የአሠልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-0 ወልቂጤ ከተማ

ያለ ጎል አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል።

ሙሉጌታ ምህረት – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው?

መጀመሪያ እንዳሰብነው ጥሩ ለመጫወት ሞክረን ነበር። በተለይ ደግሞ ከእረፍት በፊት። ከእረፍት በኋላ ደግሞ ሜዳው እኛ በምንፈልገው መንገድ እንዳንጫወት አስቸግሮናል። በጨዋታው ዋናው ምርጫችን ደረጃችንን ከፍ ለማድረግ ነበር። ግን ሁኔታዎቹ ሲታዩ አሁን ያገኘነውም ነጥብ ጥሩ ነው።

በተከታታይ ካለመውረድ ከሚጫወቱ ቡድኖች ጋር ጨዋታ ስለማድረጋቸው?

ይሄ ተፅዕኖ ያደርጋል። ላለመውረድ የሚጫወት ቡድን ያለውን አቅም አውጥቶ ነው የሚጫወተው። ቢሆንም ግን ለሁሉም ቡድኖች አንድ አይነት ዝግጅት ስለተዘጋጀን የተለየ ነገር የለውም። የጭንቅላት ጉዳይ ነው። ዛሬ ከምን ጊዜውም በላይ ከሽንፈት ማገገም ስለሆነ ፍላጎታችን ጨዋታው ለእኛ ያስፈልገን ነበር። በዚህም ደረጃ ነበር የተነጋገርነው። ሆኖም ግን አንዷም ነጥብ ለእኛ ጥሩ ነች።

ሲሳይ አብርሃ – ወልቂጤ ከተማ

ስለ ጨዋታው

ማሸነፍ ነበረብን። አቅደን የመጣነውም ያን ነበር። ምክንያቱም አቻ አይጠቅመንም። አቻ ከመሸነፍ የምትለየው ነገር አደለም። ጠዋት በነበረው ጨዋታም ሲዳማ ቡና ነጥብ ስለጣለ እኛ ብናሸንፍ ከእነሱ እና ከድሬዳዋ ጋር ያለንን የነጥብ ልዩነት አንድ ማድረግ እንችል ነበር። ይህንንም ተነጋግረን ነበር የገባነው። ግን ዝናብ መዝነቡም የጎዳን ይመስለኛል። ምክንያቱም እኛ ከኳስ ጋር በተያያዘ ነገር ነው ጥሩ የነበርነው። ዝናቡ ሲዘንብ ግን የተወሰኑ ተጫዋቾች ላይ ተፅዕኖ አመጣ። ምክንያቱም ኳሶችም ስለማይሄዱ። በአጠቃላይ ግን ዛሬ በነበረን ተነሳሽነት ሦስት ነጥብ ይኖረናል ብዬ አስቤ ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ስለተጠቀማቸው ሁለት የተከላካይ አማካዮች?

በጨዋታው ሀብታሙ ወደ ፊት ጠጋ ብሎ እንዲጫወት ነበር ያሰብነው። ከዚህም በፊት ወልዲያ እያለ ከአጥቂ ጀርባ ነበር የሚጫወተው። ዛሬም እኛ ኳስ ስንይዝ ሀብታሙ አጥቂዎቹን እንዲደግፍ ነበር ያሰብነው። ልምምድ ላይም ይሄንን ነበር የሰራነው። 

ቡድኑ ለመትረፍ ስላለው ዕድል እና ስላለበት የስነ-ልቦና ደረጃ?

እኛ እስከ መጨረሻው ያለንን አሟጠን እንጠቀማለን። ተጫዋቾቼ ባለፈውም ተሸንፈው የነበራቸው ነገር ጥሩ ነበር። አሁንም ጀማል እያለቀሰ ነው የወጣው። ከድሬዳዋ ጋር በነበረው ጨዋታም ባለቀ ሰዓት ነበር ጎል ገብቶብን የተሸነፍነው። ያኔ አቻ እንኳን ብንወጣ ድሬዳዋንም እናስቀረው ነበር። ለዛሬውም ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣ ነበር። በቀሪዎቹም ሁለት ጨዋታዎች ግን ስድስት ነጥቦችን አግኝተን በሊጉ ለመቆየት እንሞክራለን።