” እስከ 1 ቢሊዮን ብር እናገኛለን ብለን አስበናል “

“ስፖርት ለኢትዮጵያ ሕብረት” በሚል መሪ ቃል ፋሲል ከነማ ባዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶችን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

ረፋድ በሸራተን አዲስ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተሰጠው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ፣ የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ስዩም ከበደ እና አንደኛው አምበል ያሬድ ባዬ እንዲሁም አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው ከተወጣጡ ግለሰቦች ጋር በመሆን በመድረኩ ተገኝተዋለወ። በቅድሚያም የጎንደር ከተማ ከንቲባ እና የፋሲል ከነማ የበላይ ጠባቂ የሆኑት አቶ ሞላ መላኩ በስፍራው ለተገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር እና ጎንደር ሊደረጉ ስለታሰቡት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብሮች ዝርዝር መባራሪያ መስጠት ጀምረዋል። 

“በቅድሚያ ፋሲል ከነማ ዋንጫ በማግኘቱ የቡድኑን ደጋፊዎች እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ክለቡ ለተገፉ አካባቢዎች ድምፅም ሆኖ ያገለገለ ነው። የጉዳት መተንፈሻ ሆኖ ሲያገለግል ነበር። በሀገራችንም ላለው ለውጥ ትልቅ ስራ ሰርቷል። ፋሲል ከክለብም በላይ ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ቡድኑ ያለፉትን ሁለት ዓመታትም ዋንጫ ለማግኘት ጫፍ ደርሶ ነበር። ግን በኮቪድ እና በመቐለ ዋንጫውን ተቀምቷል። ስለዚህ ለዋንጫ ስንጫወት የነበረው ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ነው።

“ፋሲል ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ናቸው። ይሄ ደግሞ ቡድኑ የኢትዮጵያ ተምሳሌት መሆኑን ያሳያል። ከየትም የመጡ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ሲሰለፉ የፈለጉትን ነገር እንደሚያሳኩም የሚያሳይ ነው። የፋሲል የአሸናፊነት ሚስጥር በአንድ ዓላማ መቆሙ እና ዓላማውን በሚያደናቅፉ ነገሮችን የማይሸበር መሆኑ ነው። ይሄ ደግሞ ሀገራችንን ውስጥ ለሚከሰቱት ነገሮች መፍትሄ የሚሆን ነው። ከዚህም መነሻነት ይሄንን ድል ከተራ ዋንጫ የማንሳት ድል ከፍ አድርገን እንየው የሚል ሀሳብ ያዝን። ስለሆነም ድሉን አሁናዊ የኢትዮጵያን ግንኙነት እናጠናክርበት ጎን ለጎን ደግሞ ፋሲል ለአፍሪካ የሚመጥን ጠንካራ ክለብ እናድርገው። ሊጉን ክለቡ አደለም አሸናፊው። አሸናፊው ኢትዮጵያ ነች። ስለዚህ ከዛሬ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን የእኔ ክለብ ነው ብሎ እንዲያስብ ነው የምንፈልገው። ፋሲል በኢትዮጵያ እንደነገሰው ሁሉ በአፍሪካ እግርኳስም እንዲነግስ እና ጎልቶ እንዲወጣ እንፈልጋለን። ይህንንም የሚያስችል እቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም እንዲያግዘን እንፈልጋለን። የፋሲል ትልቁ ሀብቱ ደጋፊው ነው። ክለቡ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ብዙ ደጋፊዎች አሉት።

ስለዚህ ቡድኑን በፍይናንስ ረገድ ማጠናከር እና የስፖርት መሰረተ ልማቶችን እንዲሟሉለት ማድረግ አለብን። ስለዚህ በአፍሪካም መድረክ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ ቡድን ነው መስራት ያለብን። ማጣሪያ ላይ ብቻ የሚወድቅ ቡድን እንዲሆን አንፈልግም። ቡድኑ ደካማ ከሆነ ውርደቱ የሁላችንም ነው። ጥንካራም ከሆነ ሞገሱ የሁላችንም ነው። 

“በዋናነት ይሄ ክለብ በከተማ አስተዳደሩ እየተደገፈ የመጣ ክለብ ነው። ከጠቅላላ የከተማው በጀቱ 5% ይመደብለታል። አሁን ግን ቡድኑ ከእኛ ትከሻ ወርዶ የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሆን እንፈልጋለን። አለበለዚያ እንደ አብዛኞቹ ክለቦች ታሪክ ሆኖ ሊቀር ይችላል። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የክለቡ ደጋፊ እንዲሆን ከጎኑ እንዲቆም እንጠይቃለን።” ከንቲባው ማብራሪያቸውን ቀጥለው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቱን ዓላማ ገልፀዋል።

” ‘ስፖርት ለኢትዮጵያ ህብረት’ የሚል መሪ ቃል ያለው የገቢ ማሰባሰቢያ ዋና አላማችን ሁለት ነው። አንደኛው ክለቡ ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው የማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ መላው ኢትዮጵያዊያን የሚሰለጥኑበት የእግርኳስ አካዳሚ ጎንደር ላይ እንዲኖረው ማድረግ ነው። በቅድሚያም ግንቦት 17 አዲስ አበባ ላይ በሸራተን ሆቴል ዝግጅት እናደርጋለን። በመቀጠል ደግሞ ግንቦት 20 ባህር ዳር ዝግጅት እናዘጋጃለን። በመጨረሻም ግንቦት 21 ጎንደር ላይ ይኖረናል። በእነዚህ ዝግጅቶች በድምሩ እስከ 1 ቢሊዮን ብር እናገኛለን ብለን አስበናል። በዋናነት ደግሞ በአዲስ አበባው ዝግጅት ጥሩ ነገር እንጠብቃለን። በሸራተኑ ዝግጅትም የመንግስት ባለስልጣናት እና የሀገር ሽማግሌዎችም ይገኛሉ (በሁሉም ክልል የሚገኙ)። በአጠቃላይ የመጨረሻ መልዕክቴ ክለባችንን የጋራ ጎጆ እናውጣው የሚል ነው።”

ከከንቲባው ንግግር በኋላ ቡድኑን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ያደረጉት አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ሀሳብ መስጠት ጀምረዋል። 

“ክለቡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲለፋበት የነበረውን ነገር ማሳካቱ እና የ2013 ዓም የሊጉ ቻምፒዮን በመሆኑ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። ሁላችሁም እንደምታቁት ስፖርት በኦሊምፒክ ያለው ፍልስፍና ለሰላም እና ለአንድነት ነው። ሀገራችን ደግሞ የካፍ ምስረታ ላይ ያላት አሻራ ትልቅ ነው። ግን አሁን ያለን ቦታ እንደ መስራችነታችን አይደለም። የስፖርት ቤተሰቡ ደግሞ ያለው ስሜት ከፍ ያለ ነው። እንደምታቁት በርካታ ክለቦች መዋቅራቸው ጠንካራ ባለመሆኑ ከስመው ቀርተዋል። ዘንድሮ ራሱ ከደሞዝ እና ከተለያየ ነገር ጋር ተያይዞ ላይቀጥሉ የሚችሉ ክለቦች አሉ። 

“እኔ 2012 መጀመሪያ ላይ ነው ወደ ክለቡ የመጣሁት። ከመጣሁ ጀምሮ ለስፖርቱ ትልቅ ፍቅር ያላቸው አመራሮች በመኖራቸው ክለቡ እያደገ ነበር። የበፊቱም ሆነ የአሁኑ ከንቲባ ለእኛ ቅርብ ናቸው። አሁን ግን ክለቡ በሁለት እግሩ መቆም አለበት። እንደምታቁት ህይወታቸውን ያጡ ደጋፊዎች አሉ። ሲጀምር እግርኳስ የወጣቶች ስፖርት ነው። ለዚህ ደጋፊ ደግሞ ትልቅ ስታዲየም ያስፈልገዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎችም የሚጎለብቱበት አካዳሚ ያስፈልጋል። ይህ እንዲሳካ ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ ደግሞ ሀገር ትጠቀማለች። አሁንም ሌሎቹ ክለቦች ፋሲል እንደሚጓዝበት መንገድ ካልጀመሩ መክሰማቸው አይቀርም። ክለብ ከሌለ ብሔራዊ ቡድን የለም።
“የስኬታችን ሚስጥር ግልፅ ነው። 2011 የነበሩ ተጫዋቾችን አልበተንም። 2012 እኔ ስመጣም ትንሽ ነው ያስተካከልነው። እንደአጋጣሚ ደግሞ በአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እኔ ከደጋፊዎች ጋር ተዋወቅን። በዛም ዓመት ዋንጫውን እንዴት እንዳጣት ይታወቃል። 2013 ላይም ኮቪድ ሊጉም እሳቋረጠን ድረስ መሪ ነበርን። ዘንድሮም ይሄንን ነው ያስቀጠልነው። አሁንም በቀጣይ መጠነኛ መሻሻል እያደረግን እንቀጥላለን። ዘንድሮ ዋንጫውን እንድናገኝ ተጫዋቾቻችን መስዕዋትነት ከፍለዋል። ይሄንንም በማሳካታችን ሁላችንም ተደስተናል። ክለቡ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢ የመጡ ተጫዋቾች አሉ። ኢትዮጵያን በፋሲል ከነማ ውስጥ ብዙ እናያለን።” ብለዋል።
ከአሠልጣኙ በመቀጠል የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው መናገር ጀምረዋል። አሠልጣኙም ፋሲል የሊጉ አሸናፊ በመሆኑ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ቡድኑ ራሱን ችሎ እነንዲቆም መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።

“ለመላው የፋሲል ደጋፊዎች እና ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሁም ለእግር ኳስ አፍቃሪ እግርኳሳችን ላይ አዲስ ኃይል ስለተፈጠረ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ። አመራሩንም እንኳን ደስ አላችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ነው። በዚህ ምንም ጥርጥር የለኝም። ህዝቡም እግርኳስ ይወዳል። ሀገሩንም ይወዳል። ህዝቡን ደግሞ አንድ የሚያደርግ ክለብ በልመና እና ድጋፍ መንቀሳቀስ የለበትም። ቻምፒዮን የሆነ ክለብ ወደ ገንዘብ ልመና መግባት የለበትም ነበር። እግርኳስ ትልቅ አቅም አለው። የፋሲል ከነማ ቡድን በጎንደር አካባቢ ብቻ በመጡ ተጫዋቾች ስኬታማ የሆነ አይደለም። ከተለያየ አካባቢ የመጡ እንጂ። ስለዚህ ቡድኑ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው። እንዳልኩት የኢትዮጵያ ህዝብ እግርኳስ ይወዳል። አሁን ህዝቡ ያጣው ወደ ስፖርቱ የሚያመጣው አካል ነው። ሁሉም መሸርሸር ነው ፍላጎቱ። እንደተባለው ፋሲል ብቻ አይደለም ያሸነፈው ኢትዮጵያ ነው ያሸነፈው። በአጠቃልይ እግርኳስ በልመና አይመራም። ፋሲል የራሱ ገቢ ሊኖረው ይገባል። ፋሲል ብቻ አይደለም ሁሉም ክለቦች ገንዘብ ማመንጨት እና ማምጣት አለባቸው። መንግስት ቢያቆም ክለቦች ህልውናቸው ይዘጋል።”
በመጨረሻም የቡድኑ አምበል ያሬድ ባየ አጠር ያለ ሀሳቡን አጋርቷል። “ፋሲል ከነማ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት። ልዩነታችን አንነታችን ሆኗል። አንድነታችን ደግሞ አሸናፊ አድርጎናል። እዚህ የደረስነው በብዙ መከራ ነው። በቀጣይ ይሄ መደገም የለበትም። አመቱ መጀመሪያ ላይ ስንነሳ አሸናፊ እንድንሆን ነው። ይሄንንም አሳክተናል። አሁን ደግሞ በአፍሪካ መድረክ ተሳታፊ ነን። ለዚህ ደግሞ ገንዘብ ያስፈልጋል። ፋሲል ከነማን መርዳት ኢትዮጵያን መርዳት ነው።” ብሏል።

ከአራቱ ሰዎች ንግግር በኋላም በስፍራው የተገኙ ጋዜጠኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን መሰንዘር ጀምረዋል። በተጠየቁት ጥያቄዎች መሠረትም ከንቲባው እና አሠልጣኙ ምላሽ ሰጥተዋል። በምላሾቹ መካከልም ክለቡ 1 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማሰቡ፣ ክለቡን ለማሳደግም ከቦርድ መዋቅር ጀምሮ ስራዎች እንደሚሰሩ፣ ከስፖንሰር ጋር በተያያዘ ጠንካራ ስራ እንደሚከወን፣ 100 ሺ ቋሚ (የተመዘገቡ) ደጋፊዎችን ለመያዝ እቅድ መያዙ፣ በአጭር ጊዜ እቅድ የአሁኑን ስታዲየም የማደስ ከዛ በቀጣይ ዋናውን ስታዲየም የመስራት ሀሳብ መኖሩን ተብራርቷል።