ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው ፅሁፋችን ሌሎች ትኩረት ያገኙ ነጥቦች ተካተውበታል።

👉 የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቦታ ፉክክር

የሊጉ አሸናፊነት ክብር በይፋ ወደ ፋሲል ከነማ ማምራቱ ተረጋጥጧል። ያለፉት ሳምንታት የዐፄዎቹ ጉዞ ክብሩን መጎናፀፋቸው የማይቀር መሆኑን ያሳየ በመሆኑ የብዙሀን ትኩረት ሁለተኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫውን ቦታ ማን ይይዛል የሚለው ነበር። ሆኖም በተከታታይ ሳምንታት በተመዘገቡ ውጤቶች የሚሳተፈውን ቡድን ከመለየት ይልቅ መጠባበቅ በሚመስል መልኩ አንዱም ነጥሮ አለመውጣቱ አስገራሚ ሆኗል። ቡድኖቹ ተጋጣሚዎቻቸውን ማሸነፍ ተስኗቸው ነጥባቸውን ከፍ ማድረግ ሳይችሉ ቢቆዩም በዚህ የጨዋታ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህር ዳርን በማሸነፍ ነጥቡን ማስጠጋቱ ይበልጥ ፉክክሩን ሳቢ እንዲሆን አድርጎታል።

ሊጠናቀቅ አራት ሳምንታት በቀሩት ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንድ ነጥብ ልዩነት ሁለተኛ እና ሦስተኛ ሲቀመጡ ሀዲያ ሆሳዕና በ3፣ ባህር ዳር ከተማ በ4 እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ በ5 ነጥቦች ከሁለተኛ ደረጃው ቦታ ርቀው በፉክክር ውስጥ ይገኛሉ።

በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከባህርዳር ከተማ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሀዲያ ሆሳዕና እና አዳማ ከተማ ጋር ጨዋታውን ሲያደርግ ከአራቱ ሁለቱ ቀጥተኛ የቦታው ተፎካካሪዎቹ፤ ሁለቱ ደግሞ ባለመውረድ ፉክክር ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች መሆናቸው ለቡናማዎቹ ጨዋታዎቹን ሊያከብዱ የሚችሉ ናቸው።

በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሲዳማ ቡና፣ ሀዲያ ሆሳዕና፣ አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ጋር የሚጫወት ሲሆን አንዱ ከቀጥተኛ ተፎካካሪ ሦስቱን ደግሞ ላለመውረድ ከሚፎካከሩ ቡድኖች ጋር የሚደያደርጋቸው መሆኑ እንደ ቡና ሁሉ ፈታኝ ሊሆኑበት የሚችሉ ናቸው።

በወሳኝ ሰዓት አስተዳደራዊ ችግር ውስጥ የገባው ሀዲያ ሆሳዕና በሜዳም ከሜዳ ውጪም እየተፈተነ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ይህን ቦታ ያሳካ ይሆን የሚለው ተጠባቂ ጉዳይ ነው። የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ “ከዚህ በኋላ የማይታሰብ ነው” ያሉት ሁለተኛ ደረጃን ለማግኘት ቡድኑ በቀጣይ ከሰበታ ከተማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ጋር ይፋለማል። በሜዳ ውጪ ምክንያቶች ያለ ወሳኝ ተጫዋቾቹ ሊገባ የሚችለው ቡድኑ በትኩረት እና የተሟላ ብቃት ጨዋታዎችን ያደርጋል የሚለው አጠያያቂ ነው።

በአራት እና አምስት ነጥቦች ከሁለተኛ ደረጃው የራቁት ባህር ዳር ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ቦታውን ለማግኘት ከራሳቸው ስኬት ውጪ የሌሎቹን ውጤት የሚጠብቁ ይሆናል። በተጨማሪም ከላይ ከተጠቀሱት ሦስቱ ቡድኖች ጋር ጨዋታ የማያደርጉ በመሆናቸው እድላቸውን በራሳቸው የመወሰናቸው ጉዳይ ዝቅተኛ ነው። በተለይ በደካማ አቋም ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ የቀረው ሦስት ጨዋታ ብቻ መሆኑ በፉክክሩ ላይ ወደኋላ እንዲቀር ሊያደርገው ይችላል።

👉 በግብ ድርቅ የተመታው የጨዋታ ሳምንት

በ22ኛ ጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመጀመሪያ የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዘመኑ ከተጀመረ ወዲህ እጅግ አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት የጨዋታ ሳምንት ሆኖ አልፏል።

በድምሩ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ስድስት ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ከስድስቱ ጨዋታዎች ግማሹ ያለግብ በአቻ ውጤት ከመጠናቀቃቸው በተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የቻሉ ቡድኖች ሦስት ብቻ ናቸው። ይህም በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ በ9ኛ የጨዋታ ሳምንት ከተቆጠረው ጎል በሁለት ግቦች አንሶ በሊጉ ዝቅተኛ ግብ የተመዘገበበት የጨዋታ ሳምንት ሆኖ ተመዝግቧል

ለወትሮው በሊጉ የተለመደው የውድድር ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ የሚቆጠሩ ጎሎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚጨምሩ ቢሆንም ዘንድሮ ይህ ያልሆነበት ምክንያት ምን ይሆን የሚለው ጥያቄ የሚያጭር ይሆናል። ምናልባትም ውጤቶቹ ከክብር፣ ከሁለተኛ ደረጃ እና ላለመውረድ ከሚደረግ ፉክክር አንፃር ለሁሉም እጅግ አስፈላጊ በመሆናቸው ቡድኖች ይበልጥ ጥንቃቄ አክለው መጫወታቸው ለዚህ የግብ ቁጥር መቀነስ በአይነተኛ ምክንያትነት የሚጠቀስ ሲሆን ታዝበናል።

👉 የሀዋሳ ምዕራፍ የመጀመርያ ሳምንት ክስተቶች

የሊጉ የመጨረሻ ምዕራፍ አምስት ጨዋታዎች በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት ተጀምረዋል። በቅድመ ዝግጅት፣ በልምምድ እና መጫወቻ ሜዳዎች፣ በሆቴል አቅርቦት፣ በኮቪድ ምርመራ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ በአስተናጋጇ ከተማ ላይ ቅሬታ ያልተደመጠ ሲሆን ይህ የሀዋሳ መስተንግዶ በመልካም ጎኑ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ ሆኖ አልፏል።

ፋሲል ከነማ የሊጉ ቻምፒዮንነቱን ማረጋገጡና ወልቂጤ ከተማ ፋሲሎችን በክብር ዘብ ወደ ሜዳ ማስገባታቸው፣ በውዝግብ መነጋጋርያ የሆነው ሀዲያ ሆሳዕና በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ጨዋታውን መጀመሩ፣ የጎሎች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ መታየት፣ የሀሪስተን ሄሱ ‘ሰርከስ’ ያስከተለው ጣጣ እና ተከትሎ የመጣው ውዝግብ በጨዋታ ሳምንቱ ላይ ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ናቸው።

👉 የመጀመሪያዋ ፍፁም ቅጣት ምት…

ከተሰረዘው የውድድር ዘመን አንስቶ በፕሪምየር ሊጉ እየተካፈሉ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ያገኙት የፍፁም ቅጣት ምት ቡድኑ በፕሪምየር ሊጉ ያገኛት የመጀመሪያዋ የፍፁም ቅጣት ሆና ተመዝግባለች።

ሆኖም ቡድኑ ውጤት እጅጉን አጥብቆ በሚፈልግበት በዚህ ወቅት የተገኘችው የፍፁም ቅጣት ምትን ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ግብነት ሳይቀይር መቅረቱ ለወልቂጤ ከተማዎች እጅግ አስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።

👉 የህሊና ፀሎቶች

በዚህ ሳምንት በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮ የህሊና ፀሎት ተደርገዋል። ድሬዳዋ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ ላይ በቅርቡ በድሬዳዋ ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የታሰቡ ሲሆን የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾችም በክንዳቸው ላይ ጥቁር ጨርቅ አስረው ተጫውተዋል።

በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባህር ዳርን ባሸነፈበት የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ከቀናት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደንበል ባልቻ የህሊና ፀሎት ተደርጎላቸዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው የጨዋታ ሳምንትም ለሀዋሳ ከተማው ታዳጊ አቤል አያኖ እና የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ኢትዮ ሴሜንት ተጫዋች ፀጋዬ ተስፋዬ የህሊና ፀሎት መደረጉ የሚታወስ ነው።

© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ