የአሠልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-2 ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻን አሸናፊ ካደረገው የረፋዱ ጨዋታ በኋላ ሱፐር ስፖርት ከአሰልጣኞች አስተያየት ተቀብሏል።

ዘላለም ሽፈራው – ወላይታ ድቻ

ስለ ጨዋታው?

በጨዋታው እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። ምክንያቱም በዋናነት ከመጣንበት የአቻነት ስሜት መውጣት ነበር ፍላጎታችን። ይሄንን ደግሞ በማሸነፍ አልያም በሽንፈት ነው መቀየር የሚቻለው። ስለዚህ እኛ ይሄንን በማሸነፍ ቀይረነዋል። በዚህም እጅግ በጣም ደስ ብሎኛል። ከመጨረሻው ጨዋታችን አንፃር በዛሬው ጨዋታ የተጫዋቾቻችን ፍላጎት ከሚገባው በላይ ጥሩ ነበር። ይሄንንም ተጠቅመን ድሉን አሳክተናል።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን እና ስለ ራሱ ቡድን እንቅስቃሴ?

እኛ በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ አጋጣሚዎችን አግኝተን ነበር። ከእረፍት በኋላ ደግሞ የእኛ ቡድን በሙሉ አቅሙ ተጫውቶ ጥንካሬውን አሳይቷል። ምናልባት ተጋጣሚያችን በሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቀዝ ብሎ የታየ ይመስለኛል። የእኛዎቹ ደግሞ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል።

ስለቸርነት ጉግሳ ብቃት?

ቸርነት ለእኔ ቡድን ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች ነው። ቸርነት የመስመር ተጫዋች እንደሆነ ይታወቃል። ከፍተኛ ኳስ የመግፋት ብቃት፣ ግብ የማስቆጠር ችሎታ እና ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን የማቀበል ብቃት አለው። በእኛ ሀገር ሁኔታ ደግሞ ከአንድ የመስመር ተጫዋች ከሚገባው በላይ ነው። ስለዚህ ቸርነት እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ እና ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች ነው። ነገርግን አሁንም በርትቶ መስራት አለበት። አሁን ያለውን ውዳሴ መውሰድ ብቻ ሳይሆን በደንብ መስራት ያስፈልገዋል።

ስለ ቀጣዩ የሲዳማ ጨዋታ?

እኛ አሁንም በመጣንበት የፍላጎት ደረጃ ነው የምንጫወተው። የማሸነፍ ፍላጎታችን እንዳለ ሆኖ ከወትሮ ሳንቀንስም ሳንጨምርም ነው የምንጫወተው።

ፋሲል ተካልኝ – ባህር ዳር ከተማ

ጨዋታው እንዴት ነበር?

ጨዋታው ሁለት መልክ ነበረው ብዬ አስባለሁ። በሁለተኛው አጋማሽ ተጋጣሚያችን ብልጫ ወስዷል። ከእኛም የተሻለ የጎል ዕድል ፈጥረዋል። ከዚህም መነሻነት ጎል ማግባታቸው የሚያስደንቅ አይደለም። በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረንን እንቅስቃሴ በሁለተኛውም አጋማሽ መቀጠል ስላልቻልን ጨዋታውን አተነዋል።

በውድድር ዘመኑ ቡድኑ ላይ ስለነበረ ክፍተት?

ድሬዳዋ ላይ በተከታታይ ነጥብ ጥለን ወደ ሀዋሳ ስንመጣ ከዛ ችግር ቶሎ አለመውጣታችን ትልቁ ክፍተታችን ነበር። እርግጥ በየጨዋታው የአቅማችንን ሞክረናል። ጨዋታዎችንም የምናሸንፍባቸውን ዕድሎችም ሁል ጊዜ ሜዳ ላይ እናገኛለን። እነዛን ግን አለመጠቀማችን ዋጋ አስከፍሎናል። ብዙ ጨዋታዎች ከእኛ አቅም በላይ አልነበሩም። እኛ እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ግለሰብ የምንሰራቸው ስህተቶች ዋጋ አስከፍሎናል።

በውድድር ዘመኑ ጠንካራ የሜዳ ላይ ተፎካካሪያችሁ ማን ነበር?

ሁሉም ቡድን ጠንካራ ነው። በተለየ መልኩ ይሄ ነው ብዬ መናገር ይቸግረኛል። ግን የፋሲል ጥንካሬ የሚታይ ነው። ከነጥቡ ርቀትም አንፃር ይሄንን እንረዳለን። በዚህ አጋጣሚ እንደውም ፋሲሎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ።

የውድድር ዘመኑ ኮከብ ተጫዋች ማነው?

ፍፁም ዓለሙ እና አቡበከር ናስር በዓመቱ የተለየ አቅም አሳይተዋል። ፍፁም የእኔ የሁል ጊዜ ኮከብ ነው። አቡበከር ደግሞ የሊጉ ክስተት ነበር።