ሞሮኮ ለምታስተናግደው የ2022 የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የሚያልፉ ቡድኖች የሚለዩበት የምድብ ድልድል ከደቂቃዎች በፊት ወጥቷል።
በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ዓመት በሞሮኮ ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የማጣሪያ ተጋጣሚው ሲጠባበቅ ቆይቷል። በዛሬው ዕለትም ካፍ በቀድሞዋ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ናዲኔ ጋዚ አማካኝነት የማጣሪያ ድልድሉን በግብፅ ርዕሰ መዲና ካይሮ አውጥቷል። በዚህም መሰረት በቋት አንድ የሴካፋ ዞን ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንም በመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ከዩጋንዳ ጋር እንደሚጫወት ታውቋል።
ካፍ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረትም ሉሲዎቹ ከግንቦት 30- ሰኔ 7 ባለው ጊዜ የደርሶ መልስ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል። በደርሶ መልሱ አሸናፊ የሚሆነው ቡድንም የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታውን ከኬንያ እና ደቡብ ሱዳን አሸናፊ ከጥቅምት 8-19 (2014) ባለው ጊዜ የሚያደርግ ይሆናል።
© ሶከር ኢትዮጵያ