው ግቦች አሸንፈው መውጣት ችለዋል። ይህን ውጤት ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነጥባቸውን ወደ 34 በማሳደግ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ በማድረግ በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችለዋል። በተቃራኒው ሁነኛ ተፎካካሪያቸው የሆነውን ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በመሸነፉ በ31 ነጥቦች በመርጋት ወደ አምስተኛ ደረጃ ለመንሸራተት ተገዷል።
© ሶከር ኢትዮጵያ