የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ ስለወቅቱ ድንቅ ተጫዋች አቡበከር ናስር ሪከርድ ማሻሻል እና በብቃቱ ዙርያ አስተያየት ሰጥተውናል።
በእግርኳሱ ቤተሰብ ዙርያ በዛሬው ዕለት ትልቁ መነጋገሪያ ርዕስ የነበረው በጌታነህ ከበደ ለአራት ዓመት ተይዞ የቆየው በአንድ የውድድር ዓመት ከፍተኛ ጎል በማስቆጠር ተይዞ የነበረውን የ25 ጎል ሪከርድ አቡበከር ናስር በአስደናቂ ሁኔታ በ27 ጎል የማሻሻሉ ጉዳይ ነው። ይህን ተከትሎ የወቅቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በግል የፌስቡክ ገፃቸው ለአቡበከር ‘እንኳን ደስ አለህ’ ካሉ በኃላ ከዚህ በኋላ ‘የአቡበከር ሪከርድ በሌላ ተጫዋች በቀላሉ እንደማይሰበር እርግጠኛ ነኝ፤ በራሱ አቡበከር ካልሆነ በስተቀር’ በማለት ያሰፈሩትን ሀሳብ መነሻ በማድረግ ከሌሎች ጥያቄዎች ጋር አያይዘን አጭር ቆይታ አድርገናል።
በፌስኩህ ገፅህ ላይ ያስቀመጥከው አንድ ፁሁፍ አለ። ከዚህ በኋላ የሚሰበረው በእርግጠኝነት ራሱ አቡበከር ብቻ ነው” የሚል። ይሄን ከምን ተነስተህ ነው? በዝርዝር ብታስረዳኝ ?
” እስካሁን ሪከርዱ ተይዞ የነበረው በጌታነህ ነበር። ሁሉም አጥቂዎች በተለያየ ጊዜ የመስበር እድሉ በእጃቸው ነበር። ዘንድሮም በተካሄደው ውድድር ሪከርዱን ለመስበር ፉክክሩ ላይ አቡበከር፣ ሙጂብ እና ራሱ ጌታነህ ነበሩ። ታዲያ የቀረውን ጨዋታ ስትመለከት ሪከርዱን ለመስበር የተጠጉት አቡበከር እና ሙጅብ ናቸው። ስለዚህ ዛሬ አቡበከር ጎል ሲያስቆጥር ሪከርዱን በጁ ያዘ ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ በኋላ ሪከርዱ 25 የነበረው 27 ሆኗል። ለ28 ግብ ከአቡበክር የተሻለ ማንም ሰው የለም፤ ይሄ ቀላል ሂሳብ ነው። አቡበከር ደግሞ ሜዳ ላይ እየተጫወተ ያለ ተጫዋች ነው። ከአቡበከር የተሻለ ለ28 የቀረበ ተጫዋች የለም። አሁንም ሜዳ ላይ ቀሪ ሁለት ጨዋታ ስላለው አሁንም ከአቡበከር ሪከርዱን ለመስበር የተሻለ ነው። ሆኖም ሌሎች አጥቂዎች አቅም የላቸውም ማለቴ አይደለም። ለሪከርዱ ቁጥር የቀረበው አቡበከር እስካሁን ሁለት ቀሪ ጨዋታ እያለው እርሱ 27 ወይም 28 ለመድረስ የሚያደርጉ ጥረት ከአቡበከር አንፃር ስታየው አቡበከር በጨዋታዎች ግቦችን የማስቆጠር አቅም ስላለው ነው። በቀጣይ ዓመት ይሰበራል የሚል ነገር ሳይሆን እዚሁ ውድድር ዓመት ላይ ያለውን እውነታ ነው ማስተላለፍ የፈለግኩት። በነገራችን ላይ አብበከርን ብትጠይቀው ከኔ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስናወራ ታርጌት ያደረገው አገባለው የሚለው የጎል ቁጥር 30 ጎል እንደሚያደርስ ነው ያወራነው። አሁን ወደዛ ወደ 30 ቁጥር እየሄደ ስለሆነ እና ቢያንስ ለሠላሳ ያሰበውን ባያሳካ 27 ደርሷል፤ በጣም ነው የማደንቀው። ለጊዜው ሪከርዱ ተሰብሯል። እስከ መጨረሻው ሊሄድ የሚችልበት መንገድ አለ። በቀጣይ ዓመት ደግሞ ምናልባት ይሄን ሪከርድ አቡበከርም ይሁን ሌላ ተጫዋች ሊያሻሻሽሉት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ግን ሪከርዱን ለመስበር የቀረበው አቡበከር ነበር እንጂ የሚቀጥለው ዓመት ከዚህ ቁጥር በላይ ጎል አይገባም ማለቴ አይደለም።”
እግርኳስን ተጫውተህ እንደማለፍህ እና እንዳሰልጣኝ በኢትዮጵያ ውስጥ ካየሀቸው አጥቂዎች አቡበከር በምን የተለየ ነው ?
አቡበከር ልዩ የሚያደርገው ነገር አሁን ለመናገር ጊዜው በጣም ገና ነው። ከዕድሜ አንፃር እንኳን ካየኸው አቡበከር ገና ነው። የቀድሞዎቹ አብዛኛዎቹ አጥቂዎች ተጫውተው የጨዋታ ዘመናቸውን ጨርሰዋል። እሱ ገና የጨዋታ ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ነው ያለው። ስለዚህ ገና ጅምር ላይ ሆኖ የሚያደርጋቸው ነገሮች ወደፊት የተሻለ ነገር እንዳለው የሚያሳይ ነው። በአንድ አንድ ነገሮች ላይ መሥራት ከቻለ ለበለጡ ድሎች ለበለጠ አቅም የሚጥር ከሆነ እና በአዕምሮም በአካልም እያደገ ሲሄድ ከዚህ በላይ የተሻለ ነገር እንደሚያሳይ እርግጥ ነው። ገና ከጅምሩ ብዙ ነገሮችን እያሳየ ያለ ልጅ ነው። ሆኖም ከቀደመዎቹ የተለየ የምለው ነገር ቢኖር ጎል አካባባቢ ኳስን ወደ ግብ የሚቀይርባቸው መንገዶች፣ አይሆኑም ብለህ በምታስብበት ሁኔታ ጎል ማስቆጠር መቻሉ፣ ከዛ በተረፈ በምቾት የሚጫወት አጥቂ ነው። ከኳስ ጋር ሲሆን ደግሞ የበለጠ የሚፈጥነው ነገር አለ። ቀደዳዎችን እና ክፍት ቦታዎችን የመጠቀም እና አማካዮች ራሱ ወደዛ እንቅስቀሴ እንዲገደዱ የሚያደረግበት ሁኔታ እርሱን የተለየ ያደርገዋል። ከዚህ በኋላም የተሻለ ብዙ ነገር ያደርጋል ብየ እጠብቃለሁ።
እንደ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አቡበከርን መረን ትመክረዋለህ ?
” አቡበክር እንግዲህ ሲጀመር ወጣት ነው። በባህሪው ብዙ ምክር የሚያስፈልገው ልጅ ነው ብዬ በግሌ አላምንም። በጣም ጨዋ ነው። ሥራውን በጣም ነው የሚወደው። ገና ልጅ ነው ከተጫወተበት ጊዜ ይልቅ ወደፊት የሚጫወትበት ጊዜ ይበልጣል። አቋሙ ሳይዋዥቅ ጠብቆ ለመሄድ ይበልጥ ዲሲፕሊንድ መሆን አለበት። በሌላ መንገድ በክለብ እያደረገ ያለውን ነገር በብሔራዊ ቡድን ላይ መድገም አለበት። ለምሳሌ ጌታነህ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች እና አራት የወዳጅነት እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋተዋች 7 ጎል አግብቷል። ይሄ ደግሞ ትልቅ ነገር ነው። እንደ አንድ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ጌታነህ አንጋፋ ነው። 30ጎሎች ለብሔራዊ ቡድን አግብቷል። በቁጥር እስከማውቀው ማለት ነው። በዚህ በኩል የብሔራዊ ቡድን ሪከርድ በማን ሊሆን ይችላል የሚለው ቁጥሩ ስሌለኝ ያንን ደፍሬ መናገር አልችልም። ሆኖም አቡበከር የጌታነህን 30 ጎል ሊያልፍ የሚችልበትን ዕድል አለ። አቡበከር ሙሉ ተጫዋች ነው ማለት አይደለም። የሚጎድሉት ብዙ ነገሮች ስላሉ እነዛ ላይ ጠንክሮ መስራት ቢችል ለውጤት ሁሌም እንዲራብ ትንሽ ነገር አግኝቻለሁ ብሎ እንዳይቆም ነው የምመክረው። በእርግጠኝነት ግን ብሔራዊ ቡድናችንን በትልቅ ደረጃ ሊጠቅም የሚችልበት አቅም እንዳለው እና በዚህ ሊግ ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር ነው የምመክረው። “