በጅማ አባጅፋር እና ባህር ዳር ከተማ መካከል የተደረገው የረፋዱ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተገባዷል።
ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለዛሬው ጨዋታ የቀረቡት የጅማ አባጅፋሩ ዋና አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ከመጨረሻው ጨዋታቸው ምንም ለውጥ ሳያደርጉ የዛሬውን ጨዋታ ጀምረዋል። እንደ ጅማ ሁሉ አቻ ከተለያየ በኋላ ዛሬ ሜዳ የደረሰው ባህር ዳር ከተማ ከኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ሁለት ለውጦችን አድርጓል። በዚህም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ግብ ጠባቂው ፅዮን መርዕድ በሀሪሰን ሄሱ ቦታ እንዲሁም ባዬ ገዛኸኝን በወሰኑ ዓሊ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ገና አምስት ደቂቃ ሳይሆን ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች አድርገዋል። በቅድሚያም በረከት ጥጋቡ ከፍፁም ዓለሙ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ የመታው ሲሆም በመቀጠል ደግሞ ባዬ ገዛኸኝ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት ምንይሉ ወንድሙ ሞክሮ ነበር። ነገርግን ሁለቱም ተጫዋቾች የሞከሯቸው ኳሶች አቡበከር ኑሪን ብዙም ሳይፈትኑ መዳረሻቸው የግብ ዘቡ እቅፍ ውስጥ ሆኗል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በባህር ዳር በኩል ሲዘነዘሩ የነበሩ ጥቃቶችን በመመከት ያሳለፉት ጅማ አባጅፋሮች በ11ኛው ደቂቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሰው ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህ ደቂቃም ተመስገን ደረሰ ራሂም ኦስማኖ በግንባሩ ያቀበለውን ኳስ ወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ ሆኖ በማግኘት ወደ ግብ ቢመታውም ኳሱ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል።
የጨዋታውን የኃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የቀጠሉት ባህር ዳሮች ቀዳሚ የሚያደርጋቸውን ጎል ለማግኘት መታተር ይዘዋል። በ29ኛው ደቂቃም በረከት ጥጋቡ ከሳጥን ውጪ በድጋሜ ጥሩ ኳስ ሞክሮ በአቡበከር መክኖበታል። ቡድኑ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ዳግም የጅማን መረብ ለመፈተሽ ጥረዋል። በዚህ ደቂቃም ከርቀት የተላከውን ኳስ ለመመለስ የግብ ክልሉን ለቆ የወጣው አቡበከር ኑሪ የተፋውን ኳስ ሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ያገኘው ሳለዓምላክ ተገኘ ያገኘውን ኳስ በቀጥታ በመምታት ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። ነገርግን ስህተቱን ለማረም ለሁለተኛ ዕድል ያገኘው አቡበከር ኳሱን ተቆጣጥሮታል። አሁንም ግብ ለማስቆጠር መታተራቸውን የቀጠሉት ባህር ዳሮች በፈጣን ሽግግር ያገኙትን አጋጣሚ በሳለዓምላክ አማካኝነት ሞክረውት ተከላካዮች አውጥተውባቸዋል። አጋማሹ ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ፍቅረሚካኤል ሌላ ጥቃት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም ጥሩ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው አቡበከር ኳሱን አድኖታል። በማጥቃቱ ረገድ ያነሰ ተሳትፎ የነበራቸው ጅማ አባጅፋሮች በ44ኛው ደቂቃ ዋውንጎ ፕሪንስ በሞከረው ነገርግን ዒላማውን በሳተው ኳስ ጥቃት ፈፅመው ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ያለ ጎል አቻ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽም ባህር ዳሮች ኳስ በመያዝ ረገድ የተሻሉ ቢሆንም ጅማዎች ግን በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች ዕድሎችን በመፍጠር ጥሩ ነበሩ። በዚህም ቡድኑ ሁለት ሙከራዎችን በአስር ደቂቃዎች ልዩነት አድርጎ ባህር ዳርን አስደንግጧል። በቅድሚያም በ53ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ሥዩም ያሻገረውን ኳስ ኦስማኖ በግንባሩ ገጭቶ ጥቃት ቢፈፅምም ኳሱ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በመቀጠል ደግሞ በ63ኛው ደቂቃ ኦስማኖ በግሩም ሁኔታ ያሳፈለትን ኳስ ተመስገን ደረሰ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በቀጥታ ቢመታውም ኳሱ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቷል።
የኳስ ቁጥጥራቸውን በጎል ለማሳጀብ መታተር የቀጠሉት ባህር ዳሮች በ69ኛው ደቂቃ ፍፁም እና ባዬ አንድ ሁለት ተቀባብለው ፍፁም የመጨረሻውን ኳስ አሻግሮት ሳለዓምላክ ባልተጠቀመበት ኳስ አስቆጪ ዕድል አልፏቸዋል። በ75ኛው ደቂቃም በድጋሜ ግርማ ያሻገረውን የቅጣት ምት ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሰለሞን ወዴሳ ወደ ግብነት ለመቀየር ሞክሮ መክኖበታል። በተቃራኒው ጅማዎች ደግሞ ረጃጅም ኳሶችን እና የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን በመጠቀም መጫወት ቀጥለዋል። በ77ኛው ደቂቃ ላይ ግን ቡድኑ ሳላዓምላክ ተሳስቶ ዋውንጎ በሞከረው ያልታሰበ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃ ሲቀረው ደግሞ ባህር ዳር ከተማ መሪ ለመሆን እጅግ ተቃርቦ ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ የጅማ ተከላካዮች ሲመልሱት የጎሉ ጫፍ ላይ ሆኖ ያገኘው አፈወርቅ ኃይሉ እጅግ ወርቃማ የነበረችውን ዕድል አምክኗታል። የዕለቱ የመሐል ዳኛ ባህሩ ተካ ያሳዩት ጭማሪ ደቂቃ መጠናቀቂያ ላይ ደግሞ ባዬ የጨዋታውም የመጨረሻ ጥቃት ለመፈፀም ብቻውን ሲሮጥ ስዩም ተስፋዬ ይፋት ሰርቶበታል። በሰራው ጥፋትም የቀይ ካርድ አይቶ ከሜዳ ተሰናብቷል። ጥፋቱን ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ፍፁም ለመጠቀም ቢሞክርም አቡበከር መልሶታል። ጨዋታውም ያለ ጎል ተገባዷል።
ውጤቱን ተከትሎ መውረዳቸውን ቀድመው ያረጋገጡት ጅማ አባጅፋሮች ነጥባቸውን 15 በማድረስ 12ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል። የዛሬውን የአቻው ውጤት ተከትሎ በይፋ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ እንደማይኖራቸው ያረጋገጡት ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ በ33 ነጥቦች ያሉበት አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።