ሪፖርት | በዋንጫ ሥነ-ስርዓት በታጀበው ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ዐፄዎቹን ከኃይቆቹ ያገናኘው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ፋሲል ከነማዎች ከድሬዳዋው ሽንፈት አንፃር ይድነቃቸው ኪዳኔ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ ፣ አምሳሉ ጥላሁን ፣ ሰዒድ ሀሰን ፣ ሀብታሙ ተከስተ ፣ ሽመክት ጉግሳ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ፍቃዱ ዓለሙን በማሳረፍ ሳማኬ ሚኬል ፣ ሄኖክ ይትባረክ ፣ ይሁን እንዳሻው ፣ አቤል እያዩ ፣ ዓለምብርሀን ይግዛው ፣ ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ፣ በዛብህ መለዮ እና ዳንኤል ዘመዴ ወደ ቋሚ አሰላለፍ አምጥተዋል። ከወልቂጤ ከተማ ጋር ነጥብ ከተጋሩ በኋላ ዛሬ ወደ ሜዳ የገቡት ሀዋሳዎች ደግሞ ዳግም ተፈራን በሜንሳህ ሶሆሆ እንዲሁም ተባረክ ሔፉሞን በዳንኤል ደርቤ ብቻ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ከጨዋታው አስቀድሞ የሊጉ ዋንጫ በክብር ዘብ ታጅቦ የፋሲል ተጫዋቾች ደግሞ በሀዋሳ ስብስብ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ፋሲል ከነማ ዋንጫውን በሚያነሳበት በዛሬው የጨዋታ ቀን በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ደጋፊዎች በውስን ቁጥር ወደ ሜዳ እንዲገቡም ተደርጓል። በሌላ በኩል የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት በተጨዋችነት ዘመኑ 1996 ላይ የሊጉን ክብር በአምበልነት ሲያነሳ አሰልጣኙ ለነበሩት ከማል አህመድ የቡድኑን ምስል የያዘ ፎቶ በስጦታ መልክ በማበርከት የቀድሞው አለቃውን አክብሯል።

በጥሩ የፉክክር ግለት የጀመረው የመጀመሪያው አጋማሽ በተመሳሳይ መንፈስ የተጠናቀቀ ነበር። እርግጥ ነው ለረጅም ደቂቃዎች ከባድ ሙከራዎችን ባናይም በሁለቱም በኩል ለማጥቃት ይደረጉ የነበሩ ጥረቶች በግልፅ ይታዩ ነበር። በቀዳሚነት ብልጫ የነበራቸው ሀዋሳ ከተማዎች በሁለቱ መስመሮች በተለይም በቀኝ በኩል አመዝነው ቶሎ ቶሎ ወደ በተጋጣሚያቸው አጋማሽ ላይ መግባት ችለው ነበር። በሙከራ ደረጃ ግን 10ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከግራ መስመር ያሻማል ተብሎ የተጠበቀውን ኳስ በቀጥታ ሞክሮ ወደ ላይ የተነሳበት አጋጣሚ ብቻ ተጠቃሽ ነበር። ተደጋጋሚ ግጭቶችን እያስተናገደ በቀጠለው ጨዋታ ግን የሀዋሳዎች ብልጫ እየቀነሰ ሄዷል።

ወደ ፊት ሲሄዱ ቅብብሎቻቸው ይቆራረጡባቸው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች የሀዋሳን እንቅስቃሴ በቶሎ መሀል ላይ ለማፈን እና ወደ ፊት ለመሄድ ጥረት ሲያደርጉ ቢታዩም የማጥቃት ሽግግሮቻቸው አስፈሪ መሆን የጀመሩት ከውሀ ዕረፍቱ በኋላ ነበር። በዚህ ወቅትም በመጀመሪያው ሙከራቸው ጎል አግኝተዋል። 31ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ይትባረክ ከግራ መስመር በረጅሙ የላከውን ኳስ ምኞት ደበበ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ዓለምብርሀን ይግዛው አግኝቶ ነው ያስቆጠረው። ሀዋሳዎች በቶሎ ወደ ቀደመው የማጥቃት ጉልበታቸው ተመልሰው ጫና መፍጠር ሲችሉ 36ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ከኤፍሬም አሻሞ ከተነሳው ኳስ አለልኝ አዘነ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ በመቀስ ምት ያደረገውን ሙከራ ሚኬል ሳማኬ አውጥቶበታል።

የፉክክር ግለቱ ይበልጥ ከፍ ብሎ በታየባቸው የመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ግብ በመድረሱ በኩል የተሻሉ ሆነው ታይተዋል። ጨዋታው ወደ ዕረፍት ከማምራቱ አስቀድሞም ሀዋሳዎች አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። 43ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የመጣውን ኳስ ሳማኬ በአግባቡ መያዝ ተስኖት ኤፍሬም አሻሞ ከቅርብ ርቀት ሲሞክር ሳማኬ በድጋሚ አድኖታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም መስፍን ታፈሰ ከአለልኝ አዘነ የደረሰውን ኳስ አክርሮ መትቶ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል።

ከዕረፍት መልስም የሀዋሳዎች ጫና ቀጥሎ ታይቷል። ለፋሲል ግብ ክልል ቀርበው የነበሩት ሀዋሳዎች ከርቀት በአለልኝ ካደረጉት ሙከራ ውጪ ሌሎች ዕድሎችን ሳያገኙ ፋሲሎች ለግብ ቀርበው ነበር። 56ኛው ደቂቃ ላይ የዳንኤል ዘመዴን ረጅም ኳስ ተከተሎ እና የዳግም ተፈራን የተሳሳተ የጊዜ አጠባበቅ ተጠቅሞ ሙጂብ ቃሲም ወደ ግብ የላካትን ኳስ የቀድሞው የአዳማ የኋላ ክፍል አጣማሪው ምኞት ደበበ ከግብ ስር አውጥቶበታል። በእንቅስቃሴው ወቅት ጉዳት የገጠመው ዳግም ለቀጣይ አራት ደቂቃዎች ህክምና ሲደረግለትም ቆይቷል። ጨዋታው ሲቀጥል ሀዋሳ ከተማዎች ብቻሉት ፍጥነት ወደ ፊት ለመሄድ የሙያደርጉትን ጥረት ሲቀጥሉ ፋሱሎች ኳስ ተቆጣጥረው ጨዋታውን ለማቀዝቅዝ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል።

ፍጥነቱ ዝግ እያለ በመጣው ጨዋታ ሀዋሳዎች ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች በሚነሱ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ወደ ግብ ቢደርሱም ጠንካራ መከራዎችን ማሳየት አልቻሉም።
85ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ተነስቶ ሳጥን ውስጥ የተነካካውን ኳስ ወንድምአገኝ ኃይሉ ከቅርብ ርቀት አክርሮ ሞክሮ በሳማኬ የተመለሰበት አጋጣሚ ግን ኢላማውን የጠበቀ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር። በጭማሪ ደቂቃ ጨዋታው ከባባድ ሙከራዎች ሲያስተናግድ የመስፍን ታፈሰ የግንባር ሙከራ በሳማኩ ሲድን ፋሲሎች በመልሶ ማጥቃት ግብ ላይ ደርሰው የሙጂብ ሙከራ ወደ ውጪ ወጥቷል። ጨዋታው ተጠናቀቀ ሲባል ግን የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ ይትባረክ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ አስቆጥሮ ሀዋሳ ነጥብ እንዲጋራ አድርጓ ጨዋታው ተፈፅሟል።