ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው የረፋዱ ጨዋታ በኋላ አሠልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ
ጨዋታው ምን ያህል ፈታኝ ነበር?
ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን ግልፅ ነበር። ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚያስችል ዕድል አግኝተን ነበር። በተለይ ቡናዎች አንድ ተጫዋች ከጎደለባቸው በኋላ ይሄንን ዕድል መጠቀም አልቻልንም። ቡድኔ ላይ ጥድፊያ ይታይ ነበር። ቀስ ብለን ነፃ ሰው እየፈለግን ብንጫወት ኖሮ ጨዋታውን እናሸንፍ ነበር። ግን ተጫዋቾቻችን ላይ ትልቅ ጉጉት ይታይ ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ ቡና ላይ የነበራቸውን የቁጥር ብልጫ ስላለመጠቀማቸው?
በሁለተኛው አጋማሽ ለመከላከል አላሰብንም። ግን ብዙ ጊዜ ጎዶሎ የሆነው ቡድን የተነሳሽነት ስሜቱ ከፍ ይላል። ይሄ እንደሚሆንም አውቄ ለተጫዋቾቼ ትዕዛዝ አስተላልፌ ነበር። ግን እኛ ቡድን ላይ ሦስተኛ ጎል ለማስቆጠር ትልቅ ጥድፊያ ይታይ ነበር። ይሄ ደግሞ ዋጋ አስከፍሎናል።
ስለ ቀሪ ጨዋታዎች እና ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ስለማጠናቀቅ?
እስከመጨረሻው እንጫወታለን። ሁለተኛ ደረጃን እንኳን ባናገኝ ምርጥ ሦስት ደረጃ ውስጥ ለመግባት የምንችለውን እናደርጋለን። ዕድሎችም አሉን። ዛሬ ሜዳ ላይ ጥሩ ቡድን ነበረን። አለማሸነፋችን ብቻም ነው ያስከፋኝ።
ስለ ዳኝነቱ?
ስለ ዳኛ ማውራት አልፈልግም። ዳኞችን የሚረዳ ቴክኖሎጂ ሳይኖር ሁል ጊዜ እነሱ ላይ ጣታችንን መቀሰር ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። በእርግጥ አንዳንድ ስህተቶች ነበሩ። ግን ሰዋዊ አድርጌ አያቸዋለሁ።
ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው?
እነሱ ጫና ለመፍጠር ወደ እኛ ሲመጡ ከጀርባ የሚተውሉንን ሰው ነበር። ይሄንን ሰው መጠቀም እንዳለብን ተነጋግረን ነበር። ግን በዚህ ሂደት ኳስ የሚዘውም ሆነ የሚቀበለው ተጫዋች ዝግጁ መሆን ነበረባቸው። ይሄንን በተገቢው መንገድ አልሰራንም። ከዚህ ውጪ ተጋጣሚያችን በዚህ መንገድ እንደሚመጣ ጠብቀን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ኳሶች ሲበላሹ 90 ደቂቃ እንደዛ እንደሚቀጥሉ የማሰብ ችግር ነበር። ነገሮች 90 ደቂቃ በዛ መልኩ አይቀጥሉም። ነገርግን ተጫዋቾች ነገሮች እንደዛ እንደሚቀጥሉ ሲያስቡ የራስ መተማመን መውረድ ችግር ይመጣል።
በጨዋታው ስለነበራቸው ደካማ እና ጠንካራ ጎን?
በእኛ በኩል በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረው ድክመት እነሱ ጫና ለመፍጠር ወደ እኛ ሲመጡ ከጀርባ የሚተውሉንን ሰው መጠቀም አለመቻላችን ነው። ይሄ የእኛ ደካማ ጎን ነበር። ይህንን እረፍተ ላይ ተነጋግረን ነበር። ነገርግን በጊዜ ነው ሰው በቀይ ካርድ የወጣብን። ይሄ ሆኖም ጨዋታውን መቆጣጠራችን ጠንካራ ጎናችን ነበር።
ቡድኑ ላይ ስለታየው የዳኞችን ውሳኔ ያለመቀበል ችግር?
ዳኞች መከበር አለባቸው። ግን ዳኞች ማወቅ ያለባቸው ተጫዋቾች የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ነው። ምናልባት ተጫዋቾች መስመሩን ያለፈ ነገር ሲያደርጉ መቀጣት እንዳለባቸው እስማማለሁ። ግን ዳኞች ተጫዋቾች የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ማወቅ አለባቸው። አንዳንድ ዳኞች ይሄንን ነገር ማስተዋል ያለባቸው ይመስለኛል። እርግጥ ጨዋታውን የሚቆጣጠሩት ራሳቸውን አስከብረው ነው። ግን ዋናው ትኩረታቸው ራሳቸውን ማስከበር ላይ ከሆነ ለተጫዋቾቹን ጥበቃ ሳያደርጉ ይወጣሉ። አንዳንድ ዳኞች መጠየቅ አይፈልጉም። ሲጠየቁ ወዲያው የመቆጣት ነገር ያሳያሉ። ይሄ መስተካከል አለበት። በተጫዋቾች በኩል ያለውን እኛ ማስተካከል ካለብን እናስተካክላለን።
አቡበከር ናስር የጌታነህን ሪከርድ ይሰብራል?
አቡበከር ቀሪ ጨዋታዎች ስላሉ ዕድሎች አሉት ብዬ አስባለሁ። ጎሎችንም አስቆጥሮ ሪከርዱን ይሰብራል የሚል እምነት አለኝ።
© ሶከር ኢትዮጵያ