የ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን የሆነው ፋሲል ከነማ የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግ በሸራተን አዲስ ሆቴል ያካሄደው የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሐግብር ምሽቱን ተካሂዷል።
“ስፖርት ለኢትዮጵያ ኅብረት” በሚል መሪ ቃል አመሻሽ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ባለሀብቶች፣ የእግርኳሱ የበላይ አካላት እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ደማቅ በሆነ በዚህ የምሽት ሥነስርዓት ከመንግሥት አካላት እግርኳሱን በተመለከተ መልዕክቶች ከመተላለፋቸው ባሻገር ሀገራዊ መግባባት የሚፈጥሩ ንግግሮች ከተለያዩ የመንግሥት ኃላፊዎች ሲተላለፉ ተሰምቷል።
የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ከድሉ ጀርባ የመጡበትን ዕልህ አስጨራሽ ትግል እንዴት እንዳለፉ ከገለፁ በኋላ የቡድኑ አንበል ያሬድ ባዬ በማስከተል ” ይህ ስኬት አንድ በመሆን በጋራ ሰርተን በጥረት ያመጣነው ድል ነው። ፋሲል ከነማ ‘ትንሿ ኢትዮጵያ’ን የሚያገኙበት ክለብ ነው።” በማለት የገለፀበት መንገድ በዝግጅቱ ላይ የተገኙትን እንግዶች በአንድ ድምፅ አስጨብጭቧል።
በገቢ ማሰባሰቢያው መርሐግብር ከተለያዩ አካላት ከ አንድ መቶ ሀምሳ አምስት ሚልየን ብር በላይ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የተገባ ሲሆን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እግርኳሱ በጎጥ በተከፋፈለበት አስቸጋሪ ጊዜ ወደ ኃላፊነት እንደመጡ ገልፀው በተለይ የአማራ እና የትግራይ ክለቦች መካከል ተዟዙሮ ለመጫወት ባልፈለጉበት ወቅት ችግሩን ለመቅረፍ በተወሰደው ጥረት የፋሲል አስተዋፆኦ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ የፌዴሬሽኑን አሰራር ለማዘመን የተደረገው ለውጥ የሊግ ካምፓኒውን ወልዶ የዘንድሮ ውድድርን በልዩ ሁኔታ እግርኳሱ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያስገኝ ያስቻሉ ስኬቶችን በማስመዝገባቸው የሊግ ካምፓኒው አመራሮችን አመስግነው እግርኳሱ ከመንግሥት ጥገኝነት ወጥቶ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው ለማድረግ እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች አስፋላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል። ሌሎችም ክለቦች ከዛሬው መድረክ ትምህርት እንዲወስዱ በመግለፅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን አድንቀዋል። በመጨረሻም ወደፊት በእግርኳሱ የሚጠብቅ ብዙ የቤት ሥራ ስላለ ከጊዜያዊ ደስታ በመውጣት ለቀጣይ ኃላፊነት እንዲዘጋጁ መልዕክት አስተላልፈው በፈዴሬሽኑ ስም አምስት መቶ ሺህ ብር ለማበርከት ቃል ገብተዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረመስቀል እግርኳስ የሰላም መድረክ መሆኑን ገልፀው “በጥረታችሁ ለስኬት በመብቃታችሁ ፋሲል ከነማዎችን እንኳን ደስ አላችሁ” በማለት በሚድሮክ ኢትዮጵያ ስም ሁለት ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በጥዑመ ዜማ ታጅቦ በቀጠለው በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐግብር የአማራ ክልል 20 ሚሊዮን፣ የኦሮሚያ ክልል 25 ሚሊዮን፣ የደቡብ ክልል 10 ሚልዮን፣ የሲዳማ እና የሱማሌ ክልል እያንዳንዳቸው አምስት ሚሊዮን፣ ፋሲል ከነማን በገንዘብ በመደገፍ የሚታወቁት አቶ ወርቁ አይተነው አስር ሚሊዮን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ አምስት ሚሊየን ብር ቃል ከገቡ ግለሰቦች እና ተቋማት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።