ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በ24ኛ የጨዋታ ሳምንት የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ አሰልጣኝ ነክ ጉዳዮች እና ዓበይት አስተያየቶች የሦስተኛው የፅሁፋችን አካል ናቸው።

👉 ባለውለታቸውን ያልዘነጉት ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) 

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከሀዲያ ሆሳዕና አመራሮች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከሥራ መታገዳቸውን ተከትሎ ኃላፊነቱን የተረከቡት የእሳቸው ረዳት የነበሩት ኢያሱ መርሐፅድቅ (ዶ/ር) ቡድኑ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በታዳጊ ተጫዋቾቻቸው ድንቅ ብቃት ታግዘው ጠንካራው ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲረቱ ኮስታራ የጨዋታ አቀራረብ ይዘው በመግባት ጉልህ ሚና ተወጥተዋል።  

ቁጥቡ አሰልጣኝ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ለእርሳቸው ወደ አሰልጣኝነት መምጣትም ሆነ በእሳቸው አገላለፅ ለቡድኑ ውለታ ውለዋል ላሏቸው አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ምስጋናቸውን አድርሰዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በነበረው ድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቃቸው እንዲህ ሲሉም ተደምጠዋል 

“ይህ ውጤት እዚህ ባለነው አካላት ብቻ የመጣ አይደለም፤ ለዋና አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። እነዚህ ልጆች እንዲመጡም ምክረ ሀሳብ ያቀረበው እሱ ነበር። ከመጡ በኃላም ከዚህ እስኪሄድ ብዙ ሥራዎችን ሰርቷል። በዚህም የዛሬው ውጤት የእርሱም ነው።”

አበርክቶ መነጣጠቅ በተለመደበት እግርኳሳችን መሰል ግለሰቦች ለሰሩት ሥራ እርስ በእርሰ መከባበር እና መሞጋገስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተለመደ መምጣቱ ይበል የሚያሰኝ በጎ ተግባር ነው።

👉 በብርድ እየተነዘፈዘፉ ጨዋታ የመሩት አሰልጣኝ

ከጥቂት ቀናት በፊት አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛውን በመተካት ወደ ወልቂጤ ከተማ ዋና አሰልጣኝነት መንበር የመጡት አሰልጣኝ ሲሳይ አብርሃ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በቀናት ልዩነት አዲሱን ቡድናቸውን ለሁለተኛ ጊዜ እየመሩ ወደ ሜዳ መግባት ችለዋል። 

እጅግ ከፍተኛ በሆነ ዝናብ ታጅቦ በተካሄደው እና በቀዝቃዛ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ያለ ግብ በተጠናቀቀው ጨዋታ በዚያ ዝናብ ውስጥ ጃኬት ሳይለብሱ የስፖርት ካኔቴራ ብቻ ሆነው ዝናቡ በላያቸው ላይ እየዘነበ ቡድናቸውን የመሩት አሰልጣኙ በከፍተኛ ሁኔታ በዝናብ ከመደብደባቸው የተነሳ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ በሜዳው ጠርዝ ቆመው እየተንቀጠቀጡ ጨዋታውን ሲከታተሉ አስተውለናል። በተመሳሳይ የተጋጣሚያቸው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምኅረትም ቡድናቸውን ለመምራት በሚወጡበት ወቅት እንዲሁ የዝናቡ ሰለባ ሆነዋል።

በመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት እንዲሁም በሁለተኛ ጨዋታቸው ደግሞ አቻ የተለያዩት አሰልጣኙ የመውረድ ሥጋት የተጋረጠበትን ቡድን ለመታደግ በአጭር ጊዜ ውል ስምምነት ቡድኑን እንደመረከባቸው የተቀበሉት ኃላፊነት እጅጉን ከባድ ከመሆኑ እና በትከሻቸው ላይ ከተጫነው ከፍ ያለ ጫና አንፃር ቡድናቸውን በዝናብ ውስጥ በዚህ መልኩ መምራታቸው የሚያስገርም ባይሆንም በዚህ ልክ ግን እስከመንቀጥቀጥ ድረስ የደረሰ መሆኑ ጉዳዩን አስገራሚ ያደርገዋል። 

👉የገብረመድኅ ኃይሌ ሌላ ገፅ 

ገብረመድኅን ኃይሌ ለሁለት አስርት ዓመታት በዘለቀው የአሰልጣኝነት ቆይታቸው ደስታቸውን ከፍ ባለ ስሜት ውስጥ ሆኖ ሲገልፁ እምብዛም ተመልከተን አናውቅም። ከሰሞኑ ግን አሰልጣኙ ባልተለመደ መልኩ ከግቦች መቆጠር በኋላ ከፍ ባለ ስሜት ደስታቸውን ሲገልፁ እየተመለከትን እንገኛለን። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ምንም እንኳን ቡድን በመጨረሻ ደቂቃ ግብ አስተናግዶ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ይለያይ እንጂ በተለይ ሦስተኛዋ የይገዙ ቦጋለ ግብ ስትቆጠር ደስታቸውን የገለፁበት መንገድ የተለየ ነበር። 

በእርግጥ አሰልጣኝ ገብረመድኅን በአሰልጣኝነት ቆይታቸው በአመዛኙ በዚህ ደረጃ ጅማ አባ ቡናን ተረክበው ላለመውረድ ከመታገላቸው በዘለለ በሊጉ የተረጋጉ ብሎም ወደ ሰንጠረዡ አናት የሚጠጉ ቡድኖችን በማሰልጠን ከነበራቸው ልምድ አንፃር በዚህ ደረጃ ላለመውረድ የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችን የማሰልጠን ልምድ የሌላቸው መሆኑ በዚህ ደረጃ ከወትሮው በተለየ ደስታቸውን ሲገልፁ መመልከታችን ከዚህ የመነጨ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል።

👉 ዓበይት አስተያየቶች

*ዘርዓይ ሙሉ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ስለሆነው አቡበከር ናስር ብቃት እና ስለ አብዲሳ ጀማል?

አቡበከርን የቡድኑም ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች አግዘውታል። ዞሮ ዞሮ የተጫዋቹ አቅም ምንም ጥርጥር የሌለው ነው። ትልቅ ተጫዋች ነው። ከዚህም በላይ ትልቅ ቦታም ይደርሳል ብዬ አስባለሁ። በእኔ ቡድን ውስጥ አብዲሳ አለ። አብዲሳም በራሱ ጥረት እዚህ መድረሱ ራሱ አቅሙን ያሳያል። ስለዚህ የሁለቱ ተጫዋቾች ቡድንም እነሱ ላይ ተፅዕኖ ያደርጋል ብዬ አስባለሁ። በአጠቃላይ ግን አቡበከርን ትልቅ አጥቂ ነው ብዬ ነው የምገልፀው።

*ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማን በጠበቁት ልክ ሰለማግኘታቸው 

“እንደ ቡድን እኛ ባለፉት 6 ጨዋታዎች አልተሸነፍንም ነበር። እነሱ በተወሰነ መልኩ ኳሱን ዘና ብለው ይዘው ለመጫወት ይሞክሩ ነበር። እኛ ደግሞ ውጤቱ ያስፈልገን ስለነበር ጫን ብለን ለመሄድ ያደረግነው ጥረት ውጤታማ አድርጎናል። ከሰሞኑ ካሳየነው መሻሻል እና ነጥቡን ይበልጥ ፈልገን አንደመጫወታችን ነጥቡ ይገባን ነበር።”

*ሥዩም ከበደ ከ19 ጨዋታዎች በኃላ ስለመሸነፋቸው 

“እስከዛሬ ካደረግናቸው ጨዋታዎች የዛሬውን በጠበቅነው መልኩ አላገኘነውም። ተነጋግረን የነበረው ሁሉንም ጨዋታዎች በ100% ማሸነፍ ለመጨረስ ነበር። ግቡን እስካስቆጠርንበት ጊዜ ድረስ የነበረው ጫና እንዲሁም መነሳሳት የድሬዳዎች የተሻለ ነበር ያም ቢሆን ግብ ማስቆጠር ችለን ነበር። ግቡን ለማስጠበቅ በነበረው ሒደት የሰራናቸው ስህተቶች ይበልጥ እንዲነሳሱ አድርጓል። በዚህ ሂደት የእኛ ልጆች ይበልጥ ወደ መሰላቸት ስሜት እንዲገቡ አድርጓል። በሁለተኛው አጋማሽ የተጫዋቾች ለውጥ አድርገን ለማስተካከል ሞክረን ነበር፤ ነገርግን አልተሳካልንም። እንደ አጠቃላይ የዛሬው ውሏችን ጥሩ አልነበረም። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነገሮችን አስተካክለን ወደ ነበረን የአሸናፊነት ጉዞ ለመመለስ እንሞክራለን።”

*ፋሲል ተካልኝ በመጨረሻዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ነጥቦችን ስለመጣላቸው?

“ለሁለተኝነት በምናደርገው ጉዞ ድሬዳዋ ላይ መሸነፍ ከጀመርን ጀምሮ ተጫዋቾቻችን በትልቅ ጫና ውስጥ ናቸው። ያንንም ለማስተካከል በአዕምሮም ሆነ በአካል ሞክረን ነበር። ግን እስካሁን ጨዋታዎችን ማሸነፍ አልቻልንም።  ወይም ደግሞ ወርቃማ የሚባሉ ዕድሎችን አበላሽተናል።”

*ሲሳይ አብርሃ ቡድኑ ለመትረፍ ስላለው ዕድል እና ስላለበት የስነ-ልቦና ደረጃ?

እኛ እስከ መጨረሻው ያለንን አሟጠን እንጠቀማለን። ተጫዋቾቼ ባለፈውም ተሸንፈው የነበራቸው ነገር ጥሩ ነበር። አሁንም ጀማል እያለቀሰ ነው የወጣው። ከድሬዳዋ ጋር በነበረው ጨዋታም ባለቀ ሰዓት ነበር ጎል ገብቶብን የተሸነፍነው። ያኔ አቻ እንኳን ብንወጣ ድሬዳዋንም እናስቀረው ነበር። ለዛሬውም ጨዋታ የተሻለ ነገር ይዘን እንመጣ ነበር። በቀሪዎቹም ሁለት ጨዋታዎች ግን ስድስት ነጥቦችን አግኝተን በሊጉ ለመቆየት እንሞክራለን።

*ካሣዬ አራጌ ስለ አቡበከር ናስር

“አቡበከር አሁንም ግቦችን ሊጨምር ይችላል ብዬ አስባለሁ። የቡድኑ እንቅስቃሴም ስለሚያግዘው ተጨማሪ ጎሎችን ሊያገባ ይችላል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የተመቻቸ ነገር ሊኖር ይገባል። በተለይ መሐል ላይ ያሉ ተጫዋቾች እሱን የያዙ (ማርክ) ተጫዋቾችን እየተቆጣጠሩ ለእርሱ ኳሶችን እንዲሰጡ የሚያደርግ መንገድ እንደ አሠልጣኝ መፍጠር አለብን። ለምሳሌ ሁለተኛው ኳስ ዊሊያም የሰጠው በዚህ መንገድ ነው። ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገሮችን እኛ እንደ አሠልጣኝ መፍጠር አለብን። ይሄ ነገር ካለ ተጫዋቹ ተጨማሪ ጎሎች ያገባል የሚል እምነት አለኝ።

“አቡበከር እኛ ከምንጫወተው ጨዋታ አንፃር ሂደቱን የመጠበቅ አቅም እንዲኖረው እንፈልጋለን። በግል ነገሮችም የመወጣት፣ ራሱን ለመጨረሻ ኳስ የማዘጋጀት እና የመጨረሻ ኳስ የመስጠት አቅም የሚታዩበት ተጫዋች  ነው። ኳሶችን እንደ ቡድን የማስጣል ሂደት ውስጥም ይሳተፋል። ለምሳሌ አሰግድ እንደዚህ አይነት ብዙ ብቃቶች አሉት። ግን እሱ በቡድን ኳሶችን በመንጠቁ ረገድ ትንሽ ደካማ ነው። ምናልባት ግን ይሄ ነገር ከምንጫወተው አጨዋወት ጋርም ይያያዛል። በፊት ተጫዋቾቹ የሚጠየቁት ነገር ሌላ ነው። ከዚህ መነሻነት አቡበከርን ከበፊት ተጫዋቾች ጋር ማነፃፀሩ ይከብዳል።”

ያጋሩ