የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ባዘጋጀው አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ ዙሪያ ለጠቅላላ ጉባዔ ከመቅረቡ በፊት ነገ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት ያከናውናል፡፡
ፊፋ ለአባል ሀገራቱ ባስታወቀው አዲስ አሰራር መሠረት የተከለሰው የፌዴሬሽኑ ረቂቅ የመዋቅር ደንብ ከ2006 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሚተዳደርበት ደንብ ብዙ የሚቀሩት እና በየወቅቱ ከሚለወጠው የፊፋ ደንብ ጋር በተቃራኒው የቆመ በመሆኑ ለማሻሻል ያለመ ነው ተብሎለታል።
በውይይቱ ላይ የክለብ አመራሮች፣ የማኅበራት ተወካዮች እና እግር ኳሱ የሚመለከታቸው አካላት ይገኙበታል የተባለ ሲሆን በመስከረም ወር በሚደረገው የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከመፅደቁ በፊት መወያየቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በነገው ዕለት አዲስ አበባ ኢሊሌ ሆቴል ከ2፡30 ጀምሮ ውይይት ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት በቀረበው ደንብ ላይ ሙያዊ ትችቶች፣ ሀሳቦች እና በተዘጋጀው ደንብ ላይ መሻሻል አለባቸው የሚባሉ አስተያየቶች እንዲሰጡበት ይጠበቃል፡፡