ሪፖርት | በተከላካይ ስህተት የተገኘው የኦሴ ማውሊ ብቸኛ ጎል ሰበታን ባለ ድል አድርጓል

የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሐ-ግብር የሆነው የሰበታ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በሰበታ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል።

የሰበታ ከተማው አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ሀዲያም ድል ካደረጉበት ጨዋታቸው አራት ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በዚህም አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ፣ ናትናኤል ጋንቹላ፣ ኢብራሂም ከድር እና አዲሱ ተስፋዬ አርፈው ፉአድ ፈረጃ፣ መስዑድ መሐመድ፣ ታደለ መንገሻ እና ቢያድግልኝ ኤልያስ በቋሚ አሰላለፉ ተካተዋል። የአዳማ ከተማው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው በሀዋሳ ከተማ ከተጠቀሙበት ቋሚ ስብስብ ማማዱ ኩሊባሊ፣ ኢሊሴ ጆናታን እና ኤልያስ ማሞን በኤልያስ አህመድ፣ ጀሚል ያዕቆብ እና ደሳለኝ ደባሽን ምትክ አሰልፈው ለጨዋታው ቀርበዋል።

የጨዋታውን የሃይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ሰበታ ከተማዎች አብዛኛውን የኳስ ቅብብላቸውን የአዳማ ሜዳ ላይ በማድረግ ግብ ማስቆጠሪያ ክፍተቶችን በትዕግስት ሲጠባበቁ ነበር። በ10ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የአዳማ ተከላካይ የተሳሳተውን ኳስ ተጠቅመው መሪ ሊሆኑ ነበር። በዚህም ኦሴ ማውሊ ደስታ ዲቻሞን ተጭኖ የተቀበለውን ኳስ ለዳዊት እስቲፋኖስ አቀብሎት ዳዊት ጥቃት ቢፈፅምም ሌላኛው ተከላካይ አሚኑ ነስሩ የአጋሩን ስህተት በጥሩ ቅልጥፍና አርሞታል። በዚሁ ቅፅበት ተከላካዮ የመለሰውንም ኳስ ፉአድ ፈረጃ ሞክሮት የነበረ ቢሆንም ኳስ ዒላማዋን ስራ ወደ ውጪ ወጥታለች። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም በድጋሜ ፉአድ ከማውሊ የደረሰውን ኳስ በመጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ጥሮ መክኖበታል።

ቀጥተኛ አጨዋወትን ምርጫቸው ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ዘለግ ያለውን ደቂቃ ከኳስ ጀርባ በማሳለፍ አልፎ አልፎ ብቻ የሰበታ የግብ ክልል መድረስ ይዘዋል። በ15ኛው ደቂቃም ቡድኑ በአብዲሳ ጀማል የርቀት ኳስ ጥሩ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። ለተሰነዘረባቸው ጥቃት ወዲያው ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ሰበታዎች ከደቂቃ በኋላ እጅግ ለግብ ቀርበው ነበር። በዚህም ፎአድ ራሱን ከግብ ጠባቂው ሴኩምባ ካማራ ጋር አንድ ለአንድ የሚያገናኘውን ኳስ ከዳዊት በተከላካዮች መካከል አግኝቶ በአስቆጪ ሁኔታ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የወረደ ድርሻ የነበራቸው አዳማዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አደገኛ መሆናቸውን በ20ኛው ደቂቃ አሳይተዋል። በዚህም ሀብታሙ ወልዴ በጥሩ ሽግግር ራሱን ነፃ አድርጎ ከአብዲሳ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ ቢመታውም ኳሱ ለጥቂት የግቡን መረብ ታኮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

ያለ ጎል ሲጓዝ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ፍክክር በ35ኛው ደቂቃ መሪ አግኝቷል። በተጠቀሰው ደቂቃም የመሐል ተከላካዩ አሚኑ ነስሩ ከግብ ጠባቂው ሴኩምባ ካማራ የደረሰውን ኳስ መልሼ ለራሱ እሰጣለሁ ብሎ ወደ ኋላ ሲመልስ ኦሴ ማውሊ ከግብ ጠባቂው ቀድሞ በማግኘት ቡድኑን ቀዳሚ ያደረገ ጎሎ አስቆጥሯል። ግብ ሲቆጠርባቸው መጠነኛ የማጥቃት ፍላጎት ያሳዩት አዳማ ከተማዎችም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል አቻ ሊያደርጋቸው የሚችለውን አጋጣሚ ፈጥረው ነበር። በዚህም የአጥቂ አማካዩ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጪ ጥብ ኳስ ወደ ግብ የመታ ቢሆንም የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል ኳሱን ተቆጣጥሮታል። አጋማሹም ተጨማሪ ሙከራ ሳይደረግበት በሰበታ ከተማ መሪነት ተገባዷል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ደቂቃዎች የነበራቸውን መነሳሳት በዚህኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይም ያሳዩት አዳማ ከተማዎች ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ጎል ለማግኘት መታተር ይዘዋል። በ53ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘን የቅጣት ምትም ሀብታሙ ከርቀት መትቶት ነገርግን ፋሲል በተቆጣጠረው ኳስ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል። ይሄንኑ ሙከራ ያደረገው ሀብታሙ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ከቡድኑ አምበል ኤልያስ የደረሰውን ኳስ በድጋሜ ከርቀት ወደ ግብ ልኮ ነበር። በተቃራኒው በመጠኑ ቀዝቀዝ ብለው የታዩት ሰበታዎች ደግሞ በ57ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር የራሳቸውን የግብ ክልል ለቀየው የወጡት የአዳማ ተጫዋቾች ጀርባ ሰፊ ሜዳ አግኝተው ጥቃት ፈፅመዋል። በዚህም መሱዑድ መሐመድ ከፎአድ የደረሰውን እጅግ ያለቀለት ኳስ ተጠቅሞ ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር ሲጥር የግራ መስመር ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን ደርሶ አውጥቶበታል።

ጨዋታው ቀጥሎም በ65ኛው እንዲሁም በ72ኛው ደቂቃ ግብ ሊያስተናግድ ነበር። በመጀመሪያም የብቸኛው ግብ ባለቤት ማውሊ ራሱ ላይ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ ወደ ግብ የመታው የቅጣት ምት ካማራ ወደ ውጪ ሲያወጣበት በመቀጠል ደግሞ አዳማዎች በቃሉ ገነነ ከሳጥን ውጪ በሞከረው ኳስ ፋሲልን ፈትነዋል። ከእነዚህ ሙከራዎች በኋላም የሁለቱም ቡድን አሠልጣኞች ግብ ለማስቆጠር የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ ቢያስገቡም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርቷል። ከላይ ከተጠቀሱት ሙከራዎች በኋላም በጨዋታው ሌላ ምንም የጠራ የግብ ማግባት እድል አልተፈጠረም። ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በሰበታ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተገባዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ለተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት የማያቀው ሰበታ ከተማ ነጥቡን 33 አድርሶ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል። ከሊጉ መውረዱን ቀደም ብሎ ያረጋገጠው አዳማ ከተማ ደግሞ በ13 ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል።