ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

የመጨረሻው የትኩረታችን ክፍል ሌሎች ትኩረት የሚገባቸው ጉዳዮች በተከታዩ መልክ ተዳሰውበታል።

👉 የተሻለው ነገርግን ይበልጥ መሻሻል የሚገባው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መጫወቻ ሜዳ 

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር እስካሁን በአራት የተለያዩ ከተሞች ተደርጎ አሁን ላይ በአምስተኛዋ አዘጋጅ ከተማ በሆነችው ሀዋሳ ከተማ ጅማሮውን ካደረገ ሦስተኛ የጨዋታ ሳምንቱ ላይ ደርሷል። 

ላለመውረድ እንዲሁም ለሁለተኝነት በሚደረገው ፉክክር ወሳኝ የሆኑትን እነዚህን የመጨረሻ ሳምንታት ጨዋታዎች እያስተናገደ የሚገኘው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም አስቀድመው በተለቀቁ የሜዳው ምስሎች በርካቶች በሜዳው ላይ ጥርጣሬ ገብቷቸው የነበረ ቢሆንም ውድድሩ መካሄድ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከተስተዋሉበት እንከኖች ውጭ ጥሩ ገፅታን የተላበሰ ሜዳ መሆኑን እያስተዋልን እንገኛለን። 

እርግጥ በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞ ከባህር ዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ውጭ የተካሄደባቸው ሁሉም ስታዲየሞች የመጫወቻ ሜዳቸውን በተመለከተ ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን ማስተናገዳቸው አይዘነጋም። ነገርግን የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመጫወቻ ሜዳ ግን በግልፅ የሚታዩ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ቢኖሩትም ከባህር ዳር  አለምአቀፍ ስታዲየም ቀጥሎ የተሻለው የመጫወቻ ሜዳ ስለመሆኑ ግን በግልፅ መናገር ይቻላል። 

ሜዳ ዝናብ ባልጣለባቸው ወቅቶች በሜዳው የቀኝ ወገን በተወሰኑ ክፍሎቹ ላይ በአሽዋ ከተለበጡ (patch ከተደረጉ) ክፍሎቹ ውጪ ለዕይታም ሆነ ለጨዋታ ምቹ የሆነ ሜዳ ነው። ነገርግን እንደሌሎቹ ሜዳዎች ሁሉ በዝናብ ወቅት በሜዳው ደካማ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት ምክንያትነት እንደቀደሙት አስተናጋጅ ከተሞች መቸገሩ አልቀረም። 

ከሌሎች ስታዲየሞች በተለየ ግን ሜዳው በከፍተኛ ዝናብ ውስጥ እንኳን ሆኖ ጨዋታዎችን በሚያስተናግድበት ወቅት በተወሰኑ የሜዳ ክፍሎቹ ውሃን ከመቆጠር በዘለለ እንደሌሎቹ የመጫወቻ ሜዳዎች በጭቃ ሲላቁጥ አለመስተዋሉ በበጉ የሚነሳለት ጉዳይ ነው። 

ይህ የመጫወቻ ሜዳዎች ጉዳይ አሁንም በአወዳዳሪ አካላትም ሆነ በሌሎች ስታዲየሞችን በበላይነት በሚያስተዳድሩ የክልል ማዘጋጃ ቤቶች ሆነ በሚመለከተው የስፖርት ኮሚሽን ሰዎች ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል። 

በዚህም በበርካታ ስታዲየሞች ላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የመጫወቻ ሜዳዎችን ለማሻሻል ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል። ነገርግን እነዚህ የማሻሻያ ሥራዎች የቀደመውን ሳር በማስወገድ በተወሰነ መልኩ የቀደመውን አፈር በሌላ የተመረጠ አፈር ከተመካት ጋር እንጂ የስታዲየሞችን የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት የማዘመን ሆነ የመጫወቻ ሳሮቹን በጥራት እና በምቹነት እስከማሻሻል በሚደርስ ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶባቸው መሰራት ይገባቸዋል።

👉 የውድድር ዘመኑ መገባደጃ እና የጨዋታ ዳኝነት 

የውድድር ዘመኑ ለመጠናቀቅ ሁለት ያክል የጨዋታ ሳምንታት ብቻ ቀርተዋል። በዚህም ሒደት የሁለተኝነት ደረጃን ለማግኘት ሆነ ሶስተኛውን ወራጅ ቡድን ለመለየት የሚደረገው ትንቅንቅ አጓጊ መልክን ይዞ እንደቀጠለ ነው። 

ዳኝነት እንኳን በእኛ ሀገር በቴክኖሎጂ እንኳን እየተደገፈ በሚገኝባቸው ያደጉት ሀገራት ከስህተት የፀዳ አለመሆኑ እርግጥ ነው። ነገርግን በእኛ ሀገር አውድ በተለይ በረዳት ዳኞች ላይ በመሰረታዊ የጨዋታ ህጎችን ላይ የሚፈፀሙ ስህተቶች እና የትኩረት ችግሮች በተለይ ባለፉት ጥቂት የጨዋታ ሳምንታት ላይ እየተበራከቱ መምጣታቸው በቀላሉ መታየት የሌለበት ጉዳይ ነው።

በተለይ እንደዚህ ፉክክሩ በጦዘበት ወቅት ቡድኖች ሜዳ ላይ በሚደርግ እግርኳሳዊ ፉክክር ብቻ እንኳን ተሸንፈውም ምክንያቶች የመደርደር እንዲሁም የሴራ ንድፈ ሀሳቦች ማስቀመጥ በተለመደበት የሀገራችን እግርኳስ በተለይ በቀሩት ሁለት ጨዋታዎች አወዳዳሪው አካል ከዳኝነት ምደባ ጋር በተያያዘ እንዲሁም የጨዋታ ዳኞችም ጨዋታዎችን ይበልጥ በጠንቃቄ የሚመሩበት አግባብ መፍጠር የግድ ይላል። ይህ መሆን የማይችል ከሆነ ለተለመዱ እና ማለቂያ ለሌላቸው ንትርኮች በር ሊከፍት ስለሚችል ጥንቃቄ መደረግ ይኖርበታል።

ያጋሩ