ሪፖርት | የጦና ንቦቹ ወደ አሸናፊነት ሲመለሱ ባህር ዳሮች በሽንፈት ዓመቱን አጠናቀዋል

ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻን ያገናኘው የ25ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ወላይታ ድቻን አሸናፊ አድርጓል።

የውድድር ዓመቱን የመጨረሻ ጨዋታ የሚያደርጉት ባህር ዳር ከተማዎች ከጅማ አባጅፋር ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ አራት ተጫዋቾችን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ  በአምስት ቢጫ ካርድ ምክንያት ወደ ሜዳ ያልገባው ፍቅረሚካኤል ዓለሙን እና በጉዳት ምክንያት ለስብስቡ ውጪ የሆነው ፍፁም ዓለሙን ጨምሮ በረከት ጥጋቡ  እና ምንይሉ ወንድሙን በይበልጣል አየለ፣ ደረጄ መንግሥቱ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና አፈወርቅ ኃይሉ ተክተዋል። በ24ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብር አራፊ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች በበኩላቸው ከመጨረሻው የጅማ ጨዋታ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ፀጋዬ ብርሀኑ፣ አንተነህ ጉግሳ እና ነፃነት ገብረመድህንን በማሳረፍ በረከት ወልዴ፣ ኢዙ አዙካ እና ዮናስ ግርማይን ወደ ቋሚ አሰላለፍ አምጥተዋል።

የተመጣጠነ የጨዋታ እንቅስቃሴ ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የተቆራረጡ የኳስ ቅብብሎች ሲስተዋሉበት ነበር። በአንፃራዊነት ግን ባህር ዳር ከተማ በመጠኑ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ኖሮት ሲጫወት ታይቷል። ቀጥተኛ አጨዋወት ለመከተል ሲጥሩ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በ6ኛው ደቂቃ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ስንታየሁ መንግስቱ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ ለመጠቀም ጥሮ ሳይሳካለት ቀርቷል። ይሄንን ኳስ ለመሞከር የጣረው ስንታየሁ ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ከግራ መስመር መነሻን ያደረገ ኳስ በመጠቀም ከሳጥኑ ጫፍ ጥሩ ጥቃት ፈፅሞ ነበር። ሁለቱን ተከታታይ ሙከራዎች ለማድረግ የባህር ዳር የፍፁም ቅጣት ምት ክልል አካባቢ የተገኘው ስንታየሁ አሁንም ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ሌላ ጥቃት ፈፅሞ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ሞክሯል። በዚህም አናጋው ባደግ ከቸርነት ጉግሳ ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ለስንታየሁ አመቸችቶለ ቁመታሙ አጥቂ ኳስን ከመረብ ጋር ለማዋሀድ ጥሯል። ነገርግን ተጫዋቹ የሞከረውን ዒላማውን የጠበቀ ኳስ የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድ አክሽፎታል።

አሁንም ኳሱን በማንሸራሸር እና የድቻን ጥቃቶች በመመከት ተጠምደው ያሳለፉት ባህር ዳሮች አንድም የጠራ የግብ ማግበት ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ቀጥሏል። በዋናነት ደግሞ ቡድኑ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ሲገባ አላማ ያላቸው ኳሶችን በጥሩ ስኬት መቀባበል ተስኖት ታይቷል። በዚህም ቡድኑ ጠንቃቃ ሆነው ጨዋታውን ሲከውኑ የነበሩትን የድቻ ተከላካዮች ማለፍ አቅቶት የመጀመሪያውን አጋማሽ ያለ ምንም ሙከራ አገባዷል። በብዙ መስፈርቶች ጥሩ የነበሩት ወላይታ ድቻዎችም በአጋማሹ አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በማጥቃቱ ረገድ በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ መሻሻል አድርገው የመጡት የሚመስሉት ባህር ዳሮች በመጀመሪያዎቹ የአጋማሹ ደቂቃዎች ወደ ግራ ባዘነለ መስመር ጥቃት ለመሰንዘር ሲጥሩ ታይቷል። በ52ኛው ደቂቃ ደግሞ የመጀመሪያውን የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ (ዒላማውን ያልጠበቀ) አድርገዋል። በዚህ ደቂቃም ባዬ ገዛኸኝ ግብ ጠባቂውን ዳንኤል አጃዬን ተጭኖ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። በዚህ የባህር ዳር ጥቃት ያልተደናገጡት ወላይታ ድቻዎች በ55ኛው ደቂቃ በጨዋታው መሪ የሚያደርጋቸውን ጎል አስቆጥረዋል። በዚህም ቸርነት እድሪስ ሰዒድ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ እየገፋ የመጣውን ኳስ ተቀብሎ ድንቅ ጎል ከወደ ግራ ባዘነበለ ቦታ አስቆጥሯል።

ከመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጥረት ውጪ እምብዛም የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማስመልከት ያልቻሉት ባህር ዳሮች በ63ኛው ደቂቃ ባዬ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ በሞከረው ኳስ አቻ ለመሆን ሞክረዋል። በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ላይ የተመጣጠነ የተጫዋች ቁጥር አድርገው መጫወታቸውን የቀጠሉት ወላይታ ድቻዎችን በ69ኛው እና 70ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል። በቅድሚያም ስንታየሁ ከቸርነት እንዲሁም ቸርነት ከያሬድ የደረሳቸውን ኳስ በመጠቀም ጥቃት ፈፅመዋል።

ጨዋታው 76ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወላይታ ድቻ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። በዚህ ደቂቃም የተገኘውን የቅጣት ምት የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ ለቸርነት አቀብሎት ቸርነት ለቡድኑ እና ለራሱ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ሁሉ ነገር ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሆነባቸው የመጣው ባህር ዳሮች በ79ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህ ደቂቃም ባዬ ገዛኸኝ ከመሐል የተላከውን ኳስ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ቢያገኘውም የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ ውጪ ምንም ጥቃት ያልፈፀሙት ባህር ዳሮች የውድድር ዓመቱን የመጨረሻ ጨዋታ በሽንፈት ደምድመዋል። ወላይታ ድቻዎችም በጠንካራ ሁኔታ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በመከለከል እና አልፎ አልፎ አደገኛ የመልሶ ማጥቃት እንቅስዋሴዎችን በማድረግ ጨዋታውን አገባደዋል። 

ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር ከተማ በአጠቃላይ የውድድር ዓመቱ በሰባቸው 33 ነጥቦች 5 ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ወላይታ ድቻ ደግሞ ነጥቡን ወደ 33 ደረጃዉን ደግሞ ወደ 6 (በግብ ክፍያ ተበልጦ) ከፍ አድርጓል።

ያጋሩ