ቅዱስ ጊዮርጊስ የዕግድ ውሳኔውን እንዲያነሳላቸው ተጫዋቾቹ ጠየቁ

የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ማኅበር የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅመዋል በማለት የእግድ ውሳኔ ካስተላለፈባቸው ተጫዋቾች መካከል ሁለቱ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሳምንታት በፊት የዲሲፕሊን ግድፈት ፈፅመዋል ያላቸው ጌታነህ ከበደ፣ አስቻለው ታመነ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ሙሉዓለም መስፍን “በሲሲቲቪ የተቀረፀውን ምስል እንዲሁም የክለቡ የልብ ደጋፊዎች የላኩትን አስተማማኝ ማስረጃዎች ተመልክቶ የክለቡን ስም፣ ክብር እና ዝና ለማስጠበቅ እንዲሁም የቀሪ ተጫዋቾችን ሰላም ለማረጋጋት እና በክለቡ የወጣውን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት በማድረግ አራቱም ተጫዋቾች እያንዳንዳቸው 20 ሺ ብር እንዲቀጡ እንዲሁም ተጫዋቾቹ ከክለቡ ጋር ያላቸው ስምምነት እስኪጠናቀቅ ድረስ ታግደው እንዲቆዩ” የሚል ውሳኔ መወሰኑ የሚታወስ ነው።

እገዳ ከተላለፈባቸው ተጫዋቾቸች መካከል ጌታነህ ከበደ እና ሙሉዓለም መስፍን ለክለቡ ባስገቡት ሁለት ገፅ ያለው ደብዳቤ በዋናነት “ከፍተኛ የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅመዋል ከተባለ አለ የተባለው የቪዲዮ ማስረጃ በግልፅ ሊቀርብ ይገባል። እኛ ተጠርተን በጉዳዩ ዙርያ ተጠይቀን ምላሽ ሳንሰጥ በቀረበብን አቤቱታ ብቻ የተጣለብን የገንዘብ ቅጣት እና የዕግድ ውሳኔ ተገቢ አይደለም። ከተፈቀደልን ሰዓት በላይ አርፍደን ወደ ሆቴል መግባታችን ስህተት በመሆኑ የተፀፀትን ሲሆን የታላቁ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ደጋፊዎችም ሆነ ስፖርት ቤተሰቡ እና የሥራ አመራር ቦርድ ያቀረብነውን አቤቱታ ከመረመረ በኃላ የተጣለብንን ቅጣት በይቅርታ እንዲያልፈን እንጠይቃለን።” የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ አስገብተዋል።

ተጫዋቾቹ ያስገቡት ደብዳቤ ከምን ደረሰ ስንል በክለቡ በኩል የሚመለከታቸውን አካለት ዝርዝር መረጃ እንዲሰጠን ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም ደብዳቤው ለክለቡ እንደደረሰው ማረጋገጥ ግን ችለናል።