በኢትዮጵያ ለሚደረገው የሴካፋ ውድድር ዝግጅቱን እያደረገ ከሚገኘው የዋልያው ስብስብ በዛሬው ዕለት ሰባት ተጫዋቾች መቀነሳቸው ታውቋል።
ከቀናት በፊት ለምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ (ሴካፋ) ውድድር ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ አድርጎ ዝግጅቱን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ማድረጉን ቀደም ብለን መዘገባችን ይታወቃል። የቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተም በተለያዩ ምክንያቶች ከቡድኑ ገለል ካሉ ተጫዋቾች ውጪ ያለውን ስብስብ በካፍ የልህቀት ማዕከል ልምምድ ሲያሰሩ የቆዩ ሲሆን አሁን ሰባት ተጫዋቾችን መቀነሳቸው ሰምተናል።
በዚህም በህመም ምክንያት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ እና ዓለምብርሀን ይግዛው (ከፋሲል ከነማ) ፣ በዛሬው ጨዋታ ጉዳት የደረሰበት አማኑኤል ተረፉ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ) እንዲሁም ደስታ ዋሚሾ (ከሀዲያ ሆሳዕና)፣ ኤርሚያስ በላይ (ከአርባምንጭ ከተማ) ፣ መሐመድኑር ናስር እና ታምራት ዳኜ (ከኢትዮጵያ መድን) ከቡድኑ መቀነሳቸውን አረጋግጠናል።
በተያያዘ ዜና ብሔራዊ ቡድኑ በመጪው ሳምንት ሴካፋ ወደሚደረግበት ባህር ዳር ከተማ እንደሚጓዝ ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ተነግሮናል።