ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የ25ኛ ሳምንት የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ መርሐ-ግብር የሆነውን ጨዋታ እንደሚከተለው ቃኝተነዋል።

ድል ካደረጉ ሰባት ጨዋታዎች ያለፋቸው ባህር ዳር ከተማዎች የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታቸውን በማሸነፍ የተሻለ ደረጃን ይዘው ለማጠናቀቅ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታሰባል። ከሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶች በኋላ ነገ ወደ ሜዳ የሚገቡት ወላይታ ድቻዎች ደግሞ ወደ አሸናፊነት በመመለስ ወደ ደረጃ ሠንጠረዡ አናት መጠጋትን በማለም ጨዋታውን እንደሚቀርቡ ይገመታል።

በወጥነት ወጥ ያልሆነ ብቃት እያሳየ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ በመጨረሻ ጨዋታው ከሊጉ ቀድሞ መውረዱን ያረጋገጠውን ጅማን ገጥሞ ሳያሸንፍ ቀርቷል። በዚህም ውጤት ቡድኑ ሲመኘው የነበረውን የሁለተኛ ደረጃን (በአፍሪካ መድረክ የሚያሳትፈውን) እንደማያገኝ አረጋግጧል። አሁን ቡድኑ የቀረው በድል የጀመረውን የዘንድሮ የውድድር ዓመት (ሲዳማ ቡናን 3-1) በድል ማገባደድ እና የተሻለ ደረጃን ይዞ መጨረስ ብቻ ነው። የተሻለ ደረጃን ይዞ ለመጨረስ ደግሞ የነገው ሦስት ነጥብ ብቻ በቂ አይደለም። ከበላዩ የሚገኙ ሁለት (ሀዲያ እና ጊዮርጊስ) እንዲሁም ከበታቹ የሚገኙ ሦስት ቡድኖች (ሰበታ፣ ሀዋሳ እና ድቻ) ነጥብ መጣል አለባቸው። ይህ ቢሆንም ግን በእጁ ያለውን ብቸኛ የነገውን ጨዋታ አሸንፎ የቡድኖቹን ውጤት መጠበቁ መልካም ነው። ነገርግን ባለፉት ጨዋታዎች ስል ሆኖ ያልተገኘው የቡድኑ የፊት እና ክፍተቶች የሚታዩበት የኋላ መስመር ጨዋታዎችን እንዳያሸንፍ እያደረጉት ይገኛሉ። በነገውም የመጨረሻው ጨዋታ ቡድኑ ሁለቱ ክፍሎች ላይ ማሻሻያ አድርጎ ካልገባ ከወላይታ ድቻ ጠንካራ አጨዋወት ጋር ተያይዞ ፈተና ላይ ሊወድቅ ይችላል።

የአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ቡድን በርካታ ፈጣን ተጫዋቾችን በስብስቡ ይዞል። በተለይ ከወገብ በላይ የሚገኙት ተጫዋቾች ፍጥነት ለተጋጣሚ ተከላካዮች አስቸጋሪ ነው። ከዚህም መነሻነት ነገም በተንጠልጣይ እና ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች ጠጣሩን የድቻ የኋላ መስመር በማለፍ ግብ ለማስቆጠር እንደሚታትር ይገመታል። በዋናነት ደግሞ በመጀመሪያውም ዙር ጨዋታ እንደታየው የቡድኑ የጎል ማስቆጠሪያ ምንጭ የሆነው ፍፁም ዓለሙ የድቻ ተጫዋቾች የትኩረት መሐከል እንደሚሆን ይታሰባል። ይሄንንም በመገንዘብ አሠልጣኙ ሌላ የማይገመት የማጥቂያ አማራጭ ይዘው ካልመጡ ተጋጣሚን ቀድሞ አጥንቶ በመቅረብ የማይታሙት አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ማምከኛውን አዘጋጅተው ሊመጡ ይችላሉ።

ሽንፈት ካስተናገዱ አራት ጨዋታዎች ያለፋቸው ወላይታ ድቻዎች ደግሞ በመጥፎ የጀመሩትን የዘንድሮ የውድድር ዓመት በጥሩ ሁኔታ ለማገባደድ እየተጉ ይመስላል። በተለይም አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከሾሙ በኋላ በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ረገድ ጠንካራ ሆነዋል። በተለይ ደግሞ በሁለቱም ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ላይ ያለው የተጫዋቾች ትኩረት፣ ድፍረት እና ጥንካሬ ከፍ ብሏል። ነገም ይሄንን ጠንካራነት ለማስቀጠል ድል ከናፈቀው ባህር ዳር ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። በዋናነት ደግሞ የነገው ተጋጣሚያቸውን እና ቀጣይ ተጋጣሚያቸውን (ሲዳማ ቡና) ማሸነፍ ደረጃቸውን ከ8 ደረጃ እጅግ ከፍ ሊያደርግ ይችላል። ይሄንንም በማሰብ ቡድኑ በጥሩ የዝግጅት ልዕልና ወደ ሜዳ ሊገባ ይችላል።

እንደ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ሁሉ ከጅማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ለዚህኛው ጨዋታ እየተሰናዱ የሚገኙት ድቻዎች በዋናነት በሽግግሮች (ከመከላከል ወደ ማጥቃት እና ከማጥቃት ወደ መከላከል) ላይ ያላቸው ጥንካሬ የነገውን ጨዋታ ሊወስን እንደሚችል ይታሰባል። በተለይ ግጥግጥ ብሎ በመከላከል የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ፊት በመላክ እና ቁመታሙን አጥቂ ስንታየሁ መንግስቱን ዒላማ ያደረጉ ተሻጋሪ ኳሶችን በማዘውተር ግብ ለማስቆጠር ሊጥሩ ይችላሉ። ይሄንንም የቡድኑን የጨዋታ ባህሪ በመገንዘብ  ባህር ዳር ከተማ የተመጣጠነ የተጫዋቾች ቁጥር በተጋጣሚ እና በራሱ ሜዳ ላይ በማድረግ ጨዋታውን ሊከውን ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ መረቡን ሳያስደፍር የወጣው የቡድኑ የተከላካይ ክፍል ብቃቱ ተሻሽሎ መቅረብ አለበት። አለበለዚያ ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ብልጥ ተጫዋቾችን በያዘው የባህር ዳር የአጥቂ መስመር ሊቀጣ ይችላል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻ እስካሁን በሊጉ በሦስት አጋጣሚዎች ተገናኝተዋል። በሚገርም ሁኔታ ቡድኖቹ ሦስቱንም ግንኙነታቸውን በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። 2011 በነበረው የደርሶ መልስ ጨዋታ በተመሳሳይ 1-1 ሲለያዩ ዘንድሮ ደግሞ 0-0 ጨዋታቸውን ፈፅመዋል።

ያጋሩ